በረሃብተኛ ዝርዝር ውስጥ ያለመካተታችን ለሁላችንም ትልቅ ድል ነው!(ወንድይራድ ሃብተየስ)
በቅርቡ የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ማጠናቀቁን ተከትሎ የወጣው መግለጫ ላይ በርካታ ጠቀሚ ርዕሰ ጉዳዮች ተመለከትኩና ሌሎችም ቢያውቋቸው ያልኳቸውን አንዳንድ ነገሮች ለማንሳት ወደድኩ። ከእነዚህም መካከል የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ አንዱ ነበር። በቅርቡ በአገራችን ተከስቶ የነበረው ሁከት ዋንኛ መነሻ የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦት ነበር። መንግስትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ በወቅቱ ለህዝብ በገባው ቃል መሰረት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተብለው የተለዩ ጉዳዮችን በየደረጃው መፍትሄ በመስጠት ላይ ይገኛል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት በሁሉም የህብረተሰብ አካል ቀጥተኛ ተሳትፎ ብቻ ነው። የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ውጤታማነት በሕዝቡ ተሳትፎ የሚለካ ነው። በመሆኑም ኢህአዴግ አመራሩንና አባላቱን የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርጉ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር ጉድለት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ በየደረጃው ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር አስፍኗል። ይህም በተግባር ታይቷል። ፐብሊክ ሰርቪሱ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲከተል ለማድረግ በርካታ የውይይት መድረኮችን ተካሂደዋል። ህብረተሰቡም የሚታዩ ወይም አሉ የሚሏቸውን ችግሮች እንዲሁም መፍትሄ የሚለውን ሃሳብ በስፋት ሰንዝሯል። ይህን አይነት አካሄድ እጅግ መልካም ነው። ሁላችንም ለአገራችን ችግሮች በጋራ መፍትሄ የማፈላለግ ልምድ እንዲዳብር መንግስትና ገዥው ፓርቲ እየተከተሉ ያሉት አካሄድ እጅግ መልካም ነው።
በስራ አስፈጻሚው መግለጫ ላይ እንደሰፈረው የተሃድሶ ንቅናቄ እና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ሳይነጣጠሉ ለማስኬድ “እየታደስን እንሰራለን፤ እየሰራን እንታደሳለን” በሚል አገላለጽ ለእኔ እጅግ ጠንካራና በሳል ሆኖ አገኝቼዋለሁ። አዎ ይህ ድንቅ አባባል ነው። ለሁሉም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዕለቱን መፍትሄ ማግኘት አይቻልም። ዴሞክራሲ ሂደት ነው ይባላል። ይህ እውነት ነው። “እየታደስን እንሰራለን፤ … ” የሚለው የለውጥ አስተሳሰባችንን በአመራሩ፣ በአባሉና በህዝቡ መካከል እያሰረጽን የዴሞክራሲ ስርዓታችንን እያጎለበትን በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድን ማፋጠን ይጠበቅብናል የሚልን ሃሳብ የያዘ ሲሆን፤ በተመሳሳይ”…፤ እየሰራን እንታደሳለን” የሚለው ደግሞ በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማፋጠን የአስተሳሰብና የተግባር ለውጥ ማድረግ የሚያስችሉንን ተሃድሶ ማካሄድ እንደሚገባን መግለጫው አመልክቷል።
የአገራችንን ህዳሴ ዕውን ልናደርግ የምንችለው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለመተግበር የያዝናቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች ማከናወን ስንችል ብቻ ነው። ከኢህአዴግ መግገለጫ ላይ “እየታደስን እንሰራለን፤ እየሰራን እንታደሳለን” የሚለው አባባል አትኩሮ ለተመለከተው ጥልቀት መልዕክት ያለው አባባል ነው። ለዚህ ነው ድርጅቱ እነዚህን ሁለት ነገሮች ጎን ለጎን ማስኬድ መቻል አለብን ያለው።
ድርጅቱ በመግለጫው ሌላው ያነሳው ጉዳይ ትምክህትና ጠባብነትን የተመለከተ ነው። የትምክህትና ጠባብነት አመለካከቶችና ተግባራት የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ህልውና ዋንኛ አደጋ ናቸው። እነዚህ ሁለት አካላት አገራችንን ለማፍረስ፣ ህዝቦችን ለመነጣጠል፣ አገራችንን የደም አውድማ ለማድረግ በርካታ ጥረቶችን አድርገው ነበር። ይሁንና በህብረተሰቡ አንከፋፈልም አንነጣጠልም ባይነት የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ፍላጎት ሳይሳካ ቀረ። እነዚህን ሃይሎች የህዳሴውን ጉዞውን ማደናቀፍ እንዳይችሉ ህብረተሰቡ ያደረገውን ጥረት ስራ አስፈጻሚው አድንቆ በቀጣይም ለአገራዊ ህዳሴ እውን መሆን ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪውን አቅርቧል። ባለፈው በአገራችን ተከስቶ በነበረው ሁከት ጥበትና ትምክህት ሁለት ጽንፎች ለጥፋት ሲሆን ሲደጋገፉና ሲሞጋገሱ ተመልክተናል። ይህ አካሄድ አደገኛና ሁላችንም ልናወግገዘው የሚገባ አካሄድ ነው።
የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በስፋት የተመለከተው ሌላው ጉዳይ የወጣቶች በልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ነው። መንግስት ቀድሞ የነበረውን የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅ በማሻሻል ለወጣቶች የበለጠ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂን አዘጋጅቷል። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ወቅት የተስተዋሉ ድክመቶችን በማረምና የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን የበለጠ በማጎልበት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ወቅት የተሻለ የስራ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸው ኮሚቴው በመግለጫው አስፍሯል። ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት ከቻሉ የማይፈጽሙት ነገር እንደሌለ የአገራችን ፈጣን እድገት ጥሩ ማሳያ ነው።
ወጣቱ የስራ ጠባቂ እንዳይሆን መንግስት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ተገለባባጭ ፈንድ መድቧል። ይህ ገንዘብ ለወጣቱ የስራ መነሻ እንዲሆን መንግስት ከሌላ በጀት ቀንሶ ለወጣቱ መለወጥ አስቦ የመደበው ገንዘብ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ይህን የህዝብ ገንዘብ በሃላፊነት መጠቀም ይኖርባቸዋል። ወጣቱ ለስራ አክብሮት በመስጠትና የቁጠባ ባህልን በማዳበር ለአገርና ለወገን ጠቃሚ ስራዎችን ማከናወን ይኖርባቸዋል። አገራችን እያስመዘገበች ካለችው ልማት ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑት በራሳቸው ጥረት እንጂ እርዳታ የትም ሊያደርስ ስለማይችል የወጣቱ ጥረት ወሳኝ ነው።
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሌላው የተመለከተው ጉዳይ ደግሞ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምን ነበር። አሁን ላይ የዕቅዱን የአንድ አመት ከግማሽ አፈፃፀም ሪፖርት ኮሚቴው ገምግሞ የዕቅዱ አፈጻጸም በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል። በያዝነው ዓመት የመኸር ግብርና እድገት በአማካይ 12 በመቶ እድገት አስምዝግቧል። የአገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና በተቀመጠለት የዕድገት ቀመር ተጉዟል። በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ 50 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት ተሰብስቧል። በመኸር የአዝመራ ወቅት በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ ከ320 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል ማሰባሰብ የተቻለው መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ነው። የኮሚቴው ግምገማ እንዳሳየው በመስኖ እና በበልግ ስራዎች ላይ የተሻለ ርብርብ ከተደረገ የአመቱ አፈጻጸም ከዚህ የተሻለ እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡
አሁን ላይ በመኸር ብቻ ተጨማሪ ተብሎ የተሰበሰበው 50 ሚሊዮን ኩንታል ከሁለት ዓስርት አመታት በፊት ዋናው የአገራችን ምርት እንደነበር ማስታወሱ የግብርናው ዘርፍ ምን ያህል እንዳደገ ያሳያል። ከዚህም ባሻገር አገራችን ስኬታማ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መከናወኑን ኮሚቴው በመግለጫው አብራርቷል። አዎ ዛሬ በተቀናጀ በተፋሰስ ስራዎቻችን በርካታ አካባቢዎች ማገገም በመቻላቸው ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።
ሌላው በኮሚቴው በስፋት የተዳሰሰው ጉዳይ በአገራችን ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ነበር። መንግስት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ ድርቁ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት አላደረሰም። ከዚህ ባሻገር መንግስት ድርቅን በዘላቂነት መከላከል የሚቻልበትን ሁኔታ ቀይሶ በመተግበር ላይ ነው። የተባበሩት መንግስታት ሰሞኑን ባሰማው የድረሱልኝ ጥሪ መሰረት በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በናይጄሪያና በየመን ከ20 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በከፋ የምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸውን ገልጾ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ካላገኙ አስጊ ሁኔታ እንደሚፈጠር አስጠንቅቋል። ወትሮ ቢሆን ድርቅ ተከሰተ ከተባለ የአገራችን ስም በዝርዝር ውስጥ በቅድሚያ የሚጠቀስ ነበር። ይሁንና አሁን ላይ ነገሮች ተለውጠዋል። በአገራችን ድርቅ ቢከሰትም ወደ ረሃብ እንዳይቀየር ማድረግ ተችሏል። ይህን መቋቋም የተቻለው አገራችን በተከታታይ ባስመዘገበችው ዕድገት ሳቢያ ነው። ይህ ለህዝባችንና ለመንግስታችን ትልቅ ድል ነው።
ሌላው በኮሚቴው በስፋት የተዳሰሰው ጉዳይ የኢንዱስትሪ ዕድገትን በተመለከ ነው። መንግስት የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማትን በማፋጠን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ በመስራቱ ዘርፉ ዕድገት እያሳየ መሆኑን ኮሚቴው ገምግሟል። በመላ አገሪቱ 13 የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ስራም በተሻለ አፈፃፀም እየተከናወነ መሆኑ ተመልክቷል። እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የአገራችን የኢኮኖሚ አወቃቀር ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪው እንዲያዘነብል ከማስቻላቸውም በላይ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የኤክስፖርት ዓቅምን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን በሚያግዙ ናቸው። የአገራችን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ሊያመጣ በሚያስችል ትክክለኛ ጎዳና ላይ ይገኛል።
ሌላው አብይ ጉዳይ በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ንረቱን በነጠላ አሃዝ ገድቦ ለመያዝ የተደረገው ጥረት ውጤታማ በመሆኑ ቁጠባ እጅጉን መሻሻሉ እንዲሁም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተያዙ የመሰረተ-ልማት አቅርቦትና ሜጋ ፕሮጄክቶች ግንባታ በመልካም አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ በመግገለጫው ተብራርቷል። በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከተያዙ ፕሮጄክቶች መካከል 2100 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የኮይሻ ፕሮጄክት እና 120 ሜጋ ዋት የሚየመነጨው የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክት የግንባታ ስራቸው መጀመሩ በግምገማው ታይቷል። ለኢንዱስትሪው እድገት የኤሌክትሪክ ሃይል ወሳኝ ግበዓት መሆኑን መንግስት በመረዳት ከፍተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል።
በማሕበራዊ ልማት ዘርፍ የትምህርትና በጤናም የተከናወኑ ስራዎች በኮሚቴው አጽንዖት ተሰጥቷቸው የተገመገሙ ዘርፎች ናቸው። መንግስት የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ እንዲሁም በጤና መስክም በተለይ የእናቶችና የህፃናት ሞት በመቀነስ ረገድ ስኬታማ ስራዎች እንደተከናወኑ በመግለጫው ላይ ተብራርቷል። የአገራችን የትምህርት ሽፋን በተለይ በአንደኛ ደረጃ እጅግ ስኬታ ሆኗል።
የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው የተሃድሶው ንቅናቄና የሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የአንድ አመት ተኩል አፈፃፀም መልካም ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን ተብራርቷል። እየተካሄደ ያለውን የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ይበልጥ በማስፋትና በማጎልበት እንዲሁም ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ በላቀ ደረጃ ለመፈፀም ሁሉም አካል በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የኮሚቴው ሪፖርት አመልክቷል። እውነት ነው አገራችን በየዘርፉ እያስመዘገበች ያለውን ስኬቶች በማስቀጠል ህዳሴችንን እውን ለማድረግ ህዝብና መንግስት የበለጠ ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል። በአጠቃላይ የተሃድሶ ንቅናቄው እና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሳይነጣጠሉ ለማስኬድ “እየታደስን እንሰራለን፤ እየሰራን እንታደሳለን” አባባል በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ የሚያፋጥን በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል።