የኤርትራ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍንና መረጋጋት እንዳይኖር አጥብቆ ይሰራል። ይህን እውነታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር ያረጋገጠው ነው። ሥርዓቱ በሀገሪቱ ውስጥ ደግሞ የዜጎቹን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አፍኖ ኤርትራውያንን ለስደት እየዳረገ ነው። ኤርትራውያን በሀገራቸው መኖር አቅቷቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ሀገር ጥለው ስደትን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገዋል። እነዚህ ህዝቦች በዋናነት የሚፈልሱት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን ነው። ፈረንጆቹ የኤርትራውያንን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ስደት መጉረፍ ለሥርዓቱ ያላቸው የጥላቻ/ተቃውሞ ድምፅ በስደት/ሃገር ጥሎ በመውጣት እየገለፁ (voting by foot )መሆናቸውን የሚሳይ ነው ይሉታል።
በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ወደ ሀገራችን እየተሰደዱ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ ከ150 እስከ 200 የሚደርስ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ ወደ አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ደግሞ ወታደሮች መሆናቸው በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአቀረቡት ሪፖርት አረጋግጠዋል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ሁኔታው እየከፋና እየተባባሰ መሆኑን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ግን ለወንድምና እህት ህዝቦች የሚያደርገውን አቀባበል በነበረው በወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በተቃራኒው የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስና ከፀረ ኢትዮጵያ አካላት በሚሰበስበው ፍርፋሪ በመጠቀም አሰልጥኖና አስታጥቆ እየላከ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጄሌዎቹ በአካባቢው ሕዝብና ሚሊሻ እንዲሁም በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ተመልሶ ነጋሪ ሳይቀር እየተደመሰሱና እየተያዙ መሆኑ ቢታወቅም ።
የኤርትራ ህዝብ ለነፃነት፣ ለፍትህና፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለብልፅግና ሰላም ለ30 ዓመታት የትጥቅ ትግል አካሂዷል። በዚህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን መስዋአትነት ከፍሏል። አካል ጎድሏል። የኤርትራ አባቶችና እናቶች ያለ ጧሪ ቀርተዋል። የኤርትራ ኢኮኖሚም እሳት በልቶታል። ለዚህም ነው አንዳንድ ተንታኞች የተገኘው ነፃነት «የባንዲራ ነፃነት» ብቻ ሆኖ ቀርቷል እስከማለት የደረሱት።
የኤርትራ ህዝብ ለሶስት አስርት ዓመታት የዘለቀ መስዋእትነት የከፈለበት ዴሞክራሲ ፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ብልፅግና ፣ ልማትና ሰላም የውሃ ሽታ ሆነዋል። የኤርትራውያን ስቃይና ሰቆቃ መልኩን ቀይሮ ቀጥሏል። እንዳውም አብዛኞቹ ኤርትራውያን የኢሳያስ ሥርዓትን «ትግርኛ ተናጋሪ ደርግ» ብለው እስከ መጥራት ደርሰዋል። ምክንያቱም የኤርትራ እናቶችና አባቶች እንባ ዛሬም በባሰ መልኩ መፍሰሱን ቀጥሏልና ነው። ከዚያም አልፎ ሥርዓቱ ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር በፈጠረው ግጭትም ለስጋት እንደተጋለጡ ናቸው፡፡
የኢሳይያስ ሥርዓት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለብቻው በመቆጣጠር አንድ ሳንቲምም ሳትቀር በህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትህ (ህግደፍ) መዋቅር እንድትገባ በማድረግ የኤርትራ ህዝብን ከኢኮኖሚ እድገት ባይተዋር አድርጓታል። ሰላም እንዲያጣ እና በቀየው ተረጋግቶ እንዳይኖር አድርጎታል። ለዓመታት በቀጠለ ሁኔታ ወጣቶች ትምህርታቸውን ትተው ለ18 ወራት ተብሎ ነገር ግን ገደቡ የማይታወቅ የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረጉ የሀገሪቱን አምራች ዜጋ ከጥቅም ውጪ ያደረግ ሥርዓት ነው። እነዚህ ወጣቶች በብሄራዊ አገልግሎት ስም የሥርዓቱ ከፍተኛ ጀኔራሎችን የአትክልት ማሳዎች ኰትኳችና ተንከባካቢዎች በአጠቃላይ የህግደፍ ባለስልጣናት አገልጋይ ሆነዋል። ስለሆነም በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ምክንያት ኤርትራውያን ሀገራቸውን ጥለው ስደትን የሙጥኝ ቢሉም የሚደንቅ አልሆነም። በዚህ የስደት ሂደትም ከፍተኛ አደጋ እየደረሰባቸው መሆኑንም በየበረሃውና በሜድትራንያን ባህር የሚያልፈውን ህይወት በማየት መረዳት ይቻላል።
የኤርትራ አርሶ አደር ሳይቀር ሀገሩንና ማሳውን ትቶ ስደት እየወጣ መሆኑ የሥርዓቱ ክፋትና ግፍ ከአፍ እስከ ገደፉ መሙላቱ ማሳያ ነው። በአለፉት 26 ዓመታት ያልተማረ፣ሀገሩን የሚጠላና ተስፋ የቆረጠ ትውልድ በኤርትራ ተፈጥሯል። ይህ አካሄድም የሥርዓቱ ክስረትና የአደገኛ ውድቀት ማሳያ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለው የኤርትራ መንግስትም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በወጣትና አምራች ሃይል ማንቀሳቀስ ስለማይችል ከፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች በሚያገኘው ድጋፍ ክፍለ አህጉሩንና ኢትዮጵያን ማተራመስ ዋና የእለት ተእለት ስራ አድርጎት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህ ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴው ደግሞ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለክፍለ አህጉሩ ቢሆን እጅግ አደገኛ መሆኑን ለማንም ግልፅ ነው።
የኤርትራ መንግስት የቁልቁለት ጉዞውን በፍጥበነት የጀመረው ከ15 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሞ በደረሰበት ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ ነው። ከውድቀት መማር የሚችል ሥርዓት ቢሆን ኖሮ ያ ኪሳራ ከደረሰበት በኋላ የተሳሳተ መንገዱን አስተካክሎ ለሰላምና ለጋራ ጥቅም ሊሰራ የሚችልበት መልካም አጋጣሚ ነበር። ምክንያቱም ከጦርነትና ግጭት ምንም አይነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ማግኘት እንደማይችል በቂ ትምህርት የሰጠ በመሆኑ ነው። ነገር ግን ለመማር ዝግጁ ያልሆነው ሥርዓት ዛሬም በጥፋት መንገዱ ቀጥሎበታል። ይህ መንገድ ለጊዜው የጠቀመው ቢመስለውም ሄዶ ሄዶ ሞቱን የሚያፋጥን መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም። በአንድም በሌላም የሥርዓቱ የማብቂያ ምእራፎች እየታዩ የመሰሉትም ለዚሁ ነው ፡፡
አሁንም የኢሳያሰ መንግስት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። በወደብ ኪራይ ሰበብም ይሁን በሌላ መንገድ የሚያገኘውን ገንዘብ ለእኩይ ዓላማ እያዋለው እንደሆነም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መረጃዎች እያሳዩ ነው። የተለያዩ የሽብር እና ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎችን ወታደራዊ ሥልጠና እየሰጠ ወደ ሀገር ወስጥ በማስረግና የሽብር ጥቃት እንዲፈፅሙ እየሰራ የመሆኑ ሚስጥርም የሁከት ስፖንሰር አድራጊነቱ ምልክት ነው። በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ የአሰማራቸው ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና የተወሰኑት መገደላቸውንም አባባሉን ያረጋግጣል።
ይህ የሚያሳየው የኢሳያስ ሥርዓት መቼም ቢሆን የኢትዮጵያን የሰላም፣ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ለማደናቀፍ ተኝቶ የማያድር ሃይል መሆኑን ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ውስጥም የተረጋጋ ሁኔታ እናዳይፈጠር ሳያሰልስ እየሰራ ነው፡፡ ይህን እኩይ ድርጊቱን ደግሞ የሀገራችን ህዝቦችና መንግስት በሚገባ ያውቁታል። ግን ይህን አዋኪና ፅንፈኛ ሥርዓት እስከ መቼ ነው እያስታመምን የምንቀጥለው ለተጨማሪ ጥፋትና የቀቢፀ ተስፋ ሩጫ እንዲነሳሳስ እድል የሚሰጠው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ወቅታዊ ጉዳይ ነው። በተለይም ለመንግስት እረፍት የማይሰጥ ጥያቄ ሊሆንም ይገባል ፡፡
ስትራቴጅክ ትእግስት ;የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪክስ ትሪልሰን አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ የነበራት «ስትራተጂክ ትእግስት/Strategic Patience» ፖለሲ ለመለወጥ የምትገደድበት ወቅት ላይ መሆኑን በቅርቡ ገልፀዋል። ይህን ፖለሲ ለመለወጥ ጫፍ ላይ ተደርሷል የተባለበት ምክንያት ሰሜን ኮርያ በተደጋጋሚ በምታሳየው ትንኮሳና ዓለም አቀፍ ስምምነትን የመተላለፍ ድርጊት ነው፡፡ በተለይ የአካሄደችው የሚሳይል ሙከራን ተከትሎ አሜሪካ ፖሲሲዋን ለማጤን ተገዳለች። ይህ የሰሜን ኮሪያ ድርጊት አጠቃላይ ምዕራባውያንና ሸሪኮቻቸውን ያሳሰበ ቢሆንም አሜሪካንን ደግሞ ይበልጥ በማሳሰቡ ከዚህ ቀደም ትከተለው የነበረውን ስራቴጅክ ትእግስት ዳግም ለመፈተሽ እንደምትገደድ እየገለፀች ነው።
ስትራቴጀክ ትግእስት የማይሰራበት ወቅት ላይ እንደተደረሰ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እየገለፁ ነው። ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ መሆናቸው (all options are under table) በአፅንኦት ገልፀዋል። ሰሜን ኮሪያን በሂደት የኑክለርና ሌሎች ጀምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ባለቤት እንዳትሆን ቀስ እያለየ በትእግስት መያዝን የሚለው የኦባማ አስተዳደር አስተሳሰብ አሁን አይሰራም ሲሉ በግልፅ መናገራቸው እኛም ልንማርበት የሚገባ ጉዳይ ነው ።
ሊ ኤች.ሃምለተን የተባሉ በህንድ ዩኒቨርሲቲ የሉላዊነትና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ምሁርም አሜሪካ ከዚህ በፊት ትከተለው የነበረው ፖለሲ ድጋሚ ማየቷ የግድ ይላታል ሲሉ ገልፀዋል። ምክንያቱም ሰሜን ኮሪያን በአሁኑ ሰዓት ስጋት መሆኗንና የጊዜ ቦምቡ ለመፈንዳት በመቃረቡ ነው። ስለሆነም አሜሪካ ቻይናን በማግባባት፣ ተከታታይ ማእቀብ በመጣል፣ ወታደራዊ ጫና እና የስለላ መረቧን በከፍተኛ ሁኔታ በማጠናከር እና ሌሎች የግድ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ የሰሜን ኮሪያን ጉዞ መግታት ይገባታል ይላሉ። ዓለምንም ለመታደግ በተለይ የሩቅ ምስራቅ ቀጣናንም ላለማወክም ከአሁን በኋላ «ስትራቴጀክ ትእግስት» ፖለሲ የማይሰራ መሆኑንም ያሰምሩበታል።
ተመጣጣኝ እርምጃ አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ የተከተለችውን ስትራቴጅክ ትእግስት ዓይነት ፖለሲ ኢትዮጵያም በኤርትራ ላይ «ተመጠጣኝ እርምጃ» ፖለሲን ተግባራዊ ስታደርግ ነበር። ይህ ፖለሲ ለረጅም ዓመታት ከኤርትራ ትንኮሳ በተቃጣ መጠን ተግባራዊ እየሆነ ዛሬ ላይ ደርሰናል። በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራን በዲፕሎማሲ መድረክ ማእቀብ እንዲጣልባት በተሰራው ስራ ማእቀብ ማስጣል ተችሏል። ነገር ግን ማእቀቡ በአግባቡ ተተግብሯል የሚል እምነት በብዙ ተንተኞችም ቢሆን የለም። የኤርትራን መንግስት በጦር መሳሪያ እና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ሊያዳክሙ የሚችሉ ማእቀቦች ቢጣሉበትም አሁንም ከፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ድጋፍ እያገኘ ነው። በወደብ ኪራይ ሰበብ እና በተለያዩ ምክንያቶች ለጥፋት የሚሆን አቅሙን ማጠንከር የሚችሉ ድጋፎች በተለይ ከመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት እያገኘ መሆኑን የአደባባይ ሚስጥር ነው።
የኤርትራ መንግስት ትንሽ ገንዘብ በአገኘ ቁጥር የምስራቅ አፍሪካን አለመረጋጋት ለማስቀጠል ይሰራል። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ትርምስ ለመፍጠር የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። የሀገር ውስጥ ፀረ ሰላም ሃይሎችን አስታጥቆ እያሰማራ ነው። በአለፈው ዓመትም በጾረና ግንባር በኩል ትንኩሳ መፈፀሙ አይዘነጋም። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተከስተው የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን ወደ ሁከቶች በመቀየር ከአዝማቾቹ ጋር ሆኖ ከጀርባ እንደነበር ገሃድ ነው። ስለዚህ በኤርትራ መንግስት ስንከተለው የነበረ ፖሊሲ አሁን ላይ የማይሰራበት ደረጃ ላይ መድረሱ መታወቅና መታመን አለበት ሚል አተያይ አለኝ።
በእርግጥ ይህንን በመገንዘብም መንግስት በጥናት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ሂደት ላይ መሆኑን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገልፀዋል። ይህ የፖለሲ ለውጥ ወቅታዊ እና የግድ ነው። የሀገራችንን ሰላም በኤርትራ መንግስት ጣልቃ ገብነት ዳግም አደጋ ላይ የማይወድቅበትን ሁኔታ መፍጠር የሚችልም መሆን አለበት። በተለይ እርምጃው 910 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የጋራ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የየእለት የፀጥታ ስጋት ተወግዶ ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥም መሆን ይገባዋል።
የኤርትራ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጠንቅ ብሎም በክፍለ አህጉሩ ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍንና መረጋጋት እንዳይኖር አጥብቆ የሚሠራ መሆኑን በግልፅ አይተናል። በዚህ መንግስት ይባል አንጂ ከመንግስት በታች የወረደ ሃላፊነት የጎደለው ሃይል ነው። ስለሆነም ሀገራችን ትከተለው የነበረው «የተመጣጣኝ እርምጃ» ፖለሲ ቆም ብሎ መፈተሽ ተገቢና አስፈላጊ ነው። በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ተጨማሪ ጥረቶች እና ሥራዎች መሰራት አለባቸው።
አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ስትከተለው የነበረው «ስትራቴጅክ ትእግስት» ፖለሲ ከአሁን በኋላ የማይሰራ መሆኑንና በሌላ መተካት እንዳለበት ይፋ እንዳደረገችው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስትም በኤርትራ ላይ ይከተለው የነበረው «ተመጣጣኝ እርምጃ» ፖሊሲ ቆም ብሎ በማየት በጥናት ላይ የተመሰረተ የፖለሲ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥናት ሂደት መሆኑን የገለፁት ተለዋጭ ፖሊሲ ቶሎ ተጠናቅቆ ይፋ ይደረግና ወደ ተግባር ይገባ የሚለው የብዙዎች አስተያየትም ሊደመጥ ይገባል ።
ከአሁን በኋላ «በተመጣጣኝ እርምጃ» ፖሊሲ ረጅም ርቀት መጓዝ የማይቻል መሆኑን በአለፈው ዓመት በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተከስቶ ከነበረው ሁከት በላይ መማሪያ የለም። ከእነዚህ ሁከቶች ጀርባ የኤርትራ መንግስትና የአዝማቾቹ (እንደነ ግብፅ… የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ሂደት ለማስተጓጎል) እጅ አለበት የሚሉ አስተያየቶችም ወደ ጎን ሊገፉ አይችሉም ። ምንም እንኳ የሁከቱ መነሻ የውስጥ ችግራችን እና የህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን መልስ ያለማግኘቱ ጉዳይ ቢሆንም።
በጥቅሉ የኤርትራ መንግስት ለሀገሩም፣ ለክፍለ አህጉሩም የሰላም ጠንቅ በመሆኑ በጋራ ከታመነበት ለራሳቸው ለኤርትራውያን፣ ለቀጣናው ሀገሮችም ሆነ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ሲባል እርምጃ መውሰድ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል እላለሁ።
ካይዳኪ ዳንኤል