በአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ከ1 ቢሊየን 25 ሚሊየን ብር በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡
በክልሉ የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት ስድስተኛው ዓመት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው ።በክልሉ የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌትነት ይርሳው ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የክልሉ ህዝብ ድጋፉን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
እስካሁንም በቦንድ ግዥ እና በስጦታ የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ከ1 ቢሊየን 25 ሚሊየን ብር በላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡በተጓዳኝም የግድቡን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች 18 ቢሊየን ብር የሚገመት የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ማከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
የክልሉ ምሁራንና የኪነጥበብ ባለሙያዎችም ህዝቡ ለግድቡ ያለውን አስተሳሰብ ወደ አንድ በማምጣትና አለም አቀፍ ጫናዎችን በመቀነስ ረገድ በሙያቸው አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አቶ ጌትነት ጠቁመዋል ።
የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት ስድስተኛ ዓመት በዓል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በፓናል ውይይት፣ በጥያቄና መልስ ውድድር፣ በስፖርታዊ ውድድሮችና በሌሎችም ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡
የፊታችን አርብ በሙሉዓለም የባህል ቡድን፣ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲና በፌደራል የግድቡ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ትብብር በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የተዘጋጀ ሙዚቃዊ ቲያትር የምረቃ ስነ ስርዓት እንደሚካሄድም ተመልክቷል፡፡