Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቀጣናዊ የዲፕሎማሲ ትስስር

0 454

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀጣናዊ የዲፕሎማሲ ትስስር (ቶሎሳ ኡርጌሳ)

ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኡጋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ተገኝተው በሁለቱ ሀገራት የሰላም፣ የፀጥታ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደው ተመልሰዋል። በውይይታቸውም በሰሜን ምሥራቅ ኡጋንዳ ውስጥ የምትገኘው “ካራሞጃ” የተሰኘች ከተማን ከሰሜናዊ ኬንያ በኩል ከደቡብ ኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘት የታቀደውን የመንገድ ስራ ለመጀመር ተስማምተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማርዲያት ለሶስት ቀናት በሀገራችን ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በተለያዩ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊና ተጓዳኝ የፀጥታ ጉዳዩች ላይ ስምምነት አድርገው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

እነዚህ ሁለት ሰሞነኛ አብነቶች የሚያሳዩን ነገር፤ ሀገራችን ዛሬም እንደ ትናንቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ ካሉት ሀገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር እየፈጠረች መሆኑን ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘለግ ላሉ ዓመታት በትስስር ከሚገኝ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ጥቅም ምንም ነገር አላገኘም። ለዚህ ደግሞ በቀጣናው ውስጥ የነበረው ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ጦርነት በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ይህ የጦርነት ታሪክ በአንፃራዊ ሁኔታ ጋብ በማለቱ፤ የቀጣናው ሀገራት ከሁለንተናዊ ትስስር የሚገኘውን ጥቅም ለማጣጣም በርካታ ውጥኖችን ይዘዋል። በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው አብነታዊ ስምምነቶች የዚህ አባባሌ አስረጅ ይመስሉኛል። ይህ ሁኔታም ሀገራችን በተጎናፀፈችው ሰላም የተገኘ መሆኑ አይታበይም።

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው፤ ሀገራችን እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ በእርስ በርስ ግጭትና ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ ኖራለች—ባለፉት ስርዓቶች። ግና ምስጋና ለኢፌዴሪ መንግስትና እርሱ የሚከተለውን ስርዓት እውን ለማድረግ ህይወታቸውን ለሰጡ ውድ የህዝብ ልጆች ይሁንና በዚህ መጥፎ ምሳሌነት የተሳለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ገፅታዋን በመለወጥ ላይ ትገኛለች። መንግስትና መላው ህዝቦቿ አንድነት ፈጥረው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ባከናወኗቸው ዘርፈ- ብዙ ቅንጅታዊ ስራዎች ከቀጣናው አንፃራዊ ሰላም ተጠቃሚ እየሆነች ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክም በአዲስ ገፅታ መታየት ከጀመረች ሰነባብታለች። በዚህም ሳቢያ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። የዲፕሎማሲው ተሰሚነቷ ሁሉንም የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቱን ሀገራት እየሳበ በመምጣቱም ዛሬ የኢትዮጵያን ምክርና ልምድ ለመጠየቅ ወደ መዲናችን የሚያቀኑ የአፍሪካ መሪዎች እየተበራከቱ እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል።

ለዚህም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ የሰፈሩት ወሳኝ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ህገ መንግሥቱ የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝና በገራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ መሰረትን እውን አድርጓል። ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮንም ተጫውቷል።

እርግጥ ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ በሚቀንስ ደረጃ የተተለመ ነው። ይህም ዲፕሎማሲው በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ አደጋዎችን የመቀነስ እንዲሁም ቀጣናዊ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ የማድረግ መንገድን የሚከተል ነው።

ይህ ሁኔታም ሀገራችን እስከ ዛሬ ድረስ የተከተለችው ቀጣናዊ የዲፕማሲ ትስስር በተቃና ሁኔታ እንዲፈፀም ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። ይሁንና አሁንም በቀጣናው ውስጥ የሚያታዩትን እንደ አልሸባብ ዓይነት አሸባሪዎችን ለመከላከል፣ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግና የቀንዱ አንዳንድ ሀገራት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገባዊ አካሄድ ለማስቆም ብሎም እንደ ኤርትራ ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው መንግስታት በቀጣናው ያልተቋጩ ቀውሶች ውስጥ በአሉታዊ መንገድ እጃቸውን ለማስገባት የሚያደርጉትን ጥረት ለመከላከል የክፍለ-አህጉሩ ሀገራት ዛሬም ቢሆን በጠንካራ የዲፕሎማሲ ገመድ ሊተሳሰሩ ይገባል። ትስስሩም በእኩል ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩር መሆን ይኖርበታል።

የዲፕሎማሲው ትስስር ገመድ የቀጣናውን ህዝቦች ጥቅም ብቻ ያማከለ ሊሆን ይገባዋል። የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በባህል፣ በታሪክ፣ በአብሮ መኖር፣ በመዋለድና አንዱ የሌላኛውን ሀገር እንደ ሁለተኛ መኖሪያው በመቁጠር የቅርብ ግንኙነት የታጠረ ነው። በመሆኑም የቀጣናው ሀገራት ይህን ዘመናትን የተሻገረ የህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ አጥብቀው ማሰር ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ በየጊዜው እየተገናኙ የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር መለወጥ ይጠበቅባቸዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ ያካበተቻቸውን ተጨባጭ ተሞክሮዎች በመቀመር የመሪነት ሚናዋን በተገቢው ሁኔታ ልትወጣ ይገባታል። እርግጥ ሀገራችን በራሷም ሆነ በአካባቢው ሀገራት የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የሰላምና የትብብር አድማስ በዲፕሎማሲ ታጅቦ እንዲሰፋ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባታል። ለዚህም ሀገራችን የምትከተለው የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርሆዎች ያግዟታል።  

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ ዛሬ ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድን አትከተልም። ከዚህ ይልቅ ለውስጥ ችግሮቿ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥታለች። ድህነት በተሰኘው አሳፋሪ ጠላቷ ላይ ጠንካራ የህዝቦቿን ክንድ በማስተባበር የቀጣናው ብሎም የአህጉሪቱ የልማት እመርታ ተምሳሌት ሆናለች። ሆኖም ይህ የልማት እመርታዋ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤቶቿም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠንካራ አካባቢያዊ ትብብርና የዲፕሎማሲ ቁርኝት የግድ ይላታል።

በምንገኝበት 21ኛው ክፍለ ዘመን አንድ ሀገር ‘ነገር ዓለሙን ሁሉ ጥሎ’ ለብቻው እየቆዘመ ሊኖር አይችልም። ዘመኑ የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) በመሆኑም እንኳንስ በአቅራቢያ ካሉት የቀጣናው ሀገራት ቀርቶ እጅግ በራቀ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦችና ሀገሮች ጋርም ቢሆን መቀራረብና አብሮ መስራት ይጠይቃል። በዚህ ዓለም እንደ አንድ መንደር በምትቆጠርበት ዘመን ውስጥ የተለያዩ ሀገራት ባለሃብቶች አህጉሮችን አቋርጠው ለኢንቨስትመንት ስራ ወደ ቀጣናው ሀገራት የሚመጡት በዲፕሎማሲያዊ ቁርኝነት ምክንያት ነው። እናም እኛ የሌለን ከባለሃብቶቹ ማግኘት ስለምንችል፤ ተቀራርቦ ለጋራ ጥቅም አብሮ መስራት ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ “ሩቅ አሳቢ፣ ቅርብ አዳሪ” የሚለው ሀገራዊ ይትብሃል አይሰራም። ይልቁንም ጠቃሚው ነገር ሩቅ አስቦ፣ ለጋራ ተጠቃሚነት ሩቅ ማደርን እንደ መርህ መከተል ይመስለኛል።  

ታዲያ አንድ ሀገር በዲፕሎማሲያዊ የቁርኝት ድር ለጋራ ተጠቃሚነት ሩቅ ለማደር ከሻተ፤ እዚሁ በአቅራቢያው ካሉት የቀጣናው ሀገራት ጋር በዲፕሎማሲው መስክ ለመተሳሰር የሚገደው አይመስለኝም። ሆኖም ትስስሩ ጥንቃቄ የተሞላበትና የቀዳሚነት ሚና ሊኖረው የሚገባ ይመስለኛል። አንድ ጉዳይ ከተፈፀመ በኋላ ሁኔታውን ለመቀልበስ የሚደረግ የ“አባሮሽ” ዓይነት ክትትል የትም የሚያደርስ አይሆንም። እንዲያውም ይህን መሰሉ የዲፕሎማሲ መስመር “ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” ከሚለው ሀገራዊ አባባል ብዙም የሚለይ አይደለም። እናም አንድ ነገር ከመፈፀሚ በፊት አስቀድሞ በማቀድና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ሩቅ በማሰብ የዲፕሎማሲውን ትስስር ይበልጥ ማጥበቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የማስፈፀምና የመፈፀም አቅሞችን ማጎልበት ይገባል።

እርግጥ ይህን አቅም ለመገንባት መሰረቱ የሰው ሃብት ነው። መፈፀምና ማስፈፀም የሚችል የሰው ሃይል በዲፕሎማሲው ዓለም የሚጠይቀውን ግብዓት ማግኘት የግድ ይለዋል። በዲፕሎማሲ እውቀትና ክህሎት የተካኑ የሰው ሃብት የሌሏት ሀገር ትስስሯን በሚገባ መንገድ ልትወጣ አትችልም። እናም ሁለንተናዊ አቅም ያላቸውን ዲፕሎማቶችን ማፍራት ይኖርባታል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ሰሞኑን በሁለተኛ ዲግሪ አሰልጥና ያስመረቀቻቸው 94 ዲፕሎማቶች በመንግስት የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት ብሎም የሀገራችን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ።

ሀገራችን ዛሬም እንደ ትናነት ቀጣናውን ብሎም አፍሪካን በመወከል በዓለም መድረክ የአፍሪካውያን ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ የማድረግ ሚናዋን ትወጣለች። ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ለውስጥ ጉዳይዋ ቅድሚያ የምትሰጥ ሀገር ብትሆንም፤ ዕድገቷ ከጎረቤቶቿ ሰላምና መረጋጋት ተለይቶ ሊታይ የሚችል አይደለም። እናም ለውስጥ ጉዳይዋ ከምትሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ ለቀጣናው ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ትስስርም ይበልጥ ጠንክራ ልትሰራ ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy