NEWS

በቆሼ በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች ስርአተ ቀብር ተፈፀመ

By Admin

March 13, 2017

በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች የቀብር ስነ ስርአት ተፈፅሟል። በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች በየእምነት ተቋማቶቻቸው የቀብር ስፍራ ነው የቀብር ስነ ስርአታቸው የተከናወነው።

የ19 ሰዎች ቀብር በተፈፀመበት የአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እና የሟቾች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና በርካታ ሰዎች ተገኝተዋል።

የቀሪዎቹ ዜጎች የቀብር ስነ ስርአት በለቡ ገብርኤል አካባቢ እና በኮልፌ ቀራኒዮ በሚገኙ መካነ መቃብሮች የተፈፀመ ሲሆን፥ ነዋሪነታቸው በተለያዩ ክልሎች የሆኑ ሟቾች አስከሬንም ዘመዶቻቸው ወዳሉበት ተልኳል።

በተያያዘ በቆሻሻ መደርመስ አደጋው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 65 መድረሱን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ አመላክተዋል። ከሟቾቹ ውስጥ 45ቱ ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ወንዶች ናቸው።

መንግስት በአደጋው ለተጎዱ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ከንቲባው አንስተዋል።

አፈሩን እና ቆሻሻውን የማንሳቱ ስራ ተጠናክሮ በመቀጠሉም የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

በደረሰው አደጋ ለጉዳት የተዳረጉ ዜጎችን በጊዜያዊነት እና በቋሚነት ለማቋቋም መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የረድኤት ተቋማት እና ሌሎች አካላት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

አደጋ የደረሰባቸውን ቤተሰቦች የማቋቋሙ ስራ ከአካባቢው የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን መልሶ የማቋቋሙ ስራ በተሟላ ሁኔታ ተጀምሯል፤ ይሄው ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ከንቲባው።

106 አባወራዎች በአጠቃላይ 297 ቤተሰቦችን በአደጋ ስጋት ወደሌላ ቦታ የማዛወር ስራ እንደተሰራ የጠቆሙት ከንቲባው፥ ሌሎችም ለአደጋ ሊጋለጡ የሚችሉ ካሉ ጥናቶች እየተደረጉ የማንሳቱ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።