Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምሥራቅ አፍሪካን የመታው ድርቅ.

0 810

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምሥራቅዊው የአፍሪካ ክፍል በ60 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ መመታቱን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 የተከሰተው ኤልኒኖና ያስከተለው ላኒና የአየር ፀባይ በአብዛኞቹ የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት አስከትሏል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኡጋንዳና በሶማሊያ ምርት እንዲቀንስ በአንፃሩም በየአገሮቹ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝቦች የምግብ እጥረት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡

በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በደቡብ ሱዳንና በኡጋንዳ ሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረግ ላይ የሚገኘው ሉተራን ወርልድ ሪሊፍ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ በአገሮቹ ዋና ምግብ የሆነው የበቆሎ ምርት እ.ኤ.አ. በጥር 2017 ላይ መስጠት ከነበረበት መደበኛ መጠን በ50 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይህም አብዛኞቹ የየአገሮቹ ክፍሎች እ.ኤ.አ. እስከ ግንቦት 2017 ድረስ የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ድጎማ እንደሚያስፈልጋቸው አመላክቷል፡፡

አገሮቹ የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ሦስት (Integrated food Security Phase 3፣ IPC 3) ደርሰዋል፡፡ ይህም ማለት በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድርቁ ያስከተለውን ረሃብ ለመቋቋም የሚመገቡበትን ሰዓት ማራዘምና ማዘለል፣ የምግብ መጠን መቀነስ፣ ከእርሻ ውጭ ሥራ መፈለግ፣ የቤት ቁሳቁስና እንስሳትን መሸጥና የምግብ ፍጆታን መደጎም ጀምረዋል፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኬንያ በ23 ግዛቶች ድርቅ መግባቱን ተከትሎ ድርቁ ብሔራዊ አደጋ መሆኑን አውጀዋል፡፡ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች በድርቁ መመታታቸውንና አፋጣኝ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ የኬንያ መንግሥት እንደገለጸው፣ በድርቅ የተጎዱት ቁጥር እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2017 ወደ 2.4 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡ አሁን የወጡ መረጃዎች ግን ለድርቅ የተጋለጡ ወገኖች የተገለጸው ቁጥር ላይ ደርሰዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን መንግሥትም በአገሪቱ ባለው ጦርነትና በተሽመደመደው ኢኮኖሚ ሳቢያ ረሃብ መግባቱን አሳውቋል፡፡ 100 ሺሕ ሰዎች ረሃብ ውስጥ መውደቃቸውን፣ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ለረሃብ ሊጋለጡ መሆኑን አክሏል፡፡

በደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ. እስከ ጥር 2017 ድረስ 3.8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የምግብ እጥረት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል የተባለ ሲሆን፣ በየካቲት 2017 ቁጥሩ ወደ አምስት ሚሊዮን አሻቅቧል፡፡ ለረሃብ የተጋለጡት 100 ሺዎቹ ሊር፣ ፖኒየር፣ ሜይንዲትና ኮች በተባሉ ግዛቶች የሚኖሩ ናቸው፡፡

ረሃብ መግባቱን ማወጅ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ መሆኑን ያመለክታል ያለው ሉተራን ወርልድ ሪሊፍ፣ ብዙ ሞቶች ሳይመዘገቡ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡

ናይጄሪያ፣ የመን፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ለረሃብ አደጋ በእጅጉ የተጋለጡ በመሆናቸው፣ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪዎች ቅድሚያ የሰጡት ለእነዚህ አገሮች ነው፡፡ በአገሮቹ የደኅንነት ሥጋትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት መኖሩ ችግሩን ያጎላዋል በሚልም ከኬንያ፣ ከታንዛኒያና ከኡጋንዳ በተሻለ እጃቸውን ዘርግተውላቸዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን አስተባብሮ የሚሠራው ኦቻ በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና የመን የሚገኙ 20 ሚሊዮን ዜጎች ለረሃብ መጋለጣቸውን ገልጿል፡፡ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የረሃቡ ሁኔታ እንደሚከፋ ያሳወቀ ሲሆን፣ በረሃብ ምክንያት በሕዝቦች ላይ የተጋረጠውን ሞት ለመቀልበስ ለጋሽ አገሮችና ድርጅቶች እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቋል፡፡

በአገሮቹ በሚገኙ አንዳንድ ሥፍራዎች ረሃብተኞችን በውኃ፣ በሕክምና፣ በምግብ ለመድረስና ረሃብን ተከትሎ ከሚመጡ በሽታዎች ለመከላከልም ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ 5.1 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና 450 ሺሕ ሕፃናት ደግሞ ለከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አትቷል፡፡

በናይጄሪያ በረሃብ የተጎዱትን ለመታደግ 1.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ከለጋሾች የተገኘው 45.8 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ እንደ ድርጅቱ ሪፖርት፣ የተገኘው ገንዘብ ከሚያስፈልገው በአንድ ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን 100 ሺዎች ረሃብ ውስጥ ሲሆኑ፣ አንድ ሚሊዮን ያህል ረሃብተኛ ለመሆን ተቃርበዋል፡፡ አምስት ሚሊዮን ያህል ደግሞ አፋጣኝ የምግብና ለመኖር የሚያስፈልጉ ዕርዳታዎች ፈላጊዎች ናቸው፡፡

270 ሺሕ ሕፃናትም ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን ላይ የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ለመታደግ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ እስከ ማክሰኞ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የተገኘው ዕርዳታ 24.1 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ኦቻ አስፍሯል፡፡

በሶማሊያ 185 ሺሕ ሕፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ 2.9 ሚሊዮን ሰዎችም አስቸኳይ ዕርዳታ እየተጠባበቁ ነው፡፡ በአገሪቱ ያሉ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመርዳት 863.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ቢሆንም ለጊዜው የተገኘው 55.8 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

በየመን 7.3 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ዕርዳታ የሚጠባበቁ ሲሆን፣ 462 ሺሕ ሕፃናት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጋለጡ ናቸው፡፡ እነዚህን ዜጎች ለመርዳት ኦቻ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ቢልም፣ እስካሁን ያገኘው 130 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ አገሮች በተደጋጋሚ ድርቅ ብሎም ረሃብ የሚከሰት ቢሆንም፣ ከችግሩ ሲወጡ አይስተዋሉም፡፡ ድርቅ የትም የሚያጋጥም ቢሆንም ረሃብን ለመቋቋም ቀድሞ በመሥራት ሕዝቦችን ከረሃብ መታደግ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ሆኖም ጦርነት፣ ግጭትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በተደጋጋሚ በሚስተዋልባት ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ድርቅን በዓለም አቀፍ ዕርዳታ እንጂ በራስ አቅም ሲመክቱት አይስተዋልም፡፡

ኦክስፋም በተደጋጋሚ የሚከሰት ረሃብን አገሮች በራሳቸው መመከት እንዲችሉ፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች በድርቅ የሚጠቁ አገሮች በምግብ ምርት ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መርዳት አለባቸው ብሏል፡፡

በገጠር ለሚገኙ የአፍሪካ ሕዝቦች የመንገድና የኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ማሟላትና ለማኅበራዊ ጥበቃ የሚደረጉ ዕርዳታዎችን በመቀነስ አገሮቹ ራሳቸውን ማብቃት በሚችሉበት ላይ መሥራትንም ይመክራል፡፡

ለድንገተኛ ችግር መድረስ ወሳኝ እንደሆነ ያስታወሰው ኦክስፋም፣ ‹‹ችግሩ ለምን ይከሰታል? ‹‹እንዴትስ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም እንችላለን ብለን መጠየቅ አለብን፤›› ሲልም በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy