NEWS

በአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች ሀብት

By Admin

March 10, 2017

በአነስተኛ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እጅ ሃብት እየተፈጠረ መሄዱ ሀገሪቱ የነገ መዳረሻዋ ኢንዱስትሪ ለመሆኑ ማሳያ ነው አለ የመንግስት ኮሙኒዩኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት።

ጽህፈት ቤቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት በላከው ሳምንታዊ መግለጫ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን ውጤታማነት ከሚመሰክሩ መካከል በየዓመቱ ምርትና ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩ እነኚህ የልማት ጀግኖቻችን ናቸው ብሏል።

ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የአርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በዓል ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በደማቅ ስነሥርዓት በመከበር ላይ መሆኑም ብቁና ተወዳዳሪ አርሶ አደሮችንና ከፊል አርብቶ አደሮችን በማበረታታት ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲሸጋገሩ ማትጋት ነው ብሏል ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው፡፡

ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ወይም ጥሪት ያፈሩ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩበት ዕለት በመሆኑም በዓሉ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።

የኢፌዴሪ መንግሥት ለመላው አርሶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች እንዲሁም በስራ ትጋታቸው ተሸላሚ ለሚሆኑት ለበዓሉ እንኳን አደረሳችሁ ብሏል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላትም ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደረገውን ሽግግር ለማሳካት ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጽህፈት ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።