CURRENT

በሀሰተኛ ምስክሮች ፍትህ እንዳይዘባ የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

By Admin

March 05, 2017

መቀሌ  የካቲት 26/2009 በሀሰተኛ ምስክሮች  ፍትህ እንዲዘባ የሚደረጉ ሙከራዎችን ለመግታት  የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ  በህግ ስርፀት፣ የእውነተኛ ምስክርነት አሰጣጥ፣የጠበቆችና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ   ሚዛናዊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከህዝብ ክንፍ አደረጃጀቶችጋር በአክሱም ከተማ ተወያይቷል፡፡

በቢሮው  የወንጀል ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ጎይቶኦም ገብረማርያም በውይይቱ ላይ እንዳሉት በሀሰተኛ ምስክሮች በክልሉ  ፍትህን ለማዛበት  የሚደረጉ ሙከራዎች አሉ፡፡

በገንዘብና በሌሎችም መደለያዎች ሀሰተኛ ምስክር የሚሆኑ ግለሰቦች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ጠቁመው  በተጨማሪም  የሚያውቁት ነገር በትክክል አለመናገርና እንደማያውቁ መምሰል ሌላው ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

” በዚህም  አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት ሲገባቸው ንፁሀን ለቅጣት ይዳረጋሉ “ብለዋል፡፡

በመሬት፣በህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣አስገድዶ መድፈርና በአራጣ  አበዳሪዎች የሀሰት ምስክር የሚበዛባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ ጎይተኦም ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በፍርድ ቤትና በሌሎችም የፍትህ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ  ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማድረስ አቅሙ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡

ችግሩን ለመግታት የሀይማኖት አባቶች ምስክር ሆነው ቃላቸውን ለሚሰጡ ምእመናን ትክክለኛ ቃላቸውን እንዲሰጡ  በማስተማር  ሚዛናዊ ፍትህ እንዲኖር  የድርሻቸውን እንደወጡም ጠይቀዋል፡፡

የሀይማኖት አባቶች በበኩላቸው የሀሰት ምስክርነትን ለማስቆም ከፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ከትግራይ ደቡባዊ ዞን የኦፍላ ወረዳ ሰበካ ጉባኤ  ጽህፈት ቤት  ተወካይ  ሊቀ ትጉሃን ሞላ በየነ በሰጡት አስተያየት ”  የሀሰት ምስክርነት መበራከት የሀይማኖት አባቶች ሀይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዳልተወጡ ያሳያል” ብለዋል፡፡

በሀሰት ምስክርነት ፍትህን ማዛባት  በሀይማኖት የተወገዘ መሆኑን ተከታዮቻቸውን ለማስተማር  ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

“በሀሰት ምስክርነት ምክንያት አንድ ሰው ባልፈፀመው ጥፋት እንዲሸከም የማድረግ ዝንባሌዎች መገታት አለበት” ያሉት ደግሞ ከመቀሌ ወንገላውያን ቤተክርስትያን የተወከሉት ፓስተር አለማየሁ ግርማይ ናቸው፡፡

የሀሰት ምስክር በሂደት ማህበራዊ ቀውስ ስለሚያስከትሉ በዚሁ ድርጊት የተሰማሩ ግለሰቦች ለመገሰፅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በማዕከላዊ ዞን ወርዒ ለኸ ወረዳ  የእደጋዓርቢ ከተማ ነዋሪና የውይይቱ ተሳታፊ ሼክ  መሐመድ ሃጎስ በበኩላቸው “በሀሰት መመስከር በቅዱስ ቁርአን  የተከለከለ ነው ” ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመከላከል የሀይማኖት አባቶች በየእምነት ተቋማቱ ህብረተሰቡን ማስተማር እንደሚገባቸም ጠቁመዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በተካሄደውና ትናንት በተጠናቀቀው ውይይት ላይ  የሃይማኖት አባቶች ፣የአገር ሽማግሌዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ፣ሞዴል አርሶ አደሮችና ሌሎችም የህዝብ ክንፍ አደረጃጀቶች ተሳትፏል።