English

በአማራ ክልል ‹‹ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር›› የተሰኘ ግዙፍ ኩባንያ እየተቋቋመ ነው

By Admin

March 25, 2017

በአማራ ክልል መንግሥት፣ በክልሉ የልማት ድርጅቶችና የግል ባለሀብቶች አማካይነት ‹‹ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ግዙፍ ኩባንያ እየተቋቋመ መሆኑ ታወቀ፡፡

ከ516 በላይ በሚሆኑ የክልሉ የልማት ድርጅቶችና የግል ባለሀብቶች አማካይነት የተቋቋመው ይህ ግዙፍ አክሲዮን ማኅበር በአሁኑ ወቅት 22 ፕሮጀክቶችን ለይቶ ሥራ ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን፣ በቅርቡ የተሾሙት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ ተሻገር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይህን በክልሉ ታሪክ ትልቅ የሆነ አክሲዮን ማኅበር 25 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ የክልሉ መንግሥት የሚገዛ ሲሆን፣ 75 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በክልሉ ውስጥ ባሉ የልማት ድርጅቶችና የግል ባለሀብቶች እንደሚያዝ አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለጻ፣ በክልሉ ውስጥ የ‹ኢንዱስትሪ አብዮት› ያመጣሉ ተብለው ከተለዩ 22 ፕሮጀክቶች መካከል የብረታ ብረት ፋብሪካ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ፋብሪካ፣ የሰፋፊ እርሻ ልማት ሥራዎችና ሌሎች ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

ከእነዚህ 22 ፕሮጀክቶች መካከል የሦስቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚቀመጥ የገለጹት አቶ ደምስ፣ በባህር ዳር የሚገነባው የብረታ ብረት ፋብሪካ፣ በዓባይ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ የምሥራቅ ጎጃም ወረዳዎች መካከል በአንዱ ወረዳ የሚገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ በደብረ ብርሃንና በወልዲያ ከተሞች አካባቢዎች የሚገነቡ የእንጨት ሥራ ፋብሪካዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡ በአዋጭነት ጥናቱ መሠረት ለእነዚህ ሦስት ፋብሪካዎች ግንባታ ይውላል ተብሎ ከታሰበው 10.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ በአሁኑ ወቅት በአንድ ቢሊዮን ብር የተፈረመና የተከፈለ ካፒታል ሥራውን ለማስጀመር መታቀዱን አቶ ደምስ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ፕሮጀክቶች የሚገነቡበትን አካባቢ የመለየት ሥራ የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፣ በዋናነት ግን የክልሉን ዞኖች ያማከለ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትና ባለሀብቶች እነዚህን ለክልሉ በዓይነትና በመጠን ልዩና ግዙፍ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ሲያስቡ፣ የክልሉን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ አብዮት ለማሸጋገር ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነም አክለዋል፡፡ በሺሕ ለሚቆጠሩ የክልሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ይህ ገና ከጅምሩ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ የሚቋቋመው አክሲዮን ማኅበር ቶሎ ወደ ሥራ እንዲገባና ገብቶም ውጤታማ እንዲሆን፣ አሁን ካሉት አማካሪዎች በተጨማሪ የዓለም አቀፍ አማካሪዎችን ግዥ ለማስፈጸም ጨረታ መውጣቱን፣ በዓለም ላይ አሉ የሚባሉና ትልቅ ልምድ ያላቸው ድርጅቶች እየተወዳደሩ እንደሆነ አቶ ደምስ ተናግረዋል፡፡

አክለውም የአክሲዮን ማኅበሩን ጠቅላላ ካፒታል፣ የተሸጠውን የአክሲዮን ብዛትና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች በተመለከተ ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ይህ በክልሉ ተወላጆችና ተቆርቋሪ በሆኑ የግል ባለሀብቶች አነሳሽነት የተቋቋመው አክሲዮን ማኅበር፣ በክልሉ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አለብን በማለት ቃል የተገባበትና በአሁኑ ወቅትም አንድ ባለሀብት ከ30 ሚሊዮን እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን እየገዛ ነው፤›› ብለዋል፡፡