Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በደመወዝ ጭማሪው ባልተገባ መንገድ ለማትረፍ በሚሞክሩ ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ በመደረጉ ሳቢያ በአንዳንድ የምግብ ሸቀጦችና የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን፣ ከዚህ በኋላም ዕርምጃ እንደሚወስድ ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪዎች መታየታቸውን፣ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰድ ዚያድ ማክሰኞ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ከደመወዝ ጭማሪው ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ክፍተት በመገመት ንግድ ሚኒስቴር ቀድሞ አንድ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ሲሠራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በኮማንድ ፖስቱ የተሰበሰበው መረጃ የዋጋ ጭማሪዎችና ምርትን ሸሽጎ ማስቀመጥ በመታየታቸው፣ መንግሥት በተደራጀ መንገድ ወደ ዕርምጃ እንዲገባ እንዳስገደደውም ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

በአገር ደረጃ ያለውን የገበያ ሁኔታ መረጃ እየሰበሰበ ለውሳኔ የሚያቀርበውም ኮማንድ ፖስቱ ነው፡፡ አሁን ያለውንም ችግር በማየት ዕርምጃ የተወሰደው በንግድ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት መሆኑን ሚኒስቴር ዴኤታው አስታውሰዋል፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በንግድ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ኅብረተሰቡን በአግባቡ እያገለገሉ እንዳሉ ነጋዴዎች ሁሉ በአንፃሩ  አንዳንድ ነጋዴዎች የነፃ ገበያ መርህን እየተፃረሩ እንደሆኑና ይህንንም የማስቆም ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንግድ ሚኒስቴርና በሌሎች በሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በተደረገ የገበያ ዳሰሳ ጥናት፣ ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ተከትሎ በአንዳንድ ክልሎች መሠረታዊ ሸቀጦችና አትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ ጭምር ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱንም  ጠቁመዋል፡፡

‹‹ደመወዝ የተጨመረው በዜጎች ላይ ችግር እንዲፈጠር ሳይሆን የዜጎችንና የሸማቾችን ኑሮ ለማረጋጋት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ነገር ግን ሸማቾችን የሚያማርሩና ጫና የሚፈጥሩ፣ ፍትሐዊ ያልሆነ ዋጋ የሚወስኑ እንዳሉ በመታየቱ በተደራጀ መልክ ወደ ዕርምጃ ሊገባ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ ወቅትና ጊዜን እየጠበቁ ዋጋ የሚያንሩ መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ከመደበኛው የግብይት ሥርዓት ውጪ ምርትን በመደበቅ ገበያ  እንዳይወጣ በማድረግ ሰው ሠራሽ እጥረት እንዲፈጠር እያደረጉም ነው ተብሏል፡፡

እንዲህ ያሉ ሕገወጥ ተግባራት መቆም ስላለባቸው እስካሁን ችግር በፈጠሩት ላይ በተለያየ እርከን የተለያዩ ዕርምጃዎች ስለመወሰዳቸው ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተጨባጭ ስለተወሰዱ ዕርምጃዎች ግን ማብራሪያ አልሰጡም፡፡ ሆኖም የሚወሰዱት ዕርምጃዎች አስተዳደራዊና ሕጋዊ ተጠያቂነትን ያካተተ ስለመሆኑ፣ እንዲሁም የንግድ ፈቃድ እስከመሰረዝ እንደሚደርስ ግን ጠቁመዋል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ዋናው ሥራ ግን ግንዛቤ መስጠት እንደሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በአዲስ አበባ መሠረታዊ ፍጆታዎችንና ምርቶችን በደበቁ ላይ በአስተዳደሩ ዕርምጃ መወሰዱ በምሳሌነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ አሁንም በሕገወጦች ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ ለማጠናከር ሸማቾችም በነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  አሁን እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት በአጭር ጊዜ መፍታት እንደሚቻል እምነት እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ያልተገባ ዋጋ መስጠት አሁን በደመወዝ ጭማሪው ሰሞን የተከሰተ አለመሆኑን የሞገቱት ጋዜጠኞች፣ ችግሩ ቀድሞ የነበረ ነገር ግን ንግድ ሚኒስቴር ዕርምጃ ሳይወስድ በመቅረቱ የተባባሰ አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ችግሩ ዛሬ አንዳንዶች ሊያባብሱት የፈለጉ ቢሆንም የቆየ መሆኑን አምነዋል፡፡

‹‹እንዲያውም አጋጣሚዎችን እየጠበቁ ዋጋ የሚጨምሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፤›› በማለትም ይህንን ችግር ለዘለቄታ ለመፍታት የተለያዩ ፓኬጆችን በማውጣት ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ይህን ሊከታተሉና ዕርምጃ ሊወሰዱ የሚችሉ አደረጃጀቶች በክልሎችም እንዲፈጠሩ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም ለዚህ ሥራ የተደራጁ አካላት በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ በተገቢው መንገድ ኃላፊነታቸውን ያለመወጣት ችግር ታይቷል ብለዋል፡፡ ችግር ፈጣሪ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እየወሰዱ ለማስተካከል ክፍተቶች እንደነበሩም አምነዋል፡፡

ለሚኒስትር ዴኤታው ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የዋጋ ንረቱን ለመቀነስና ለምርቶች ያልተገባ ዋጋ ከሚሰጡ ነጋዴዎች ሸማቹን ለመታደግ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የተቋቋመው አለ በጅምላ የተባለው የንግድ ድርጅት አሁን ምን ያህል ውጤታማ ነው? የሚለው ይገኝበታል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹አለ በጅምላ በሁሉም ትልልቅ ከተሞች ሱቆችን በመክፈት በተለይ መሠረታዊ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ነው፤›› ብለዋል፡፡  ‹‹ይሁን እንጂ የዋጋ ግሽበትን በሚፈለገው ደረጃ እየተፈታ ነው ወይ? የዋጋ ጭማሪዎችን ለማስተካከል ሚናውን በሚገባ ተወጥቷል ወይ? ብለን ከጠየቅን መልሱ አልተወጣም ነው፤›› ብለዋል፡፡

አለ በጅምላ የሚጠበቀውን ያህል ለመሥራት ያልቻለው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሐሰን፣ ‹‹አንዱ ችግርም የአቅም ውስንነት ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የተደራሽነት ችግርም እንደነበር የጠቀሱት አቶ ሐሰን ከዚህ በኋላ ግን እነዚህ ችግሮችን ለመፍታትና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለው፣ አቅሙን በመገንባት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy