CURRENT

በኢንዱስትሪ ፓርኮች አቅራቢያ የደረቅ ወደቦች ግንባታ ሊካሄድ ነው

By Admin

March 13, 2017

በኢንዱስትሪ የሚመረቱ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ውጪ ለመላክ እንዲቻል በኢንዱስትሪ ፓርኮች አቅራቢያ የደረቅ ወደቦች ግንባታ ሥራን የማስፋፋት ተግባር እንደሚያከናውን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።ደርጅቱ ለመገናኛ ብዙሃንና ለፌዴራል ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የባቦጋያ ማሪታይም ማሰልጠኛ፣ የሞጆና የገላን ደረቅ ወደቦች ተርሚናሎችን ያሉበትን ሁኔታ አስጎብኝቷል።የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ገብረሕይወት እንደተናገሩት፤ ያሉትን ሰባት የደረቅ ወደቦች ከማስፋፋት ጎን ለጎን በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢም ደረቅ ወደቦች ይገነባሉ።

እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ፤ ድርጅቱ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አቅራቢያ የደረቅ ወደብ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። በአማራ ክልል በወረታ ከተማ ሌላ የደረቅ ወደብ ለመገንባት የጥናት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል።የደረቅ ወደቦች ግንባታ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚወጡ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ውጪ ለመላክ እንደሚያስችሉ ምክትል ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ተፈራ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ኮንቴነሮች መካከል 80 በመቶውን የሚይዘው የሞጆ የደረቅ ወደብ ተርሚናል ነው። ለዚህ ተርሚናል የበለጠ አቅም ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ የማስፋፊያ ስራ እየተከናወነለት ይገኛል።የደረቅ ወደቡ ማስፋፊያ የሚከናወነው አሁን ካለው የ60 ሄክታር መሬት ስፋት ወደ 140 ሄክታር ለማድረስ መሆኑን ነው አቶ መስፍን ያስረዱት።ከጅቡቲ የሚጫኑ ኮንቴነሮችን በባቡር በማጓጓዝ ለማራገፍ የሚያስችል በስድስት ሄክታር ላይ ያረፈ የባቡር ሐዲድ ግንባታም እየተፋጠነ መሆኑን ነው የገለጹት።ለሚራገፉ ዕቃዎች ማቆያ የሚሆኑ ሁለት ትላልቅ መጋዘኖች  እየተሰሩ ሲሆን፤ በቀጣይም ሁለት እንደሚገነቡ ገልጸዋል። ምንጭ፡- ኢዜአ