Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹በድንበር ምክንያት ክልሎችን እያጋጨ ያለው የእኛው አመራር ነው››

0 408

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የ2009 ዓ.ም. የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ያደረጉትን ቆይታ የተከታተለው ዮሐንስ አንበርብር በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡

ጥያቄ፡- በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ማለትም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኦሮሚና በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ ደንበሮች ጋር በተገናኘ ያልተመለሱና ለረዥም ዓመታት የሚንከባለሉ የሕዝብ ጥያቄዎች ለግጭት እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ክልሎቹ ተቀራርበው ችግሮቹን ለመፍታት ሲሞክሩ አይታይም፡፡ የፌዴራል መንግሥት እነዚህን ችግሮች እስከ መቼ ነው የሚያስታምመው?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- በጥልቅ ተሃድሶው ከተለዩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ለበርካታ ዓመታት የተንጠለጠሉ ጉዳዮችን መልክ ማስያዝ ነው፡፡ በተለይ ከወሰን መካለል ጋር የተያያዙ ለበርካታ ዓመታት የተንጠለጠሉ ጉዳዮችን መፍታት አለብን በሚለው ላይ ተስማምተናል፡፡ ለበርካታ ዓመታት የተንከባለሉበት ምክንያት ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በእኛ በኩል የነበረው ዳተኝነት ነው፡፡ ተሃድሶው ካመጣቸው ለውጦች መካከል አንዱ ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባን የደረስንበት ስምምነት ነው፡፡ እነዚህን የወሰን ጥያቄዎች ለመፍታት መጀመሪያ የአመለካከት ችግሮችን መፍታት ይገባል፡፡ የወሰን ጥያቄዎቹ እንዳይፈቱ ካደረጉት ምክንያቶች ዋናው አመለካከታችን የተበላሸ ስለነበር ነው፡፡ አሁን ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ምክንያት ችግሮቹን መፍታት አለብን፡፡ አንድ በእርግጠኝነት ልገልጽላችሁ የምፈልገው የወሰን ጥያቄ በተነሳባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኅብረተሰቦች መቼም ጊዜ ቢሆን ግጭትን ፈልገው እንደማያውቁ ነው፡፡ እየተጋጩ ያሉት ሚሊሻ ከሚሊሻ ጋር ነው፡፡ ልዩ ፖሊሲ ከልዩ ፖሊስ ጋር ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ አርብቶ አደሩንም አርሶ አደሩንም የሚገሉባቸው ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ ይኼ በግላጭ ነው የታየው፡፡ ታጣቂዎቹን የሚያዘምተው ደግሞ ታች ያለው የራሳችን አመራር ነው፡፡ ይህ ድርጊትና አመለካከት ከክልል ክልል ሊለያይ ይችላል እንጂ ነፃ ነኝ የሚል የለም፡፡ ይኼ ደግሞ የጠባብነትና ትምክህት አመለካከት የሚነዳው ነው፡፡ ጠባብነትና ትምክህት ባለበት ሁኔታ ሕዝቡ ግራ መጋባት ውስጥ ወድቋል፡፡ ስለዚህ አሁን ተሃድሷችን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይኼንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እነዚህን ችግሮች መፍታት አለብን የሚል አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው አቅጣጫ በዚህ ሒደት ውስጥ ሕዝቡን ያጋጩ፣ ደም ያፋሰሱ አካላት በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ በነፃ የሚታለፍ ነገር የለም በማለት ወስነናል፡፡ በፌዴራል መንግሥት በኩል ከዚህ አኳያ ያደረግነው አንድም መረጃ እንዳታመልጠን ነው፡፡ ማስረጃም አለን፡፡ ከክልሎቹ ጋርም የተስማማነው ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሠለፈ፣ ሰው እንዲጋጭና እንዲሞት ያደረገ አመራር ማንም ይሁን ማን በሕግ መጠየቅ እንዳለበት ነው፡፡ ይኼንን የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ እንደሚያስፈጽም ከስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ አጋጭቶና ደም አፋሶ ማምለጥ የሚባል ነገር እንደማይኖር ስምምነት አድርገናል፡፡ እነዚህ ሁለት አቅጣጫዎች በጣምራ ከተሄደባቸው አሁን ያለውን ችግር መፍታት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ችግሮቹ በባህሪያቸው የሕዝብ ሳይሆኑ የአመራር ናቸው፡፡ ጠባብነትና ትምክህት የመራው የአመራሩ የተበላሸ አመለካከት የወለዳቸው ችግሮች ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ከብሔር ጋር የሚገናኝ ችግር የለም፡፡ የሁለት የሦስት ቀበሌዎች ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ብዙ ቀበሌዎችን የሚመለከት ችግር ያለው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኞች ላይ ነው፡፡ በዚህም ቢሆን ባለኝ መረጃ 26 ቀበሌዎች ናቸው፡፡ የተቀሩት በሙሉ በሕዝብ ውሳኔ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም 26 ቀበሌዎች ውስጥ ሕዝበ ውሳኔው ባለመተግበሩ የተፈጠረ ነው፡፡ ችግሩ ሊፈታ የሚችለውም በሕዝበ ውሳኔው መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ ግጭቱ የሶማሌና የኦሮሞ ሕዝቦች አይደለም፡፡ ይኼ ግልጽ መሆን አለበት፡፡

ከቀበሌዎች ወሰን ጋር የተያያዙ አለመግባባቶችን የብሔሮች ግጭት ለማድረግና ለማወሳሰብ የሚፈልጉ አካላት እንቅስቃሴ አለ፡፡ የትግራይና የአማራ ወሰን ላይ ያሉ ነዋሪዎች ደርግን በጋራ በመፋለም በአንድ ጉድጓድ የቀበሩ ናቸው፡፡ እኛ ነን እንጂ ገብተን የምንበጣበጠው እነሱ በደንብ ይተዋወቃሉ፡፡ ወሰኑ የት እንደሆነ፣ ማን የቱ ጋ እንደሚያርስ ያውቃሉ፡፡ እውነት ለመናገር የጃርሶ ጎሳ፣ የኦሮሞ ጃርሶና የሶማሌ ጃርሶ ነው የሚባባሉት፡፡ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ ሁለት ክልሎች ቢሆኑም ሁለቱም የኦሮምኛና የሶማሌ ቋንቋዎች ይናገራሉ፡፡ አሁን ተጋጩ የሚባሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ብዙ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይኼንን የወሰን ጥያቄ ገብቶ በመበጥበጥ አጠቃላይ ፖለቲካ ለማድረግ በማወሰብሰብ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ባካሄድነው በጥልቀት መታደስ እነዚህን የመሳሰሉ የማወሳሰብ ተግባሮች ተገቢና ትክክል አለመሆናቸውንና ወደ መስመራችን እንግባ የሚል መግባባት ስለተፈጠረ፣ ችግሮቹ ይፈታሉ የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ እያጋጨ ያለው የእኛ አመራር ስለመሆኑ በግልጽ የታየ ነው፡፡

ይኼ ቋቅ የሚላቸው ሰዎች (አመራሮች) አሉ ወይ ከተባለ አዎ አሉ፡፡ ጥሩ የሚሆነው ግን (ቋቅ የሚላቸውን) ቢያስወጡት ነው፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛ አመለካከት ስላልሆነ፡፡ የትምክህትና የጠባብነት አመለካከት ቢወጣ ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ለግለሰቡም፣ ለአካባቢውም፣ ለአገራችን ልማትም በሽታ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን ችግር ፊት ለፊት ተጋፍጠን ማስተካከል አለብን፡፡ ካልሆነ ሕዝቡ ምንም በማያውቀው ጉዳይ እየተጋጨ እንዲቀጥል ነው የምንተወው፡፡ በሌላ በኩል ከኅብረተሰቡ ተወክዬ ነው የሚሉ እኛው አበል እየከፈልን የምናመላልሳቸው ጥቅም ፈላጊዎች ኅብረተሰቡ መሀል አሉ፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ገበያ የደራላቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ግጭት እስካለ ድረስ ነው አበል የሚያገኙት፡፡ በየጊዜው ምርጥ ምርጥ ሆቴሎች አሳድረን አበል እየከፈልን የምናዞራቸው ሰዎች ይኼ ግጭት እንዳይቆም ሌት ተቀን ይሠራሉ፡፡ እነዚህ አደብ መግዛት አለባቸው፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት የተወሳሰበ በመሆኑ ግጭቱ እንዳይቆም ያደርጋሉ፡፡ በመሀል ሕዝቡ እንዲሰቃይ ያደርጋሉ፡፡ ይህን መረብ በመበጣጠስ ነው ችግሩ ሊፈታ የሚችለው፡፡ እዚህ ላይ ሕዝብን የሚስቆጡ አካላትም አሉ፡፡ ልዩ ኃይሉን ተጠቅመው ሕዝቡ እንዲቆጣ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ስለዚህ ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሠረት ይፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የፌዴራል መንግሥትም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ክትትል እያደረገ ነው፡፡

ጥያቄ፡- በሪፖርትዎ የውጭ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በተሳካ መንገድ እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት በድንበር አካባቢ ትንኮሳውን እንደቀጠለ ነው፡፡ በቅርቡም በህዳሴው ግድብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያሰረገው ቡድን በፀጥታ ኃይሎች ተደምስሷል፡፡ ይሁንና በድንበር ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰላም ማግኘት አልቻሉም፡፡ ይኼንን የኤርትራ መንግሥት እኩይ ተግባር እስከ መቼ ነው ማስታመም የምንችለው? ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም አይቻልም ወይ?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲ በተከሰቱ አጋጣሚዎች የሚዘበራረቅ አይደለም፡፡ አሁንም ስትራቴጂካዊ የሆነው የሰላም ፍላጎታችን እንዳለ ነው ያለው፡፡ እኛ አካባቢው ሰላም እንዲሆን ማንኛውም ዓይነት ችግር ቢከሰትም በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎታችን የፀና ነው፡፡ የእኛ ሰላም የመፍታት ፍላጎታችን ጆሮ ሲያገኝና ፍላጎታችንን ተጋርቶ ለዚሁ ዓላማ መሥራት ሲቻል ነው ውጤት ማምጣት የምንችለው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለሰላም የዘረጋናቸው እጆች ብዙም ተቀባይነት ማግኘት ባለመቻላቸው፣ በግትርነትና በማናለብኝነት ምክንያት እስካሁን ድረስ የምንፈልገውን ውጤት ሳናገኝ ቀርተናል፡፡ በዚህ የተነሳ ለሰላም የዘረጋናቸውን እጆች ሳንሰበስብ፣ ነገር ግን ለሚፈጠሩ ማናቸውም የማተራመስ እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ ዕርምጃ የመውሰድ ፖሊሲ አስቀምጠናል፡፡ ይኼ ፖሊሲ አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ነገር ግን ከሕዝባችን ጥያቄና ግፊት የተነሳ ያስቀመጥነው የፖሊሲ አቅጣጫ ለዘለዓለም ሊቀጥል አይችልም፡፡ ስለዚህ አሁን ካለንበት ሁኔታ በመነሳት ምን ማድረግ እንዳለብን በጥናት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ማስቀመጥ ይገባናል፡፡

በድንበር አካባቢ የሚገኘው ሕዝብ የሚያነሳው ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ ይኼ ሕዝብ ለመላው የአገራችን ሰላም እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኼ ሕዝብ በከፈለው መስዋዕትነት መላው አገራችን በሰላም እንዲኖርና ተረጋግቶ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ በሁሉም ድንበሮቻቸን ላይ ያሉ ሕዝቦች ለሚወጡት ኃላፊነትና ድንበራችን ከውጭ ሰርጎ ገብ ለመጠበቅ ለሚያደርጉት ትግል ትልቅ አክብሮትና ምሥጋና እንዳለኝ ቀደም ብዬ የገለጽኩት ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በላይ የሚከፍሉት መስዋዕትነት ስላለ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን የሕዝቦች ጥያቄ መሠረት አድርገን ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝበት ፖሊሲ ማስቀመጥ እንዳለብን ግንዛቤ ተወስዶ ጥናቶች ተጠናቀዋል፡፡ ጥናቱ በሚመለከተው አካል ሲፀድቅ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይገባል፡፡  ከሁሉ በላይ ግን ወንድምና እህት የሆነው የኤርትራ ሕዝብ አካላችን እንደሆነ አውቀን ወጣቶችን፣ አዛውንቶችን፣ ሕፃናትን መታደግ አለብን፡፡ በነገራችን ላይ ማንም የማይከታተላቸው በርካታ ሕፃናት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸው አብረዋቸው የሉም፡፡ ስለዚህ ይኼ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በዋናነት በእኛ በኩል ያለው ፖሊሲ ወንድምና እህት ለሆነው የኤርትራ ሕዝብ የምንሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡

ጥያቄ፡- የተሃድሶው እንቅስቃሴ ያመጣው ውጤትና ለውጥ፣ እንዲሁም ባለፉት ስድስት ወራት ያበረከተው አስተዋጽኦ እንዴት ይገመገማል?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- የመጀመሪያውና ትልቁ ውጤት ባለፉት 15 ዓመታት ሥራ ላይ ውለው ውጤት ያመጡት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምንድን ናቸው? ብሎ መገምገም ነበር፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ውይይት በማካሄድ እንድንታደስ ረድቶናል፡፡ በአዕምሮ አስተሳሰብ እንድንታደስ አድርጎናል፡፡ ሁለተኛውና አደገኛ ሆኖ ያገኘነው የሥርዓቱ አደጋ ናቸው ተብለው የሚታዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ችለናል፡፡ ይኼ ማለት ግን እዚያም እዚህም የሚታዩ መዘናጋቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በአብዛኛው ግን ተግባብተናል፡፡ አንዱ መግባባት የተፈጠረበት ጉዳይ ብዬ የማምነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የአድልኦ ሥርዓት አይደለም በሚለው ላይ የደረስንበት መግባባት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል የፈጠረ፣ ማንም ብሔር ከማንም ብሔር የበለጠ እንዳልሆነ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች እኩል የሆኑበት ሥርዓት ነው፡፡ ሥርዓቱን ለመናድ የሚፈልጉ ኃይሎች በሚነዙት ውዥንብር የአገሪቱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የአድልኦ ሥርዓት አድርገው ለማቅረብ የሚያደርጉት ዘመቻ የተሳሳተ አመለካከት መሆኑንና በዚህም ጥርት ያለ አቋም መያዝ አንዱ የተሃድሷችን ውጤት ነው፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት ሁሉም ተጠቃሚ መሆን የሚችልበት ያስቻለ ሥርዓት ነው፡፡ በአፈጻጸም ያጋጠሙ ችግሮችን የፌዴራል ሥርዓቱ እንከኖች እንደሆኑ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩ ኃይሎች በሚነዙት የፌስቡክ ፕሮፓጋንዳ የሚናድ ሥርዓት እንዳልሆነ መግባባት ተችሏል፡፡ የጠባብነትና የትምክህት መገለጫ የሆኑ አመለካከቶች ከተሃድሶው በፊት ብቅ ብቅ ብለው ነበር፡፡ በድርጅታችንም ውስጥ ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚሠራጩ ፕሮፓጋንዳዎች ለጥፋት ሲዳርጉን የነበሩ አመለካከቶች ናቸው፡፡ እነዚህ አሁን በደረስንበት ደረጃ አጥፊ አመለካከቶች ስለመሆናቸው መግባባት ተደርሷል፡፡ ይኼንን በግላጭ የሚናገር አመራር ቁጥሩ ጨምሯል፡፡ ይኼን አመለካከት ይሸሽ የነበረ አመራር አሁን ቆሞ መናገር ጀምሯል፡፡ ትክክል አይደለም አበል ልታፍስ ነው የመጣኸው ማለት ጀምሯል፡፡ ሥርዓቱ የእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ነው ብሎ መናገር ጀምሯል፡፡

