Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በትዕዛዝ ሊቅ መሆን…

0 445

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዛሬ እስቲ ወደ «ራሳችን» ማለቴ ያው ወደ ማንነታችን እንመለስ እና ትንሽ እንተዛዘብ። አንዳንድ ጊዜ «ንትርክ» ሳይበዛ በትንሹም ቢሆን ደስ ይላል አይደል? ስህተቶቻችንን እና ጉድለታችንን ብሎም የድክመት ቀዳዳችንን ለመሸፈን ደግሞ ትንሽ እርስ በርስ መተቻቸታችን መልካም ነው። ለጉዳዬ መግቢያ ደግሞ ለጥቆ ያለችውን ጣፋጭ ግጥም እንደ መክፈቻ ተጠቅሜባታለሁ። ግጥሟን አንድ በነገሮች የተማረረ ጓደኛዬ የፌስ ቡክ ግርግዳው ላይ ለጥፏት ነው ያገኘኋት። እኔም ሰሞኑን የታዘብኩት ጉዳይ ነበረና ስመለከታት በልኬ የተሰፋች ነበር የመሰለች።

ላም እሳት ወለደች፤

ወንፊት ውሀ ቀዳ፤

ሺ ግመል አለፈ በመርፌ ቀዳዳ፤

በሰንበሌጥ ቁጣ ወደቀ አሉ ዋርካ፤

ተከካ አልተከካ፤

ተቦካ አልተቦካ፤

የምንቸገረኝ ቤት ሁል ጊዜ ፋሲካ፤

በትእዛዝ ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ።

ከላይ የሰፈረው ግጥም የተከተበበት ዘመን እና አውድ እንግዲህ ለዚህ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። የንጉሡ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ አማች ደጃዝማች ካሣ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ይሾማሉ፤ ዕውቀት በሹመት ይገኝ ይመስል። ደጃዝማቹ በዩኒቨርሲቲ በር እንኳን ሳያልፉ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ሕዝቡን ቢያስደንቀው ጊዜ ታዲያ እቺን ግጥም ገጠሟት አሉ።

የሚገርመው ይህ ከሆነ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥሯል። ዘመኑ ያልሰለጠነ እንዲሁም «ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ» የሚባልበት ነበረና ዘር እየተቆጠረ፣የዓይን ቀለም እየታየ፣ በአባት ስም መመሳሰል ዝምድና እየተመዘዘ፣ የአገር ልጅ፣ የሰፈር ልጅ፤ በሚል እንቶ ፈንቶ ስልጣን እና ጥቅም ወዳለበት ቦታ ወዳጆን ቢያስጠጉ እምብዛም ላይገርም ይችላል። ለኔ ግን ይሄ ጉዳይ በጣም የገረመኝ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥረው እንኳን ስልጣኔ እና እውቀት ላይ ደጃችንን በመቀርቀሪያ ሸጉረን ከድሮ ጋር ላለመፋታት ግብ ግብ ውስጥ ዛሬም የመግባታችን ጉዳይ ነው።

መች ይሄ ብቻ ሆነና ከኔ በላይ ግጥሚቷ ቆንጆ አድርጋ ብትገልፀውም፤ ላም እሳት ትወልድ ይመስል፤ «በሰንበሌጥ ቁጣ ዋርካ ለመገንደስ» የሚጥሩ ያለቦታቸው እና ያለ እውቀታቸው የተቀመጡ ስንቶች ናቸው? ከእነርሱም ብሶ በትዕዛዝ ድሪቶ እና በእንቶ ፈንቶ ማወቃቸውን ለማሳየት የሚሞክሩ እና ሠራተኞቻቸውን የሚያስጨንቁትስ?

በማይገባው ቦታ ላይ ተቀምጦ በግፍ የሰበሰበውን ገንዘብ ይዞ «ቢቦካ ባይቦካ፤ ቢከካ ባይከካ» ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ፤ ስልጣን ላይ ባለው ዘመዱ ተመክቶ፤ ትንንሽ መንግሥት የሚሆነውን ቤት ይቁጠረው። ያለቦታቸው ተቀምጠው ያሻቸውን ሲያደርጉ እና ለህሊናን የሚቀፍ ስራ ሲሰሩ ቅንጣት ያህል እንኳን የማይዘገንናቸው የመብዛታቸው ጉዳይ ደግሞ በእውነት የሚያሳዝን ነው።

ቀኑን ሙሉ ቢሮ ውስጥ ተጎልቶ «ውሀ በወንፊት የሚቀዳውስ?» 2 ሰዓትከ30 ገብቶ 11ሰዓት ከ30 ላይ በመውጣቱ ደረቱን ነፍቶ ሲንጎማለል ማየት የእውነት ያቃጥላል። ስምንት ሰዓት ወንበር ላይ መጎለት መስራት የሚመስለው ብዛቱ። ትዕዛዝ ብቻውን ስራ የሚመስለው አለቃም በየስራ ቦታው አሸን ነው። ደግሞም ከሱ ብሶ የሚሰራውን ማናናቁ።

ደርሶ ሥራ ወዳድ የሚመስለውን ጠጋ ብለው ሲያዩት በተገላቢጦሽ ያገኙታል። ይዞት በሚዞረው መፅሀፍ ሊቅነቱ የሚለካ የሚመስለውማ አቤት ብዛቱ። ደግሞ ማስመሰሉ። ገጣሚው የምንቸገረኝ ቤት ሁልጊዜ ፋሲካ ነው ያለው ወዶ አይደለም። ዘመን ፈቅዶለት እያግበሰበሰ ያገኘውን ቁጭ ብሎ ሲቃርም፤ ወገን ተራበ ወገን ተጠማ ደንታው አይደለም። አረ እሱ እቴ። ለዚህ ሰው ጊዜ ሲጥል እንደ ጅብ እየበላ፤ እንደ ሰው የበላ ቀን እንደሚሞት ማን በነገረው።

ወዳጄ ነገርዬውን በዚህ ብንቋጨው ምን ይመስልሀል? ክርስቲያኖች «ታላቁ መፅሀፍ ቅዱስ» በማለት በሚጠሩት የእምነት መመሪያቸው ላይ እንዲህ የሚል ጥቅስ ተቀምጧል። «ባለጠጋ ከሚፀድቅ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላታል» ይህ ፅሁፍ የራሱ አውድ እና ፍቺ ቢኖረውም ከትርጉሙ መረዳት የሚያስችለን «ግመልን በመርፌ ማሾለክ» ተዓምራት ከማድረግ የማይተናነስ መሆኑን ነው። ታዲያ አንተም እኔም የማንችለው እና የማይገባን ነገር ላይ መማሰናችን፤ ሺ ግመሎችን በመርፌው ለማሾለክ ከመሞከር የማይዘል ሞኛሞኝነት መሆኑን ተረድተን ቆም ብለን ብናስብ የሚሻል አይመስልህም? (ዳግም ከበደ)

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy