NEWS

ሽብር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ በምዕራብ ትግራይ ዞን የተያዙ 76 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

By Admin

March 06, 2017

በኤርትራ ከአሸባሪው ግንቦት ሰባት የሽብር ተልእኮ ወስደው በሀገር ውስጥ ሽብር ለመፈጸም በምዕራብ ትግራይ ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ የተያዙ 76 ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።ግለሰቦቹ ቃፍታ ሁመራ ላይ በፀጥታ ሃይሎች ላይ ተኩስ በመክፈት የሁለት የጸጥታ አስከባሪዎች ህይወት እንዲያልፍ ማድረጋቸው በቀረበባቸው ክስ ላይ ተጠቅሷል ።ዛሬ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ለቀረቡት ተከሳሾች የክስ ሰነዱ እንዲደርሳቸው ያደረገ ሲሆን፥ ክሱን ለማንበብም ለረቡዕ የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።1ኛ ሚፍታህ ሼክሱሩር፣ 2ኛ ግርማ ፈቀደ፣ 3ኛ እሸቴ ዘለቀን ጨምሮ 76 ግለሰቦች ናቸው።የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ ላይ ተከሳሾቹ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፈራረስ አላማ ይዞ በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ህብረተሰቡን በማስፈራራት የሃገሪቱን መንግስታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማፈራረስና ማናጋት የሚንቀሳቀሰውና ራሱን የአርበኝች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ብሎ በሚጠራው የሸብር ቡድን በ2007 ዓ.ም አባል መሆናቸው በክሱ ተጠቅሷል።ተከሳሾቹ ከተለያዩ የሽብር ቡድኑ አመራሮች የሽብር ተልዕኮ በመቀበል ኢትዮጵያ መሃል ሃገር ገብተው ሽብር ለመፈጸም በቡድን በመከፋፈል በጸገዴ፣ ላይና ታች አርማጭሆ፣ መተማ፣ ወልቃይት እና በቋራ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞችን በመንግስት ላይ ለማሳመጽ፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ነዳጅን እንዳይገባ ለማድረግ፣ በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤቶች ጥቃት ለመፈጸምና ታራሚዎችን ለማስለቀቅ በተለይም ቋራ ላይ የሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ለመመስረት በማቀድ መግባታቸውንም ክስ ያስረዳል።ለዚህ ተግባር ማስፈጸሚያም ሁለት መትረየስ ከ1 ሺህ ጥይት፣ ሶስት ስናይፐር ከ450 ጥይት ጋር፣ 73 ክላሽ መሳሪያ ከነብስ ወከፍ 280 ጥይት ጋር፣ 85 ቦምብ፣ 36 የቅስቀሳ ሰነድ፣ 1 የጦር ሜዳ መነጽር በመታጠቅ ሊገቡ ሲሉ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ላይ በመከላከያ ሰራዊትና በአካባቢው ነዋሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።ተከሳሾቹ በጸጥታ ሃይሎች ላይ ተኩስ በመክፈት የሁለት የሚኒሻ አባላት ህይወት እንዲያልፍ ማድረጋቸው በቀረበባቸው ክስ ላይ ተጠቅሷል።ጠቅላይ አቃቤ ህግም በዋና ወንጀል አድራጊነት የሽብር ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።ተከሳሾቹ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ ሰነዱ ለእያንዳንዳቸው ተሰጥቷቸዋል።ፍርድ ቤቱ በግላቸው ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ መንግስት ጠበቃ እንደሚያቆምላቸው ገልጿላቸዋል።በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ፌዴራል ፖሊስ ተከሳሾቹን ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ አዟል።ክሱን ለተከሳሾቹ ለማንበብ ለየካቲት 29 ቀን 2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።FBC