በሳዑዲ ያለፈቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይጉላሉ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ የሚያመቻች ልኡክ ዛሬ ወደ ሪያድ ያቀናል

By Admin

March 31, 2017

የሳዑዲ ዓረቢያን ህግ ተላልፈው በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይጉላሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር የሚመክር እና አቅጠጫ የሚያስቀምጥ የልኡካን ቡድን ዛሬ ወደ ሪያድ ያቀናል።

ልኡካኑ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ያለ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሚኖሩ የማንኛውም ሀገር ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ከሀገሪቱ እንዲወጡ ማሳሰቡን ተከትሎ ነው ልኡካን ቡድኑ ወደ ሪያድ የሚያቀናው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹ ያለመጉላላት ወደ ሃገራቸው በሰላም እንዲመለሱ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጓል።

በአሁን ወቅትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል አስተባባሪ ኮማንድ ፖስት የተቋቋመ ሲሆን፥ በሀገር አቀፍ ደረጃም ስራውን የሚመራ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

በዚህ መልኩም በሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ጅዳ ባለው ቆንጽላ ጽህፈት ቤት አማካኘነት ለዜጎች አስፈላጊውን መረጃ በማቅረብ ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዛሬው እለትም ከሳዑዲ ዓረቢያ ባለስልጣናት ጋር የሚመክርና አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የልኡካን ቡድን ወደ ሳዑዲ ያመራል ያሉት ቃል አቀባዩ፥ እስከ 90 ቀናት ወደ ሃገራቸው ለሚመለሱ ዜጎች ወደ የመጡበት አካባቢ የሚመለሱበትና ቀጣይ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ ላይ ከዚህ ቀደም እንደተደረገው መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ ያመቻቻል ብለዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት የሀገሪቱን ህግ የተላለፉ የውጭ ሀገር ዜጎች ያለምንም እስራት እና የገንዘብ ቅጣት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዲስ የምህረት አዋጅ ማውጣቱ ይታወቃል።

የምህረት አዋጁ ከመጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፥ ለ90 ቀናት የሚቆይ ነው።

በህግ የሚፈለጉ፣ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ያልጨረሱ ግለሰቦች እና በእስር ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ጉዳይ በምህረት አዋጁ አልተካተተም ተብሏል።

በአጠቃላይ ስለ ምህረት አዋጁ ሊያውቋቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ 

1. የምህረት አዋጁ የተጀመረበት እለት – መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ማርች 29 ቀን 2017)

2. የምህረት አዋጁ የሚቆይበት ጊዜ – 90 ቀናት

3. ወደ ሀገር ለመመለስ የሚያስፈልጉ መረጃዎች

– የጉዞ ሰነድ (የታደሰ ፓስፖርት ወይም ሊሴ ፓሴ)

– የመውጫ ቪዛ እና

– የአየር ትኬት

4. ለጉዞ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን እንዴት ማግኘት ይቻላል?

– የጉዞ ሰነድ – ከኢትዮጵያ ኤምባሲ (ሪያድ) ወይም ከኢፌዲሪ ቆንስላ ፅህፈት ቤት (ጂዳ)

– የመውጫ ቪዛ – ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ሹሜይስ ማዕከል (ኢዳረተል ዋፊዲን)

– የአየር ትኬት – በግል (በተጓዡ/ዣ)

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ከዚህ በታች ያሉትን የስልክ አድራሻዎች መጠቀም ይችላሉ።

1. ኦሮምኛ 0507323889/0502683771/0508352545

2. ትግርኛ 0554227348/0531939823

3. ጉራጌኛ 0557914427/0506915277

4. ስልጥኛ 0504878127

5. አፋርኛ 0508210696

6. ሶማሊኛ 0500974200

7. ሀረሪኛ 0508352545

8. አማርኛ ከላይ ከተጠቀሱት ቁጥሮች በተጨማሪ 0530019206/0559891559/0537694608/0532840381 በመጠቀም መረጃ ማግኘት ይቻላል ብሏል በሳዑዲ አረቢያ

የኢትዮጵያ ኤምባሲ።

የ2017ቱ የምህረት አዋጅ፦

1. የሳዑዲን ህግ የተላለፉ የውጭ ሀገር ዜጎች ያለምንም ቅጣት በ90 ቀናት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ሲያስቀምጥ ህጋዊ ማዕቀፉን ተከትለው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መመለስ የሚፈልጉ የሚመለሱበትን አማራጭ አስቀምጧል።

2. በህግ የሚፈለጉ፣ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ያልጨረሱ ግለሰቦች እና በእስር ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ጉዳይ በ2017 የምህረት አዋጅ አልተካተተም፤ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ተለይተው በሀገሪቱ ህግ እንደሚስተናገዱ ተገልጿል።

3. በህግ የሚፈለጉ እና የህግ ሂደታቸውን ያልጨረሱ ግለሰቦች ጉዳያቸው በሚመለከታቸው የፖሊስ ተቋማት ተጣርቶ የሚቀርብ ይሆናል።

4. ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) ያላቸው ዜጎች የ2017 የምህረት አዋጅ አይመለከታቸውም።

በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲም የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በምህረት አዋጁ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የጉዞ ሰነዳቸውን በማስተካከል ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪውን አቅርቧል።