NEWS

በአዲስ አበባ ቆሼ አካባቢ በደረሰ የቆሻሻ ተደርምሶ እስካሁን የ46 ሰዎች ህይወት አለፈ

By Admin

March 12, 2017

በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የተከመረ ቆሻሻ ተደርምሶ እስካሁን የ46 ሰዎች ህይወት አለፈ።

ማምሻውን የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በሰጡት መግለጫ የሟቾቹ ቁጥር ወደ 46 ከፍ ብሏል።

ከሟቾቹ ውስጥ 32 ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውንም ከንቲባው ገልጸዋል።

አሁን ላይ አደጋውን የመቀነስ እና ህይዎት የማዳን ስራው እንደቀጠለ ነው ብለዋል።

ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስም በአካባቢው የሚገኙትን ነዋሪዎች ራቅ ወዳለ ቦታ የማስፈር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉዳቱ ለደረሰባቸው ነዋሪዎችም የሰብዓዊና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ ነው ያሉት ከንቲባው፥ ከተማ አስተዳደሩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ህይዎት የማዳኑንና የተጎዱትን የማቋቋም ስራ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በአካባቢው ለረጅም ጊዜ ተከምሮ የነበረው ቆሻሻ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በአካባቢው በሚገኙ ቤቶች ላይ ተደርምሶ ጉዳት አድርሷል።

አደጋው ከሟቾች በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በአለርት ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።