Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስብሰባ ላይ ናቸው

0 1,187

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስለስብሰባ ምንነት በመግለጽ ጊዜያችሁን አላባ ክንም። በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለያየ አቀራረብም ቢሆን ብዙ ከተፃፈባቸው ጉዳዮች አንዱ ስብሰባ ነው፡፡ቅርብ ወዳገኘሁት ቤተመፃህፍት ገብቼ ሳገላብጥ ስብሰባ ምንድን ነው? በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የነሐሴ 16 ቀን 2006.ም እትም ላይ ሰፍሮ ተመልክቼያለሁ እዚያ ላይ ታገኙታላችሁ ለማለት ነው በዓመተ ምህረት እየተለዩ ተጠርዘው በየዩኒቨርሲቲው በየቤተ መጻሕፍቱና መልካም የዶክመንቴሽን ሥርዓት ባላቸው መስሪያ ቤቶች ይገኛሉ። ስብሰባ በመሰረቱ መልካም ነው፣ክፋት የለውም የራሱ ችግሮች ቢኖሩትም መጥፎ ተብሎ የሚወገዝ ሂደት አይደለም፡፡ ስብሰባን መጥፎ የሚያደርጉት በዋነኛነት ሰብሳቢዎቹ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ስብሰባ ለዛውን ክብሩንና ጥቅሙንም እያጣ መጥቷል፡፡ በተለይ የዘንድሮው ስብሰባ በህዝብ አፍ እንኳንስ ሊነሳ ቀርቶ ስሙን ለመጥራት የሚያስጠ ይፍበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በየዕለቱ ከሚደጋገሙ ቃሎች ለምሳሌ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ብልሹ አሰራር ….ሙስና … ኪራይ ሰብሳቢነት …ድህነት … ወዘተ ልማት መካከል «ስብሰባ እንደሚ ባለው ቃል የሚያስጠላ ነገር የለም፡፡መብራት ቢሄድ ይጠፋና በራሱ ጊዜ ይመጣል፡፡ መበሳጨትና ውኃና ፍሳሽ ድረስ የሚወስደን ጉዳይ የለም፡፡የመብራትና የውኃ ችግር ሲያጋጥም የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች አስቀድመው ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ፡፡ በዚህ በዚህ ሰፈር ከዚህ ቀን ጀምሮ እስከ ቀን ድረስ በ—- ምክንያት ውኃ የሚቋረጥ መሆኑን ይነግሩናል፡፡ ስብሰባ ውስጥ ይሄ የለም፡፡ ሌሎች ሥራዎቻችን ሁሉ ትተን ንግዳችንን ዘግተን …. ጊዜያችንን አቃጥለን የመጓጓዣ ወጪ አውጥተን ወረዳና ክፍለ ከተማ ድረስ ሄደን ብዙ ከደከምን በኋላ እዚያ ስንደርስ «ስብሰባ ላይ ናቸው» እንባላለን፡፡ በእነሱ ስብሰባ ምክንያት የእኛ ጉዳይ ሳይፈፀም ቢያንስ ለሳምንት ይጓተታል፡፡ ረቡዕና ዓርብ ከሆነ ጉዳያችን የሚታየው እነሱ /ፈጻሚዎቹ/ ስብሰባ ላይ ከሆኑ ጉዳያችንን ይዘን የምንመጣው በቀጣዩ ሣምንት ረቡዕና ዓርብ ነው ያበሳጫል፣ያማርራል፡፡

የሕዝቡን ስሜት ተረድቻለሁ፡፡ በተለያዩ ወረዳዎች ተዟዙሬም ተመልክቸዋለሁ፡፡ ሕዝቡ ከሥራ ቃላት መካከል «ስብሰባ ላይ ናቸው እንደሚለው መግለጫ የተማረረበት ነገር የለም፡፡ስብሰባ በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ጭራቅ መስሎ ተቀርጿል የሚያስገኘው ጥቅም የለም ካለም ጥንቅር ብሎ ይቅር የሚለው ሰው በዝቷል እንዲያውም ህዝባዊ ተቃውሞ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ ከሚባሉ ቀደምት ሁኔታዎች ውስጥ ዋናው ስብሰባ ነው፡፡ በስብሰባ የተማረረው አገልግሎት ፈላጊው ህዝብ ብቻ አይደለም፡፡ በዋነኛነት የተማረረው ተሰብሳቢው ፈፃሚ ነው፡፡ እኔ የማውቃቸው ሰራተኞች በሙሉ ተደዋውለን «ጠፋህ ጠፋህ» ስንባባል የመጀመሪያ ምክንያታቸው ስብሰባ ነው፡፡ «ምን እዚህ ስብሰባ እያሉ …የሚለው ይበዛል፡፡ ስብሰባን የሚወድ የለም አበል የሌለው ከሆነማ የሚገኝለት ሰው የለም ፡፡ አበሉም ቢሆን ብዙ ደጋፊ የለውም ፡፡ በጥናት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በዚህ ከቀጠለ ስብሰባ እንደ አገር ፀር የሚቆጠር ታላቅ በሽታ ይሆንና አስፈላጊነቱና ጠቃሚነቱ ቅቡልነቱን ያጣል፡፡ ስለዚህ ለጥቅሙና ለአስፈላጊነቱ ስንል ስብሰባን መታገል አለብን፡፡

ለዚህም ሁለት ጥያቄዎችን ማስታረቅ አለብን፡፡ በአንድ በኩል ስብሰባ ይጠቅማል ወይ? የሚለው ሲሆን መልሱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ አዎ እጅግ በጣም ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ ሌላው ጥያቄ ደግሞ «ስብሰባ ሥራን /የአገልግሎት አሰጣጥን ያስተጓጉላል ወይ የሚለው ነው። የዚህም መልሱ ግልጽ ነው «አዎ እጅግ በጣም ያስተጓጉላል» አነሳሳችን እነዚህን ሁለት አቅጣጫዎች አስማምተን ማስቀጠል ነው፡፡ ስብሰባውም ሳይቀር… ሥራም ሳይበደል(አገልግሎት ሳይቋረጥ) ሁለቱንም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ (ዘዴ) ጥቅም ላይ ማዋል አለብን፡፡ ለዚህ የሚረዱ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማፍለቅ አለብን፡፡ ተሰብሳቢው ሣይማረር አገልግሎት ፈላጊውም ሳይጉላላ የስብሰባው ባቡር የሚሄድበትን ሃዲድ መዘርጋት አለብን፡፡

መታየት ካለባቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱና ዋናው ስብሰባው መቼ ይካሄድ የሚለው ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጡ እንዳይቋረጥ ሲባል ስብሰባውን ከሥራ ሰዓት ውጭ ማለት ከ11 ሰዓት በኋላ ወይም ቅዳሜና እሁድ ማድረግ ይቻላል? ቢቻልስ (በአስገዳጁ የበላይ ትዕዛዝ) ይደረግ ቢባል ፍትሃዊ ይሆናል? አይሆንም? ስብሰባው ዓላማ አለው ሰራተኛው እስከ 11 ሰዓት በሥራ ሲደክም ውሎ ከዚያ በኋላ ቢሰበስቡት በደከመ ሰውነትና በዛለ አእምሮ የሚፈለገውን ዓላማ ማሳካት አይቻልም፡፡ ሃሳቡም ሌላ ቦታ ነው የሚሆነው ልጆቹን ከትምህርት ቤት ማውጣት አለበት፡፡ የማታ ትምህርቱን መከታተል ሊያስፈልገው ይችላል ትራንስፖርት ለማግኘት መሽቀዳደም አለበት፤ ለዕለት ፍጆታ የሚያስፈልጉ ሸመታዎችን ገዛገዛ አድርጎ ቋጥሮ መግባት አለበት። ከጓደኞቹና ከዘመዶቹ ጋር ሻይ ቡና እያለ የሚያሳልፈው ጊዜ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህን እያሰበ ስብሰባ ቢጠሩት በአካል ከመገኘት ባለፈ ለአእምሮውና ለወደፊት ሥራው ስንቅ የሚሆን ጠብታ ቁም ነገር ይዞ አይወጣም፡፡ የስብሰባው ዓላማ አልተሳካም ማለት ነው፡፡ ቅዳሜና እሁድ ይሰብሰቡ ማለትም ህገወጥነት ነው፡፡ አዋጅ አለ ማንኛውም ሰራተኛ በሳምንት ውስጥ ያልተቆራረጠ የ24 ሰዓት እረፍት የማግኘት መብት አለው፡፡ ሊከበርለት ይገባል፡፡

ስለዚህ ቅዳሜና እሁድ ወይም በካላንደር ዝግ በሆነ በዓላት መሰብሰብ የለም፡፡ የራሱን ህይወት ከቤተሰቡ ጋር ለመኖር ያለው መብት መረጋገጥ አለበት፡፡ የእረፍት ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ ካላሳለፈ በቀጣዩ ሳምንት ውጤታማ ሥራ ወይም ትርፋማ ምርት ሊያስገኝ አይችልም፡፡ ስብሰባ ጨዋታ አይደለም፡፡ የትርፍ ሰዓት ሥራም አይደለም፡፡ ራሱን የቻለ የሥራ አካል ነው፡፡ ስለዚህ ስብሰባ መደረግ ያለበት በሥራ ሰዓት ነው፡፡ አለቀደቀቀ

ስብሰባው እንዴት ይካሄድ? የሚለው መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ሰራተኛው በሙሉ አንድ ላይ ይግባ ወይም በሺፍት (በተራ) ይግባ ሁለቱም የየራሳቸው ጉዳት አላቸው፡፡ ሁሉም በአንድ ይግባ ቢባል አገልግሎት የሚሰጥ ይጠፋል ማለት ነው፤ ህዝብ ይጉላላል፤ ይማረራል ማለት ነው፡፡ ስብሰባው በሺፍት ይደረግ ቢባል ማለት ወታደሮች «አንድ እግር በመሬት» በሚሉት ዘዴ ግማሹ አገልግሎት እየሰጠ የተቀረው የሚሰበሰብበት አሰራር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የስብሰባውን ቆይታ ያራዝመዋል፡፡ አንድ ሳምንት የሚበቃው ስብሰባ በሺፍት ሲሆን ሁለት ሳምንት ይፈጃል። ከዚህም በላይ ለእያንዳንዱ የሥራ መደብ የሚቀጠረው ሠራተኛ ከነተጠባባቂው አይደለም፡፡ ለሁሉም የሥራ መደብ ሁለት ሁለት ሰራተኛ አይቀጠርም፡፡ የሰው ብዛት እንደ ሥራው ዓይነትና ስፋት የሚወሰን ነው፡፡

ስብሰባው የሚፈጀው ጊዜ (ቀን) መጠን መነሳት ካለባቸው ጥያቄዎች አንዱ ነው፡፡ አንድ ቀን.. ሶስት ቀን… ሳምንት.. ወዘተ ስንት ቀን መፍጀት አለበት? በኛ ልምድ አምስት ቀን ነው፡፡ ለስብሰባው ሲባል የአገልግሎት አሰጣጡ ለስንት ቀን ይቋረጥ? ለስብሰባ መራዘም ሰበብ የሚሆኑ ጉዳዮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሰበብ የአጀንዳው ክብደትና ብዛት ነው፡፡ ስለምንድነው የሚነጋገሩት፣ ከባድ ጉዳይ ነው ቀናትን የሚጠይቅ አጀንዳ ነው? ብዛቱስ በስንት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው የሚነጋገሩት? ለእያንዳንዱ ጉዳይ /አጀንዳ / የተያዘለት ጊዜ ስንት ነው? አመራሩ ይሄን በቅድሚያ አስቦ መዘጋጀት አለበት ፡፡ «ሳንጫጫው እውላለሁ» በሚል ደንታ ቢስነት ወደ ስብሰባ መግባት ፀረህዝብነት ነው፡፡ ሌላው የስብሰባ መራዘም ሰበብ ተሰብሳቢው ራሱ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ካልተናገርኩ ባይ ይሆናል፡፡ ሌላው ሰው የተናገረውን ሳይሰማ እሱ የሚናገረውን ብቻ ሲያስብ ይቆይና ጣቱን ይቀስራል፡፡ ሲፈቀድለት ያንኑ የፊተኞቹ የተናገሩትን ኮፒ ፔስት ያደርጋል፡፡ አዲስ ሃሳብ ወይም ተጨማሪ ነገር የለውም፡፡ «ተናገረ» ለመባል ብቻ የሚናገር አለ፡፡ የፖለቲካ አቋሙን ለማንፀባረቅና ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንደሚሉት ለድርጅቱ ያለውን ታማኝነት ለማሳየት የሚፍጨረ ጨርም አለ፡፡ ይሄ ሁሉ ጊዜ ቆርጣሚ ሂደት ነው

የስብሰባው መሪዎች እውቀትና የስብሰባ አመራር ብቃት ማነስ ለስብሰባው መራዘም ሌላው ሰበብ ነው፡፡አብዛኞቹ ሰብሳቢዎች ከተሰብሳቢው የባሱ ናቸው፡፡የተነሱ ነጥቦችን እያሰባሰቡ በማደራጀትና አዲስ ሃሳቦችን ብቻ በመቀበልና ሌላ የግልና የፖለቲካ አቋም መግለጫ ንግግሮችን በማቋረጥ ወይም በማሳጠር የስብሰባውን ሂደት ወደፊት ማራመድ አይችሉም፡፡ ሰብሳቢዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች /አስተያየቶች/ መልስ መስጠት ከጀመሩ ዙሪያ ጥምጥም ይዞራሉ ከሚገባቸው የአየር ሰዓት በላይ ይፈጃሉ፡፡ በቀጥታ በጉዳዩ ላይ ብቻ የማተኮር ልምድ የላቸውም፡፡ ስብሰባው ለነገ ያድራል፡፡ ህዝቡም ይማረራል፡፡መታረም አለበት፡፡ መሰረታዊ የስብሰባ አመራር ጥበብ የሚማሩበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ ሊደርሺፕ አካዳሚ… ሌሎችም የፓርቲ ፖለቲካ ተቋማት የስብሰባ አመራር ርዕሰ ጉዳይን በጥልቀት የሚያስጨብጡበት ሥርዓተ ትምህርት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

የስብሰባዎች ተከታታይነት ማለትም አንዱ ስብሰባ ሲያልቅ እሱን በተመለከተ ሌላ ስብሰባ የማካሄድ አሠራር ለስብሰባ መራዘም ሌላው ሰበብ ነው፡፡ ለምሳሌ የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ወርቅ ሆኖ ሳለ በተሃድሶው ውጤት ላይ ተመስርቶ የስልጠና መድረክ ይዘጋጃል፡፡ ያው ስብሰባ ነው፡፡ በዚህ አያበቃም፣ ተሃድሶውና ስልጠናው ወደ መሬት ሲወርድ ያስገኘውን ለውጥ ለመለካት ከተገልጋዩ ጋር ስብሰባ ይካሄዳል፡፡ ህዝቡ ያነሳቸውን ችግሮች ወደ ፈፃሚዎች ለማውረድና የአሰራር ብቃትን ለማሳደግ ስብሰባ አይቀርም፡፡ የስብሰባ ሰንሰለት/ Chain / መብዛት አገልግሎት ሰጪ ኃይሉን ወጥሮ ስለሚይዘው የአገልግሎት ፈላጊውን ህዝብ ጥያቄ በተግባር ለመመለስ አያስችለውም፡፡ እነዚህ ከፍ ባለ ሁኔታ የሚካሄዱ ስብሰባዎች ሲሆኑ በየሥራ ዘርፉ የሚካሄዱ ሌሎች ስብሰባዎችም አሉ፡፡ ሰኞ ጠርናፊው /የአንድ ለአምስት አስተባባሪው / ይሰበስባል ማክሰኞ ዳይሬክተሩ፣ ረቡዕ ምክትሉ፣ ሐሙስ ዋናው ወዘተ ሁሉም በየፊናው ይሰበስባል፡፡ እነዚህ በአብዛኛው ከግማሽ ቀን የበለጠ ጊዜ አይወስዱም ሥራን ለማስተጓጎል ግን ጉዳታቸው ቀላል አይደለም፡፡

ስብሰባ ለይስሙላ የሚዘጋጅ አይደለም፡፡ ስብሰባ የሚያስፈልግበት በቂ ምክንያቶች አሉት፡፡ ለስብሰባ መብዛት ዋናው ምክንያት በየደረጃው ያሉ ፈፃሚዎች ብቃት ማነስ ነው፡፡ የአገልግሎት ፈላጊው ፍላጎት በአብዛኛው የማይመለሰው በፈፃሚዎችና በአስፈጻሚዎች ድክመት ነው፡፡ ብቃት የሌላቸው ይበዛሉ፡፡ በቅጥር ጊዜና ሂደት ላይ ጥንቃቄ አይደረግም፡፡ የቃልና የወረቀት ፈተናው ጠንካራ አይደለም፡፡ በንፁህ ህሊና ውጤቱ መታረሙን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ከብቃት ይልቅ ፖለቲካ ይበዛበታል፡፡ በብቃት ማነስ ምክንያት አገልግሎት ፈላጊው ፈጣንና ፍትሃዊ መፍትሄ አያገኝም፡፡ ብሶቱን ላገኘው ሚዲያ ሁሉ በምሬት እየገለፀ እገዛቸውን ይጠይቃል፡፡ ይህ የህዝብ ብሶት ቆይቶም ቢሆን የመንግሥት ጆሮ ያገኛል፡፡ ምን እንደሚሻል ይመክራል ከዚያም በፈፃሚና በአገልግሎት ፈላጊ ሥራ ውስጥ ያሉትን ተዋንያን በየደረጃው ይሰበስባል፡፡ የብቃት ማነስ በበዛበት ቦታ ሁሉ ስብሰባ ይበዛል፡፡ የስብሰባን መንዛዛት ለመግታትና ከስብሰባ የሚገኘውን ትሩፋት በትክክል ለመጠቀም የሰራተኛውን የሙያ ብቃት ማሳደግ ወሳኝ ነው፡፡ ስብሰባ ላይ ሳይሆን ስልጠና ላይ ትኩረት ማብዛት ያስፈልጋል፡፡ ማለትም ፈጻሚው በመንግሥት ሰራተኛነቱ ዛሬ ሲሰበሰብ ነገ ደግሞ በፓርቲ ስብሰባ የሚወጠርበት ሁኔታ ካለ በሥራው ላይ ጫና በማይፈጥርና ተገልጋዩን በማያማርር መንገድ ሚዛናዊ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

የስብሰባን ብዛትና መደራረብ ለመቀነስ ሌሎች ዘዴዎችን መፈለግም አንዱ ኃላፊነታችን ሊሆን ይችላል፡፡ ስብሰባ በይዘቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ ነው፡፡ ዓላማው በሥራዎች ላይ ያሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለመለየትና መፍትሄ አስቀምጦ ወደፊት ለመቀጠል የሚያስችል የእርስ በርስ ግንኙነት ሥራ ነው፡፡ ይህን የግንኙነት ተግባር ለመጠቀም ሌሎች ዘዴዎች አሉ፡፡ በሥራ ኃላፊዎች አማካይነት በሣምንት አንዴ የሚሰጥ መግለጫ ማዘጋጀት አንዱ ነው፡፡ ለኃላፊዎች ብቻ አቅጣጫ ማስጨበጫ አጭር ስብሰባ ማድረግና የተቀረው ሰራተኛ ሥራውን እንዲሰራ ማድረግ ሌላው ዘዴ ነው፡፡ በራሪ ወረቀቶችን ብሮሸሮችን… ማኑዋሎችን አዘጋጅቶ ማሰራጨት አንዱ አካሄድ ሊሆን ይችላል፡፡

ዓላማችን የግንኙነት /ኮሙኒኬሽን / ሥራችን ሣይቋረጥና «ስብሰባ ላይ ናቸው» የሚባል ቅዠትም ሣይደመጥ ሁለቱን አግባብተን ወደ ልማት ግባችን ለመገስገስ ነው፡፡ ግርማ ለማ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy