Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በከተማዋ የስኳርና ዘይት ሽያጭ በኩፖን ሊካሄድ ነው

0 823

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መንግስት ለነዋሪዎች በድጎማ የሚያቀርባቸው መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ለነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል ያለውን በኩፖን የተደገፈ አዲስ የሽያጭ አሰራር ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ አዲሱ የስኳርና ዘይት ሽያጭ አሰራር ነዋሪዎች ቢሮው ባሳተማቸው 950 ሺ ኩፖኖች አማካኝነት በየአካባቢያቸው ካሉ ነጋዴዎች መግዛት የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡

የስኳር የስርጭት መዛባት እንጂ የአቅርቦት እጥረት እንደሌለ የተናገሩት አቶ ዲላሞ ፣ለነዋሪዎች የሚቀርበው ዘይት ግን ከውጭ የሚገባ በመሆኑ አልፎ አልፎ ዘግይቶ እንደሚደርስ ተናግረዋል ፡፡

«ይህን የስርጭት ችግር ለማስቀረት ብሎም ነዋሪዎች የሚገባቸውን ስኳርና ዘይት እንዲያገኙ ለማስቻል አዲስ የኩፖን፣ የስኳርና ዘይት ሽያጭ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ነዋሪዎች በየወረዳዎቻቸው ንግድና ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት አማካይነት በየአቅራቢያቸው ስኳርና ዘይት ከሚያቀርቡላቸው ነጋዴዎች የማስተሳሰሩ እና የማስተዋወቁ ምዝገባ በመካሄድ ላይ እንሚገኝ የጠቀሱት አቶ ዲላሞ፣ ለተመዘገቡት ነዋሪዎች የኩፖን ስርጭት በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ የሚካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ዲላሞ ገለጻ፤ አዲሱ አሰራር እስከ አሁን ነዋሪዎች በፈለጉት ቦታ የነዋሪነት ካርድ በማሳየት ብቻ ስኳርና ዘይት ይገዙበት የነበረውን የሽያጭ አሰራር በማስቀረት የከተማዋ ነዋሪዎች በሚኖሩበት ወረዳ ካሉ ነጋዴዎች ጋር በተወሰነ ቁጥር በመከፋፈል እንዲመደቡ በማድረግ በሚፈጠር ትስስር የሚከናወን ይሆናል፡፡

በዚህ አሰራር መሰረት አንድ የችርቻሮ ነጋዴ ስኳርና ዘይት እንዲያቀርብላቸው የተመደቡለትን የአካባቢው ነዋሪዎች ይዘውት በሚመጡ ኩፖን በመለየት ማስተናገድ ይኖርበታል፡፡ ይህም ነዋሪዎች ስኳርና ዘይት የሚያገኙበትን ሱቅ አስቀድመው እንዲያውቁ ከማድረጉም በላይ የችርቻሮ ነጋዴዎች ዘይትና ስኳር ለተመደቡላቸው ነዋሪዎች ብቻ እንዲሸጡ የሚያደርግ ነው።

በከተማዋ የስኳርና ዘይት እጥረት እንዲከሰት የሚያደርገው ግለሰቦች ለከተማዋ ነዋሪ ታስቦ የሚመጣውን ዘይትና ስኳር ለነዋሪዎች ከመሸጥ ይለቅ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በድብቅ ስለሚሸጡት እንደሆነ ነው የሚያብራሩት፡፡

ሃላፊው ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 780 ኩንታል ስኳርና ከ64 ሺ ሊትር በላይ ዘይት ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊጓጓዝ ሲል መያዙን በከተማዋ ለሚያጋጥመው የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት እንደማስረጃነት አቅርበዋል፡፡

ሃላፊው አቶ ዲላሞ ኦቶሬ አያይዘውም የደሞዝ ማስተካከያውን ተከትሎ ተፈጥሯል ስለተባለው የዋጋ ጭማሪም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ «ከደመወዝ ማስተካከያው በኋላ በቲማቲም ላይ ካጋጠመው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የዘለለ የከተማዋን የቆየ የገበያ ሁኔታ የሚያናጋ የእህል፣ ሸቀጦችና የሌሎች ምርቶች የዋጋ ንረት የለም» ብለዋል።

ሃላፊው «የአትክልት ነጋዴዎች የቲማቲም ዋጋ እንዲጨምር እንደምክንያት የሚጠቅሱት የምርት እጥረት አጋጥሟል የሚል ቢሆንም አሁን ላይ በቲማቲምና ካሮት ዋጋ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የማያስችልና ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ከእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባገኘነው መረጃ ማረጋገጥ ችለናል» ብለዋል።

አቶ ዲላሞ የደመወዘ ማስተካከያው በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አማካኝነት በኢኮኖሚው ውስጥ የተለየ የገንዘብ ፍሰት ለውጥ ስለማያመጣ በብር የመግዛት አቅም የሚያመጣው ተጽእኖ እንደማይኖር መረጋገጡንም ነው ያብራሩት። ከዚህ በተጨማሪ የደመወዝ ማስተካከያው የምርት የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል የማይችል መሆኑን በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ጥናት መረጋገጡንም አመልክተዋል።

ከደመወዝ ማስተካከያው በኋላ የቢሮው ባለሙያዎች በእህል መሸጫ ገበያዎች ላይ የገበያ ሁኔታ ቅኝት እንደሚያደርጉ የሚናገሩት የቢሮ ሃላፊው፣ በቀይ ጤፍና የሩዝ ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መታየቱንም ጠቁመዋል።

እንደ ቢሮ ሃላፊው ገለጻ፤ ቢሮው የምርት ዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስገድድ ምክንያት በሌለበት ገበያ ላይ የደመወዝ ማስተካከያውን ተከትሎ በተለያዩ ሸቀጦች፣ እና ሌሎች ምርቶች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል ባላቸው በአዲስ ከተማ፣ በንፋስ ስልክ፣በአራዳና ቦሌ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ወስዷል። (በሪሁ ብርሃነ )

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy