NEWS

በምስራቅ ሸዋ ዞን 587 ካርቶን ሺሻ በድብቅ ሲጓጓዝ ተያዘ

By Admin

March 15, 2017

በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፈንታሌ ወረዳ ወደ አዳማ ከተማ በድብቅ ሲጓጓዝ የነበረ 587 ካርቶን ሺሻ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።እቃው ሊያዝ የቻለው በአሸዋ ስር ተጭኖ ሲጓዝ የነበረበት ሲኖትራክ ተሽከርካሪ በመገልበጡ ነው።

የዞኑ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት ኮድ 3 ኢት 77657 ሲኖትራክ ተሽከርካሪ የተገለበጠው ትናንት ከቀኑ 7 ሰዓት አሸዋ ጭኖ ከፈንታሌ ወረዳ መተሀራ ከተማ አካባቢ ወደ አዳማ ሲጓዝ ነው።

የፊት ጎማው ፈንድቶ ልዩ ስሙ አዴቻ በተባለው ስፍራ የመገልበጥ አደጋ ባጋጠመው ተሽከርካሪ ውስጥ አሸዋ ለብሶ በድብቅ ተጭኖ የነበረና 1ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው 587 ካርቶን  ሺሻ በመዘርገፉ ሊያዝ ችሏል።የመኪናው አሽከርካሪና የህገ-ወጥ ዕቃው ባለቤት ለጊዜው በመሰወራቸው ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑንም ምክትል ኮማንደሩ ተናግረዋል ።

በአሳቻ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች የሚካሄደው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሆነ ህብረሰተቡ አካባቢውን በንቃት በመከታተልና ወንጀለኞችን ለፖሊስ በመጠቆም እንዲተባበር ምክትል ኮማንደር አስቻለው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።