Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምዕራባዊያኖች በራቸውን ሲዘጉ እኛ ለሚሊዮኖች መጠጊያ ሆነናል!

0 436

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምዕራባዊያኖች በራቸውን ሲዘጉ እኛ ለሚሊዮኖች መጠጊያ ሆነናል! (አባ መላኩ)

ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድ መሰረት ያደረገ  ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መንግስት  መገንባት በመቻሏ ዘላቂነት ያለው  ሰላም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው አገራትም ጭምር እንዲሰፍን ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ነች። ሰላም የሁሉም መልካም ነገሮች የመጀመሪያው መስፈርት ነው። ሰላም ካለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይረጋገጣሉ፤  ሰላም ካለ ልማት አለ፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። የአገራችን  ዘላቂ ሰላም የተረጋገጠው ህገመንግስታችን  ለውስጣዊ ችግሮቻችንን ሁሉ  መፍትሄ መስጠት በመቻሉ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት በቀጠናው አገሮች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲዳብር የተለያዩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ከማከናወን ጎን ለጎን የሰላም አስከባሪ ሃይሎችን አሰማርቷል። የቀጠናውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥም  አገሮች በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲተሳሰሩ በርካታ ተግባሮችን በማከናወን ላይ ይገኛል። አገራችን  ትክክለኛ   የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መከተል በመቻሏ በአፍሪካ ሆነ  በአለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ አድጓል። በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል።

በአፍሪካ ሰላም ማስከበር  ረገድ  የኢትዮጵያን ያህል  አስተዋጽዖ ያበረከተ አንድም አገር የለም። ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ዳርፉርና አብዬ የሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። በመጫወትም ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ መከለከያ ሰራዊት ሰላም በተሰማራበት የሰላም ማስከበር አገራት ሁሉ በሚያሳየው ስነምግባር ምስጉን በመባል አድናቆት የተቸረው ሆኗል።

ኢትዮጵያዊያን ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በዲሲፒሊን የታነጹ  በመሆናቸው   በተሰማሩበት አገር ሁሉ  በህዝብ የተወደዱና ምስጉን በመሆን  ለሽልማት በቅተዋል። መከላከያ ሰራዊታችን ስነምግባር የጎደለው ቢሆን ኖሮ ማንም አገር አይፈልገውም ነበር። የኢትዮጵያ ሰራዊት  በአቢዬ  የሰላም አስከባሪ ሃይል ሆኖ ሲሰማራ የአንድ አገር ሰራዊት  በሁለቱም አገራት ማለትም በደብብ ሱዳንም ሆነ በሱዳን ተመራጭ ሲሆን በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ነው። ይህ የሚያመላክተው የአገራችን ሰራዊት በጠንካራ ዲሲፒሊን የታነጸ መሆኑን ነው። ስነምግባሩ የወረደን የሰላም አስከባሪ ሃይል ማንም አይፈልግም።

መከላከያ ሰራዊታችን የመንግስታችንና የህዝባችን ነፀብራቅ ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም ጎረቤቶቻችን ጋር ተቻችለን መኖር እንደምንችል ታሪክ ምስክር ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ በሌሎች አገራት ተወራ እንጂ አገራችን የትኛውንም አገር ለማጥቃት የተንቀሳቀሰችበት ወቅት እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል። ኢትዮጵያዊያን እንግዳን አስተናጋጅ ህዝቦች ናቸው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አሁን ላይ ያለውን በአገሪቱ ያሉትን የጎረቤት አገራት ስደተኞች ብዛት መመልከት ይቻላል።

አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን  ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጭምር ሙገሳን ተችሯታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ  በአብዛኛው ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ስናስታውስ እንኳን ለሌሎች አገሮች ዜጎች መጠለያ ልትሆን ይቅርና የራሷ ህዝቦችም በጦርነትና በረሃብ ሳቢያ የትውልድ ቀያቸውን  ጥለው የሚሰደዱባት የዕርስ በርስ ጦርነትና የረሃብ ተምሳሌት ተደርጋ በብዙዎች ትጠራ ነበር። ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል። በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት  በድርቅ ሳቢያ ረሃብ ተከስቶባቸዋል የተባሉ አገራት የመን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ናይጄሪያ  በተጠቀሱበት መዝገብ የአገራችን ስም አልተካተተም። ይህ የመንግስትና የህዝብ ጥረት ነው። ኢትዮጵያም በድርቅ የተመታች ብትሆንም ዜጎቿ ለረሃብ አልተጋለጡም። ይህ የሆነው መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው መስራት በመቻላቸው ነው።

ከላይ እንዳነሳሁት አገራችን የበርካታ ጎረቤት አገሮችን ስደተኞች አስጠልላለች።  ይህን ያህል ስደተኞችን ማስጠለል የሚፈጥረው ማህበራዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከባድ ቢሆንም አገራችን አቅም በፈቀደ ሁሉ ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው አድርጋለች። ኢትዮጵያ ይህን እያደረገች ያለችው በህዝቦች መካከል ያለው መተሳሰብ የበለጠ እንዲጠናከር በማሰብ እንጂ ይህን ያህል ቁጥር ያለው  ስደተኞችን ማስተናገድ የሚያመጣው  ኢኮኖሚያዊና ማሀበራዊ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።

ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት አላቸው የሚባሉት  የምዕራብ አውሮፓ አገሮች  ለስደተኞች በራቸውን ዝግ አድርገዋል። አሜሪካ ከዶናልድ ትራምፕ መመረጥ ብኋላ ስደተኛን ለመከላከል ከሜክሲኮ የሚያዋስናትን ድንበር በግንብ ለማጠር በመጣደፍ ላይ ነች። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለተቸገሩ ጎረቤቶቹ መጠጊያ ሆኗል። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መልካም ጉርብትናውን በተጨባጭ አሳይቷል። ህዝባዊነት ይህ ነው። አንድ ቆየት ያለ አባባል አለ። መልካም ጎረቤት ድመት፣ መጥፎ ጎረቤት ደግሞ  ዶሮ ያረባል ይባላል።

የቀጠናውን አገሮች በኢኮኖሚ ጥቅም ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ እያደረገች ካለችው ስራዎች መካከል አንዱ የታላቁ የህዳሴ ግድብ  ነው።  የኢፌዴሪ መንግስት የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ባደረገበት ወቅት   ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ የምትገነባውና ለአባይ ተፋሰስ አገሮች በተለይ ለሱዳንና ለግብጽ ያቀረበችው ገጸ በረከት ሲሉ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጹት ነበር።  ታላቁ  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ   አገሪቱ የጀመረችውን ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት  ለማስቀጠል የኃይል አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው።

የአገራችን ምጣኔ ሀብት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚያደርገው የመዋቅር ለውጥ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኃይል አቅርቦትን እንደሚያስፈልገው ቅቡል ሃቅ ነው። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት በየዓመቱ ከ20 እስከ 25 በመቶ ዕድገት እያሳየ  ነው። ይህን የሃይል ፍላጎቷን ማሟላት ካልቻለች እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት አይኖረውም። ይህ በመሆኑ ነው ኢትዮጵያ እንደ ጊቤ ሶስትና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ትላልቅ የሃይል ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የተገደደችው።

የኢትዮጵያ መንግስት አካባቢን የማይበክሉ በዋነኝነት የውኃ፣ የንፋስ፣ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን  በመገንባት ላይ ነች።  አባይን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም በየሚዲያው ሲገለጽ እንደነበረው  “ፍተሃዊ የውሃ  ሃብት ክፍፍል በሁሉም የተፋሰሱ አገራት መከከል” የሚል ነው። አንዳንድ የግብጽ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች አገላለጹን በአግባብ አልተረዱት ወይም መረዳት አልፈለጉም እንጂ “ፍተሃዊ”  የሚለው ቃል ሁሉንም የሚያግባባ ነው። ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአባይ ውሃ መገኛ ብትሆንም እንደአስተዋጽዖዬ ልጠቀም ወይም  እኩል ልካፈል የሚል መርህ አላራመደችም። ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ለሃይል ምንጭነት ከመጠቀም ውጪ እንደሱዳን ወይም ግብጽ ለመስኖ  ለመጠቀም የሚያስችል ሰፊ መሬት የላትም። በመሆኑም የህዳሴው ግድብ የወንዙን የውሃ መጠን የሚቀንስበት ሁኔታ አይኖርም።

ሱዳንና ግብጽ ስባሪ ገንዘብ ሳያወጡ ግድቦቻቸውን ከደለል ይታደጋሉ፤ አመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት ያገኛሉ፣ ከጎርፍ ስጋት ይድናሉ፤ በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ ሃይል ያገኛሉ፣ ከሁሉም በላይ  የህዳሴውን ግድብ ከደለል ለመታደግ ኢትዮጵያዊያን ሰፊ የተፋሰስ ልማት በማከናወን ላይ በመሆናቸው  የወንዙ ዘለቂት ህይወት ተረጋግጦላቸዋል። ይህ ሁሉ መልካም ነገር የመጣው ኢትዮጵያ እየገነባች ካለው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ነው።

የህዳሴው ግድብ ለእኛ ኢትየጵያዊያን የውሃ ማጠራቀሚያና የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ብቻ ሳይሆን እንደአድዋ ድል የትብብራችን ማሳያ ነው። ግብጻዊያን አሰዋን  ግድብ  ከውኃ  ማጠራቀሚያነቱ  ባሻገር ተጨማሪ ትርጉም እንደሚሰጡት ሁሉ፣ የታላቁ ህዳሴው ግድብም ለእኛ ኢትዮጵያዊያኖች ከኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታው  ባሻገር የሚያስተላልፈው መልዕክት እንዳለ መታወቅ አለበት። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መገለጫ በመሆኑ በማንኛውም ረገድ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ከመንግስታችን ጎን  እንደምንሰለፍ  ማንም ሊያውቀው ይገባል። መንግስታት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ ስርዓትም ይለወጣል፡፡ አገር  ግን ሁሌም አለች። በመሆኑም ለህዝባችን ዘለቂ ጥቅም ሁላችንም ከመንግስት ጎን ልንሰለፍ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy