NEWS

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

By Admin

March 07, 2017

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት እየፈጠሩ ባሉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግስት የሰራተኛውን ችግር ለመፍታትና የኑሮ ሁኔታውን ለማረጋጋት በማሰብ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ማስተካከያውን ምክንያት በማድረግ ይመስላል የተለያዩ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪዎች ከወዲሁ መታየት ጀምረዋል።

ችግሩ መከሰቱን የገለጸው የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ፥ ጉዳዩን የሚከታተል ኮማንድ ፖስት በማቋቋምና ዳሰሳ በማድረግ የችግሮችን መነሻና መድረሻ መለየት ተችሏል ነው ያለው።

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አሰድ ዚያድ በዳሰሳው፥ አቅርቦትን መደበቅ፣ ዋጋ መጨመርና የሚዛን ቅነሳ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች መለየታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም ችግር ፈጣሪ የተባሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ከማድረግ ጀምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅሰዋል።

እርምጃዎቹ ከዚህ ቀደም ሲወሰዱ የመጡ ቢሆንም፥ አሁን ላይ ከነበረው በስፋትም በፍጥነት የተሻለ የእርምጃ የአወሳሰድ ስርዓት ዘርግተናል ብለዋል።

ህብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት ረገድ 8478 ነጻ የስልክ መስመርን ጨምሮ በአካል በመቅረብ ጥቆማ እንዲያደርግ ይበረታታል ነው ያሉት።

የዚህን ጥቅል ውጤት መነሻ በማድረግም እርምጃው ይወሰዳል ተብሏል።

ሚኒስትር ዲኤታው በዳሰሳው መሰረት በቁጥርና በአይነት ባይገለጽም እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ከመለየት ጀምሮ መፍትሄ እስከመስጠት የሚያደርሱ ስራዎች መጀመራቸውንም ገልጸዋል።

የተጀመሩት ስራዎችም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ችግሮቹን በመፍታት የሸማቹን ችግር በሚፈለገው ደረጃ እንዲፈቱ ይደረጋልም ብለዋል።

አማራጭ ገበያዎችን ማስፋትም በቀጣይ ትኩረት እንደተሰጠውም አንስተዋል።

ባለድርሻ አካላትና በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማትን ጨምሮ ህብረተሰቡም በዚህ ላይ ትልቅ አቅም ሊሆን ይገባል ነው የተባለው።

ለክልል ቢሮዎች ተመሳሳይ አቅጣጫ ወርዶ ወደ ተግባር እየተገባ ሲሆን፥ ችግር ፈጣሪ አካላትም ከዚህ አይነት ተግባራቸው እንዲታቀቡም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።