ጥያቄ፡- የመሬት ካሳ ሥርዓት ከአሥር ዓመታት በፊት የነበረ ከመሆኑና አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ቅሬታን እየፈጠረ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግርም እየሆነ ነው፡፡ መፍትሔው ምንድነው?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- የአገሮች ዕድገት በሚታይበት ጊዜ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ የከተሜነት መስፋፋት የማይቀርና የሰው ልጅ የዕድገት ደረጃን የሚያሳይ ተፈጥሯዊ ሒደት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ገጠር ያለው ነዋሪ ከተማነትን እየተላበሰ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋና መሠረተ ልማቶች እያደጉ ሲሄዱ ገጠርነትም አብሮ እየተቀየረ እንደሚሄድ፣ ከተሞች እየተቀየሩ እንደሚመጡ የማይቀር እውነት ነው፡፡ ይኼ የማይቀር ከሆነ በተለይ አርሶ አደሮቻችን እንዴት ነው መስተናገድ ያለባቸው የሚለው በጥልቀት የመታደስ ሒደቱ ወቅት ከተለዩ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ የነበሩ ጉድለቶች አንድ በአንድ እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ አንደኛ ቀድሞውንም ቢሆን የነበረው የካሳ ክፍያ በጣም ዝቅተኛ ነበረ ማለት አይቻልም፡፡ በነበረው የካሳ ምጣኔ መሠረት በአግባቡ ተከፍሎ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲሁም በአግባቡ እንዲቋቋሙ ተደግፈው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነገር ማግኘት እንችል ነበር፡፡ ጉድለታችን የነበረው የሚወሰነውን የካሳ ክፍያ ወይ መክፈል ወይም ደግሞ ጭራሹኑ አይሰጥም ነበር፡፡

አንድ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ክልል 100 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ በሚል ወስዶ ሲያበቃ ለአርብቶ አደሮቹ ግን የከፈለው ካሳ የለም፡፡ አሁን አርብቶ አደሮቹ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የወረዳ አመራርም፣ የዞን አመራርም ተቀናጅተው ከአንዳንድ ከአርብቶ አደሩ አካባቢ ከወጡ ተሰሚነን ብለው ከሚያምኑ የጎሳ መሪዎች ጋር ተመሳጥረው ካሳው ተወስዷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ደረጃው ይለያይ እንጂ በሁሉም ክልሎች ከተሃድሶው በፊት የነበረ ችግር ነው፡፡ የሚፈቀደው ካሳ በአግባቡ ስለማይከፈልና የተወሰኑት ስለሚቀራመቱት አርሶ አደሩ እንዲቆጣ አድርገዋል፡፡ አሁን ሥርዓታችንን ማሻሻል ይገባናል፡፡ የካሳ ጉዳይን የሚከታተል ራሱን የቻለ ተቋም በአዲስ አበባና በየክልሉ እንዲመሠረት እየተሠራ ነው፡፡ ሁለተኛ ካሳው ራሱ በትክክል ለአርሶ አደሩ ሊደርስ የሚችልበትን ሁኔታ የሚያመቻች የካሳ ጥናት ተጠናቋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የካሳ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የማቋቋሚያ ፓኬጅ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ፓኬጅ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ሁኔታ በተሻለ ደረጃ መቀየር ይኖርበታል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy