CURRENT

በአድዋ ድል ለሁሉም ተምሣሌት የሆነ ተግባር ነው፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

By Admin

March 04, 2017

ኢትዮጵያ ከ121 አመታት በፊት ጭቆና እና የሰው ልጆች ሰብአዊ መብት ጥሰትን በመቃወም በአድዋ ላይ ያደረገችው ተጋድሎ ለሁሉም ተምሣሌት የሆነ ተግባር መሆኑን የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ገለፁ፡፡የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት 34ተኛውን መደበኛ ጉባኤ በጄኔቫ እያካሄደ ነው፡፡የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤቱ የ19 ሃገራትንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ እና አጠባበቅ ሪፖርትን አድምጧል፡፡ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት በኢትዮጵያ ባለፉት 25 አመታት  በድህነት ቅነሣ፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እመርታ እና በዜጐች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብቶች ዙሪያ ያከናወነችውን ስራዎች አብራርተዋል ለምክር ቤቱ፡፡ነገር ግን ሃገሪቱ እያስመዘገበችው ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በተለያዩ መሰናክሎች እየተፈተነ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ባለፉት ወራት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ህጋዊ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን ሽፋን በማድረግ በፀረ-ሰላም ሃይሎች የተነሳውን ሁከትና ብጥብጥ ለአብነት በማንሳት፡፡በወቅቱ ተነስቶ በነበረው ሁከት እና ግርግር የጠፋውን የሰው ህይወት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እያደረገ ስላለው ምርመራ አብራርተዋል ለምክር ቤቱ፡፡ኮሚሽኑ ሁኔታውን አጣርቶ በቅርብ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግም ወይዘሮ ሂሩት ተናግረዋል፡፡በ34ተኛው የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ጉባኤ ከ1ዐ7 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ዘገባውን ያደረሰን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ነው፡፡