Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰብዓዊ መብትን የማያውቁ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች” (ቶሎሳ ኡርጌሳ)

0 426

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ይህን ፅሑፍ ለማሰናዳት ሳስብ ወደ አዕምሮዬ በመጀመሪያ ሽው ብለው ያለፉት “መብትን የማያውቁ የመብት ተሟጋቾች” የሚለው የአንድ ወዳጄ ቅልብጭ ያለ መጣጥፍ ነው። መጣጥፉ በሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ታዛ ተጠልለውና የርዕዩተ-ዓለም ካባቸውን ተከናንበው ፖለቲካ የሚነግዱትን እንደ ሂዮማን ራይትስ ዎችና አምንስቲ ኢንተርናሽናል የመሳሰሉ የህዝቦችን ሰብዓዊ መብት ነጣቂዎችን የተመለከተ ነበር። ግና መጣጥፉን ሳነብ እነዚህ ፅንፈኛ የርዕዩተ-ዓለም አራማጆች እንሟገትለታለን የሚሉትን ሰብዓዊ መብትን አያውቁም። እናም ሰብዓዊ መብትን የማያውቁ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች” ቢባሉም ማንነታቸውን ይገልፀዋል ብዬ አስባለሁ።

ለዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ የሚሆነው ሰሞኑን የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም መስኮች ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት ያለው መሆኑን በሁሉም መስኮች በፍጥነት በማደግ ላይ ባለቸው አዲስ አበባ ውስጥ ተገኝቶ ለኢፌዴሪ የመንግስት ባላስልጣናት ቁርጠኝነቱን ሲገልፅ፤ ራሱን “ሂዩማን ራይትስ ዎች” እያለ የሚጠራው አክራሪ ኒዮ ሊበራል ተቋም ከሚከተለው ፀረ-ኢትዮጵያ የርዕዩተ-ዓለም አጀንዳው በመነሳት ‘ህብረቱ እንዴት ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሬ እሰራለሁ ይላል’ በማለት ያወጣው አስገራሚ መግለጫ ነው።

ይህ ፅንፈኛ የርዕዩተ-ዓለም ቡድን እያንዳንዱን የሀገራችንን ጉዳይ እንደ ጋዜጠኛ የዕለት ውሎው በማድረግ ተከታትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወነውን ሁሉን አቀፍ የዕድገት ዕቅድ በሐሰት ከሰብዓዊ መብት ጋር የግድ አያይዞ በመስፋት ለመቃወም የሚዳዳው ነው። እንዲያውም ሀገራትና አህጉራት ከሀገራችን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመወሰን የሚዳዳውም አስቂኝ የርዕዩተ-ዓለም ነጋዴ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ በሰብዓዊ መብት ሽፋን የሚንቀሳቀሰውና ዋነኛ ተልዕኮው እንደ ዲታው ጆርጅ ሶሮስ ያሉ ፅንፍ የወጣ ኒዮ-ሊበራሊዝም አራማጆችን ቀኖና (doctrine) እንደ ኢትዮጵያ በማገድ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ በግዳጅ ለመጫን የሚሞክረው ‘የገበያ አክራሪነትን” ናፋቂ ቡድን፤ ሀገራት ከሌሎች ጋር ስለሚኖራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ወሳኝ ሊሆን አይችልም። የሀገራት ግንኙነት በአንድ ራሱን “ለትርፍ ያልተቋቋምኩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነኝ” በሚል የሐሰት ድረታ እንደማይገታ አክራሪው ቡድን ራሱ እያወቀ፤ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያወጣውና ‘የአውሮፓ ህብረት ለምን ከኢትዮጵያ ጋር አብሬ እሰራለሁ ይላል’ በማለት የርዕዮተ-ዓለም ጣጣውን በሀገራችን ላይ ለመጫን መሞከሩ ቡድኑ ምን ያህል የሀገራችን ጠላት መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት “ሄልሲንኪ ዎች” በሚል ስያሜ በያኔዋ ሶቭየት ህብረት ይመራ የነበረውን የሶሻሊዝምን ጎራ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለማዳከም የተቋቋመው ፅንፈኛው ቡድን፤ ዛሬ ላይ ደግሞ “ለሰብዓዊ መብት እሟገታለሁ” በሚል በአዲስ መለያ የአክራሪ ኒዮ-ሊበራሊዝምን ቀኖና ለብሶ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህም በራሳቸው መንገድ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስም በመወንጀልና በየሳምንቱ መግለጫ እንዲያወጣ በእነ ጆርጅ ሶሮስ “የቤት ስራ” ተሰጥሮት የሚሰራ የርዕዩተ-ዓለም ትርፍ አጋባሽ ቡድን ነው።

ታዲያ “ለቤት ስራው” የሚሆንም እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ከዲታው ሶሮስ እየተቀበለ እንደ ‘ሲፒጄ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ አርቲክል 19፣ ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ፣…ወዘተ.’ ከመሳሰሉ “የትግል አጋሮቹ” ጋር በመሆን የአክራሪ ኒዮ-ሊበራል ርዕየተ-ዓለምን ለማስፋፋት ይጥራል—በቅብብሎሽ የመግለጫ ጋጋታ በማውጣት። ‘ከኒዮ-ሊበራሊዝም ውጭ ሌሎች የዕድገት መንገዶች አያዋጡም’ የሚል ያረጀና የፈጀ ትረካን ያስደምጣል። ይህን በቅብብሎሽና በተጠና መንገድ የሚካሄድ ትረካን የማይቀበሉና ‘በራሳችን ተጨባጭ ሁኔታ እናድጋለን’ ብለው በሚሞግቱ ሀገሮች ላይ ከቻለ የእርሱን ርዕዩተ-ዓለም የሚከተሉ ‘ተላላኪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን’ ያደራጃል።

እነዚህን “በውስጥ አርበኝነት” ያደራጃቸውን “ተቃዋሚዎች” በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት እንዲገለብጡ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል። ለዚህም ከውጭ ሆኖ የቀለም አብዩት እንዲካሄድ በሀገር ውስጥ ላለው ተቃዋሚ ፓርቲ ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል። ይህ እኩይ ምግባሩ ከሰመረለት በእነዚህ “ተቃዋሚዎች” አማካኝነት በሚመሰረተው አዲስ መንግስት የዚያች ሀገርን አንጡራ ሃብት ላይ እንደ ጆርጅ ሶሮስ ዓይነት ዲታዎች እንዳሻቸው እንዲፈነጩና ሃብቱን ዘርፈው ወደ ሀገራቸው እንዲጭኑ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ያስዘርፋል። ከትርፉም በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዶላሮችን ይወስዳል። ሆኖም ይህ “የእንዝረፋቸው” መንገዱ በዚያች ሀገር ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሳቢያ ካልተሳካና ከከሸፈ፣ ያቺ ሀገር ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሻክርና እንዲበላሽ እንዲሁም ከሀገራቱ የተለያዩ ድጋፎችን ሀገሪቱ እንዳታገኝና ፊቷን ወደ አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች እንድትመልስ ለማድረግ “ከአምሳያዎቹ” ጋር በመነጋጋር የሐሰት መግለጫ ጋጋታ በማውጣት የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፍታል። ይህ “የአልሸነፍም” ተግባሩም በእልህ የሚካሄድ በመሆኑም፤ ያለ አንዳች ሀፍረት ዓይኑን በጨው ታጥቦ ‘ለምን እገሌ ከሚባል ሀገር ጋር አብራችሁ ትሰራላችሁ’ በማለት መመሪያ ለመስጠት ጭምር ይዳዳዋል። የአውሮፓ ህብረት ከሀገራችን ጋር በሁሉም መስኮች ተባብሮ ለመስራት ያለውን ፍላጎት ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኝቶ ሲገልፅ፤ ተንገብግቦ በማግስቱ አስቂኝ መግለጫ ያወጣውም ለዚሁ ይመስለኛል።

ይህ ሰብዓዊ መብትን የማያውቀው “የሰብዓዊ መብት ተሟጋች” ለይስሙላ በዚህ መብት ስም እየተንቀሳቀሰ፤ የህዝቦችን ሰብዓዊ መብት በጠራራ ፀሐይ ለመንጠቅ ያሰፈፈ ቡድን ነው። እንዲያውም በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም በመጋፋት ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውንም ለመደፍጠጥ ይጥራል። የአንድ ሀገር ህዝብ ከሌሎች ሀገራት ወይም አህጉራት ጋር የሚገናኝበት የራሱ የውጭ ጉዳይ መርሆዎች አሉት። የአውሮፓ ህብረትም ከማን ጋር በምን ዓይነት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንደሚያደርግ ራሱ የሚከተለው አቅጣጫ አለው። ይህን አቅጣጫቸውን እንደ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ዓይነት የርዕዩተ-ዓለም ሲራራ ነጋዴዎች ሊወስኑት ወይም ሊገድቡት አይችሉም።

እንደ እውነቱ ከሆነ አውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የአባል ሀገራቱን ፍላጎት ተመርኩዞ እንጂ፤ እነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ደስ እንዲላቸው አይደለም። አውሮፓ ህብረት ለአባል ሀገራቱ ፍላጎት ካልሆነ በስተቀር ለአክራሪ ቡድኖች ንግድ ቦታ የሚሰጥ አይመስለኝም። ህብረቱ የሚያዋጣውንና የማያዋጣውን የሚያውቀው እርሱ እንጂ ፅንፈኛው የርዕዩተ-ዓለም አራማጁ ቡድን ሊሆን አይችልም። አክራሪው ቡድን “የእኛ እናውቅላችኋለን” ዲስኩሩን እንደለመደው በአውሮፓ ህብረት ላይ ማራመድ የሚፈልግ ከሆነ፤ በእርግጠኝነት መረዳት ያለበት እያንኳኳ ያለው የተሳሳተ በር መሆኑን ነው።

የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝብም ይህ የተሳሳተ በር አንኳኪ አክራሪ ቡድን ‘ሰብዓዊ መብትን እየጣሱ ነው’ በማለት በሚያካሂድባቸው የፈጠራ መግለጫዎች ከጀመሩት የልማት ጉዞ የማይናጠቡ መሆናቸውን ማወቅ አለበት። እኛ ኢትዮጵያን የሚበጀንና የማይበጀንን ማንኛውም የውጭ ሃይል የሚነግረን አይደለንም። የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ለአክራሪ ኒዮ-ሊበራል ኣልፈን አንሰጥም። እንቅጭ እንቅጩን እንነጋገር ከተባለ፤ ለእኛ የሚሆነን ፖለቲካል-ኢኮኖሚ መንገድ የሚመርጡልን እነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ሊሆኑ አይችሉም። አይገባምም። “ከእኛ ወዲያ ለእናንተ የሚያውቅላችሁ የለም” የሚለው የእነዚህ ሰብዓዊ መብትን የማያውቁ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች” አስተሳሰብ፤ ያኔ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ምዕራባዊያን አፍሪካን ሲቀራመቷት በነረበው የአስተሳሰብ ደረጃ ያበቃ ነው። በእኔ እምነት እነዚህ ሃይሎች ያኔ ከአፍሪካ አጋብሰው ለምጣኔ ሃብት ዕድገታቸው መመንደግ ምክንያት የሆናቸው የተፈጥሮ ሃብትና ርካሽ የሰው ሃይል ጉልበት አህገሪቱ ዓይኗን ባልገለጠችበት ወቅት የተከናወነ በመሆኑ፤ ከዛሬ 72 ዓመት በፊት የቀረን ያን አሮጌ እሳቤ አንግቦ በአዲስ መንፈስ እየተመራች ያለችውን አፍሪካን ዳግም ለማስገበር መሞከር ከዘመኑ ጋር አለመዘመን ይመስለኛል።

ይህን አሮጌ መንፈስን በቅኝ ግዛት ስር ወድቃ በማታውቀውና ማንነቷን “እኛ እናውቅልሃለን” ለሚሉ የውጭ ሃይሎች ፊት ባልሰጠችው ኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር መመከሩ ደግሞ እጅግ ድፍረት ይመስለኛል። አዲሲቷ ኢትዮጵያም ብትሆን ህዝቦቿን በአስተማማኝ የሰላምየልማትና የዴሞክራሲ መንገድ እየተመመች ነው። ለራሷ የሚሆናትን ትክክለኛ መስመር በመያዝም ዛሬ የአፍሪካዊያን የዕድገት ተምሳሌትና ኩራት መሆን ችላለች። ይህን ደግሞ የዛሬዎቹ ምዕራባዊያን ጠንቅቀው ያውቃሉ።

ምን ይህ ብቻ። ኢትዮጵያ አሁን በጀመረችው የሁለንተናዊ ዕድገት ጎዳና ላይ ጥቂት ዓመቶችን መራመድ ከቻለች ነገ ሌሎች የበለፀጉ ሀገሮች የደረሱበት ደረጃ እንደምትደርስ ያምናሉ። በተለይም ሀገራችን ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ ብሎም በአፍሪካ የሰላም ማስጠበቅ ተልዕኮ የምትጫወተውን ሚና ይረዳሉ። ይህ ሚናዋም በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን የአፍሪካ ብሎም የዓለም ድምፅ ሆና እየሰራች መሆኗን ይገነዘባሉ። የተከተለችው የዕድገት መስመርም ሌሎችን የማይጎዳና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የአረንጓዴ ልማትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ይረዳሉ። ይህም ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም በምሳሌነት መቅረብ የሚችል መሆኑን ከእነርሱ በላይየሚያውቅ የለም። ሀገራችን አፍሪካዊያን ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድና ያላትን በማካፈል ችግሩ እንዳይባባስ እያደረገች መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ራሳቸው እማኝነታቸውን ሲሰጡ ነበር። ታዲያ ከዚህች የዕድገት ተምሳሌት፣ የአፍሪካዊያን መከታና ድምፅ እንዲሁም በመርህ ብቻ ከምትመራ ሀገር ጋር አብሮ የማይሰራ ማነው?—በእኔ እምነት የርዕዩተ-ዓለም ነጋዴዎች ከሆኑት ከእነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” በስተቀር ማንም የሚኖር አይመስለኝም። ለዚህም ነው— የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር በበርካታ መስኮች አብሮ ለመስራት ፍላጎት ያለው መሆኑን ለመግለፅ አዲስ አበባ ድረስ የተገኘው።

“ሂዩማን ራይትስ ዎች” ግን ይህን የህብረቱን ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ የሚከናወን በትብብር የመስራት መንፈስን በመቃወም በየሳምንቱ የወረቀት መግለጫ ያትማል። ልፋ ያለው የርዕዩተ-ዓለም ነጋዴ ነውና ዛሬም ባረጀው “እኛ እናውቅላችኋላን” አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት ሲመጡ እንዲሁም ካደግን ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ህዝቦች አርአያና መጠለያ እንደምንሆን የሚያምኑትን እንደ አውሮፓ ህብረት ዓይነት ትላልቅ ጥምረቶችን ይከሳል፤ ይወነጅላል። ግን አይሳካለትም።

የኢትዮጵያ መንግስትን በይፋ በመክሰስ የሚታወቁትና የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል የሆኑትን እሜቴ አና ጎሜዝን ጭምር በመጠቀም ብዙ ቢለፋም ሰሚና አድማጭ አላገኘም። ነገም ከምግባሩ ጋር የማይገናኘውን “የሰብዓዊ መብት ተጣሰ” ዲስኩሩን ይዞ ብቅ ሉል ቢችልም እንደ ትናንቱና እንደ ዛሬው ከቁብ የሚቆጥረው የለም። እናም በሰብዓዊ መብት ስም የሀገራችንን ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመቀማት የቋመጠው አክራሪው ኒዮ-ሊበራል ድርጅት ሰሚ ጆሮ ካለው፣ በምግባሩ ራሱ ሊያፍር የሚገባ ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ ግን ኢትዮጵያዊያን በወሬ ጋጋታ ከጀመርነው የህዳሴ ጉዞ ለሰከንድ እንኳን ልንናጠብ የማንችል መሆኑን ቢገነዘብ፤ የእውነተኛውን ሰብዓዊ መብት ምንነት በሚገባ የተገነዘበ ያህል ልንቆጥርለት እንችላለን።       

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy