CURRENT

በአንዋር መስጂድ ቦምብ በመወርወር ጉዳት አድርሷል የተባለው ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት

By Admin

March 06, 2017

በ2008 ዓመተ ምህረት ታህሳስ ወር በአዲስ አበባ ታላቁ አንዋር መስጂድ ቦምብ በመወርወር በ24 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል በተባለው ተጠርጣሪ ላይ ክስ ተመሰረተ።

ተከሳሹ አህመድ ሙስጠፋ አብዶሽ የሚባል ሲሆን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኤረር ጓታ ነዋሪ ነው።

ተከሳሹ በኢፌዲሪ ህገመንግስት የተረጋገጠውን የሃይማኖት ነጻነት በመቃረን ከራሳቸው አስተሳሰብ እና አስተምሮት ውጪ እምነትና አስተምሮ መኖር የለበትም የሚል አላማ በመከተል፤ በ2007 ዓ.ም በማህበራዊ ድረ ገጽ ከተዋወቀውና ካልተያዘ ግብረአበሩ ሼህ አሊ ሃይደር ጋር “አልሃበሽን እንናጥፋ” በሚል በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በኤረር ከተማ ስምምነት መፈጸማቸውን የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ ያመለክታል።

ስምምነቱም ተከሳሽ የሃይማኖታዊ ስርአቱን የሚያከናውኑ ሰዎች ላይ ቦምብ ከወረወረ በኋላ 100 ሺህ ብር እንደሚሰጠው ያመለክታል ነው ያለው አቃቤ ህግ በክሱ።

ተከሳሽ በዚህ መልኩ የተቀበለውን ተልዕኮ ለመፈጸም በህዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም ቦምብ ይዞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኤረር ጓታ በመነሳት አዳማ በማደር ህዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም አዲስ አበባ በመግባት ለግብረአበሩ አዲስ አበባ መግባቱን የአንዋር መስጂዱን ሁኔታ አጥንቶ መጨረሱን በስልክ በመደወል ማሳወቁንም ክሱ ያስረዳል።

በክስ መዝገቡ በታህሳስ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰአት ከ15 ደቂቃ ሲሆን በታላቁ አንዋር መስጂድ በመግባት ሃይማኖታዊ ስነስርአት ሲፈጽሙ በነበሩ ሰዎች ላይ ቦምቡን መወርወሩም ነው የተጠቀሰው።

በዚህም 24 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው አድርጓል ይላል ክሱ።

ጉዳቱ ከደረሰባቸው መካከል 1ኛ አሚር መሃመድ፣ ይስሃቅ ቦዲ፣ ሸምሱ ነስሬ፣ ቶፊቅ ከድር፣ መሃመድ ሳለህ፣ መሃመድ ፋሪስ፣ መሃመድ ሙባረእና ሌሎቹንም አቃቤ ህግ በስማቸው ዘርዝሮ አቅርቧል።

በዚህም ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሹን በፈጸመው የሽብርተኝነት ደርጊት ወንጀል ክስ መስርቶበታል።

ተከሳሹ በዛሬው እለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የክስ ሰነዱ ደርሶታል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ክሱን በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከታተል፣ ፌዴራል ፖሊስም ለማረሚያ ቤት ተከሳሹን እንዲያስረክብ አዟል።

ክሱን ለመስማትም ለመጋቢት 12 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። FBC