NEWS

ማሪታይም ኢንዱስትሪው እና ያልተፈቱት ችግሮቹ

By Admin

March 31, 2017

ማሪታይም ኢንዱስትሪ ከባሕረኞች ሥልጠና ጀምሮ እስከ ዕቃዎች ጭነትና መርከቦች ስምሪት ድረስ የሚያጠቃልል ዘርፍ በመሆኑ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ለአንድ አገር የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ቢሆንም ኢትዮጵያ የባሕር በር ካጣች ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት ተዘንግቶ መቆየቱ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ በተለይ በማሪታይም ኢንዱስትሪው ሁሉንም ደረጃዎች ማዕከል ያደረገና ከጀማሪና መሰረታዊ ሥልጠናዎች ባሻገር ሌሎች ደረጃዎችን ማለትም «ማኔጄሪያል፣ ችፍ፣ ማስተር» ወዘተ… ማዕረጎችን መሰረት ያደረጉ የማሪታይም ማሠልጠኛ ማዕከላት በአገሪቱ አለመኖር ዘርፉ እንዳያድግ ማነቆ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለማሪታይም ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት ባሕረኞችን በስፋት በማሠልጠን ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችላቸውን ዕድል በማመቻቸት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲያግዙ ብሎም ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ቢጥርም፤ በአገሪቱ የሚሰጡ ሥልጠናዎች በጀማሪ ደረጃ ብቻ መሆናቸው፣ ቋሚ ማሠልጠኛ ተቋም አለመኖሩ፣ በውስን ሥልጠና በዘርፉ የተመረቁትንም ቢሆን ሥራ የሚያገናኝ ራሱን የቻለ ህጋዊ ተቋም (ኢንስቲትዩት) አለመኖሩ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ ማድረጉን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ የባሕረኞች ማህበር ሊቀመንበር ችፍ ጠለሃ ኢብራሒም እንደሚሉት፤ ማሪታይም ኢንዱስትሪ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለአንድ አገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ቢችልም ዘርፉ በኢትዮጵያ በተገቢው ሁኔታ ባለማደጉና ሁሉንም አይነት የባሕረኛ ሙያ ደረጃዎች መሰረት ያደረገ ማሠልጠኛ ተቋም አለመኖር አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንዳታገኝ አድርጓል፡፡ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የምትቆጣጠረው የባሕር በር ባለመኖሩ ወጣቱ የባሕር በር በሌላት አገር ላይ ባሕረኛ መሆን አያስፈልግም የሚል አመለካከት እንዲይዝ ያደረገ ሲሆን፤ በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተማረው ወጣት የግል ጥረቱ ውስን እንዲሆንና በዘርፉም የሚገባውን እድገት እንዳያመጣ አድርጓል፡፡

የባሕረኞች ማህበር ሊቀመንበር ችፍ ጠለሃን ጨምሮ አብዛኛው ባሕረኛ በግል ጥረቱ የረዥም ጊዜ የባህር ላይ የሥራ ልምድ ማግኘት መቻሉን በመግለፅ፤ ዓለም አቀፍ ህግጋቶች እየጠነከሩ መምጣታቸውና ከሥራው ጋር ተያያዥ በሆነ መልኩ መደበኛ ሥልጠና በመውሰድ ሰርተፍኬት ማግኘት አለመቻላቸው በሥራቸው ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ሁሉንም ደረጃዎች ማዕከል ባደረገ መልኩ ሥልጠና የሚሰጡ ተቋማት ቢኖሩ ዘርፉ ማደግ የሚችል መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

እንደ ችፍ ጠለሃ ማብራሪያ፤ ዘርፉን ለማሳደግ ዓለም አቀፍ መስፈርተኞችን መሰረት ያደረገና ከጀማሪ እስከ «ማኔጄሪያል፣ ችፍ፣ ሰከንድና ፈርስት ኢንጂነር» ደረጃዎች ድረስ ማሠልጠን የሚችሉ ማዕከላት ያስፈልጋሉ፡፡ እንዲሁም አገሪቱ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የምትችለው ወደብ በኪራይም ሆነ ለተወሰኑ ዓመታት መግዛት ብትችል በወደብ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ማቃለልና የወጪ ንግዱን ማሳለጥ የሚቻል መሆኑንና የተጫነው ዕቃም ለብዙ ጊዜ እንዳይዘገይ፣ የወደብ ክፍያው (ዴሜሬጅ) በየጊዜው እንዲጨምር፣ ቢሮክራሲያዊ ችግሮችና አላስፈላጊ ክፍያዎችን ማስቀረት ይቻላል፡፡

አገሪቱ በማሪታይም ኢንዱስትሪው እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የዘርፉን ጠቀሜታ በመረዳት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ባለመቻሉና ወጣቱም እንዲገነዘበው ባለመደረጉ ነው የሚሉት ደግሞ የባሕረኞች ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር ማስተር ካፒቴን ዘሪሁን ወዬሳ ናቸው፡፡

ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዥያና መሰል አገሮች በርካታ የሰው ኃይላቸውን በባሕረኝነት አሠልጥነው ወደ ተለያዩ አገሮች በመላካቸው ለምጣኔ ሀብታዊ እድገታቸው ያለው አስተዋጽኦ ከሁሉም በልማት መስክ የበለጠ መሆኑን የሚጠቁሙት ካፒቴን ዘሪሁን፤ ወጣቱ ስለ ባሕረኝነት ሙያ በሰፊው አለማወቁና በትክክል አለመረዳቱ በመስኩ ተሰማርቶ ህይወቱን እንዳይቀይር ሆኗል፡፡

በሙያው ሠልጥነው ወደ ተለያዩ አገሮች ለሥራ የሚላኩ ባሕረኞች ገቢን የሚቆጣጠርና ለሥራ የሚያሰማራ ተቋም ቢኖር የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባና አገርም ባሕረኞችም እንዲጠቀሙ በማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ እንደሚሆን ካፒቴን ዘሪሁን ያስረዳሉ፡፡

በባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክ አካዳሚ የ«ፐርሰናል ሰርቫይቫል ቴክኒክና ፒ.ኤስ.ቢ.አር.ቢ. ኢንስትራክተር» ግርማ ታደሰ እንደሚያብራሩት፤ የባሕረኝነት ሙያ አለመለመዱና ከጥቂት የዘርፉ ባለሙያዎች በቀር በርካታ ወጣቶች ግንዛቤው የሌላቸው በመሆኑ እንደ ሥራ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቅሙ እየታወቀ በመምጣቱ ትኩረት እያገኘ ነው፡፡

ኢንስትራክተር ግርማ ታደሰ በኒር ኮስታል አካባቢ በማሪን ኢንጂንና ዴክ ስር ሆነው በተለያዩ አገሮች የሚሠሩ ባሕረኞች ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት በሚያወጣቸው መስፈርቶች ሁሉን አቀፍ ሥልጠናዎች መስጠት እንዲቻል ያሉ ማዕከላትን በግብዓትና ልምድ ባላቸው የሰው ኃይል በማሟላት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን የማሪታይም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ልዩወርቅ አማረም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ባለሥልጣኑ በራሳቸው ጥረት በመንቀሳቀስ በተለያዩ አለማት ለሚሠሩ 500 ባሕረኞች፣ በዓረቢያን ገልፍ አካባቢ ለሚሠሩ ደግሞ 261 ባሕረኞች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ቢሰጥም ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት (IMO) በየጊዜው ከሚያሻሽላቸው የመመዘኛ መስፈርትና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት አኳያ ሁሉንም ደረጃዎች ማዕከል ያደረገ የማሠልጠኛ ማዕከል በኢትዮጵያ አለመኖሩ ዘርፉ የሚፈለግበትን ያህል እንዳያድግ አድርጓል ይላሉ፡፡

የባሕርዳርም ሆነ የባቡጋያ ማሪታይም ማሠልጠኛ ተቋማት ለማሪታይም ኢንጂነሮችና ለቴክኒካል ኦፊሰሮች በጀማሪ (ሰርድ ኦፊሰር፤ ሬቲንግ) ደረጃ ሥልጠናዎችን ቢሰጥም በሰከንድ ኢንጂነር፣ ችፍ ኢንጂነርና በማኔጄሪያል ደረጃ እንዲሁም የዴክ ትምህርት ክፍል ስለሌለው ሁሉንም ማዕከል ያደረገ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያትም አድቫንስድ ኮርሶችን መስጠት አይችልም የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ ከመሰረታዊ ሥልጠናዎች ባሻገር ቋሚ ማሠልጠኛ ማዕከላትን ለማቋቋም ባለሀብቱ በዘርፉ መሰማራትና በተለያዩ አገሮች ሲሠሩ የነበሩና ዕምቅ ችሎታና ልምድ ያካበቱ «ካፒቴኖች፣ ማስተሮች፣ ችፎችና ፈርስት ኦፊሰሮች»ም ሊቀናጁ ያስፈልጋል፡፡ ባለሥልጣኑም ማሠልጠኛ ማዕከላቱ ተገቢውን ግብዓት እንዲያሟሉና አድቫንስድ ኮርሶችን ሊሰጡ የሚችሉ «ችፍ ኢንጂነሮችን፣ ካፒቴኖችንና ማስተሮች»ን እንዲቀጥሩ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

`እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ አገሪቱ የባሕር በር ካጣች ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት ዘርፉ ተዘንግቶ በመቆየቱ እድገቱ በጀማሪ ደረጃ ላይ የሚገኝና ባሕረኞቹ ሥራ የሚያገኙት በራሳቸው ጥረት በመሆኑ ሥራ የሚያገናኝ ራሱን የቻለ ህጋዊ አካል አለመኖሩም ሥልጠናውን ወስደው ወደ ሥራ በቶሎ እንዳይሠማሩ ማነቆ ሆኗል፤ ይህን ለማስተካከልም የሚመለከታቸው አካላት ከባለሥልጣኑ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል፡፡ በተለይ ባሕረኞቹ ወደ ሌላ አገር ሄደው በሚሠሩ ጊዜ የራሳቸውን ህይወት ከመቀየር ባሻገር 85 በመቶ ገቢያቸው ወደ አገሪቱ የሚላክ በመሆኑ ለኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ልምዳቸውን በማካፈልና የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት እሴት ይጨምራሉ፡፡ ዑመር እንድሪ press