Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በጋራ መልማት የሚከስመው የሙርሌ ትንኮሳ

1 1,706

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጎረቤት አገር ደቡብ ሱዳን በቀጣዩ ሀምሌ ነፃነቷን የተቀዳጀችበትን ስድስተኛ ዓመት የልደት ሻማ ትለኩሳለች፡፡ ሆኖም ይሄ የልደት በአሏ በደስታ የተሞላ እንዳይሆን ዛሬም ድረስ በጎሳ ፖለቲካ ትኩሳት እየተናወጠች የሻማዋን ብርሃን ታደበዝዛለች፡፡ አስተያየት የሚሰጡ ተንታኞች እንደሚሉት ጠንካራ መሰረት ባለው ፖሊቲካዊ ስትራቴጂ ያልተመሰረተው የደቡብ ሱዳን መንግስት አገሪቱን በአግባቡ መምራት ስለተሳነው በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹ ለሞት፣ ለስደትና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው፡፡ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንዲሉ የምስራቅ አፍሪካዋ አዲስ አገር ከውስጣዊ ቀውሷ ባሻገር ለተለያዩ ኃይሎች የግል ፍላጎት ማስፈፀሚያ ስትሆንም ትታያለች፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከራሷ አልፋ ለጎረቤት አገራትም የሰላም እጦት ሰበብ እየሆነች መጥታለች፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የደረሰው በደልም የዚሁ ተግባር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከመጋቢት 1 እስከ 3 ቀን 2009 .ም ድረስ ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቀው በመግባት በተለያዩ ስፍራዎች ባደረሱት ጥቃት 18 ሰዎችን ገድለው ሌሎችንም አቁስለዋል። 30 ህጻናትን አግተው የወሰዱ ሲሆን፤ ጎጆዎችንም አቃጥለዋል።

የሙርሌ ጎሳዎች በአለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት 208 ዜጎችን መግደላቸው እንዲሁም 100 ህጻናትን አፍነው ወስደው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በጎሳዎቹ አባላት ለሚፈጸመው ጥቃት አንዱ ምክንያት የአገሪቱ አለመረጋጋትና ይህንን ማስታገስ የሚችል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ያለመኖሩ መሆኑ ይነሳል፡፡

በዚህ ሃሳብ ከሚስማሙት የፖለቲካ ምሁራን መካከል አቶ ካህሳይ ገብረየሱስ አንዱ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ አገሪቱ ምንም እንኳ ነፃነቷን ካገኘች ዓመታት ቢቆጠሩም አንድ የሚያደርጋት የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዋቅሯ የላላ ነው፡፡ ከጋራ ጉዳይ ይልቅ የግል ጥቅምን ለማስከበር የሚሯሯጡ ሃይሎች የበረከቱባት አገር እየሆነች ትገኛለች። ይህም እየበዙ ለመጡ የታጣቂ ቡድኖች እርስ በእርስ ሽኩቻ ዳርጓታል።

አንዱ ቡድን ጥቅሙ ካልተከበረለት ብሄረሰቡን አስተባብሮ በሌላው ላይ ጦር ያነሳል፤ ይዘርፋል፤ የበላይነቱን ለማሳየትም ሰዎችን ይገድላል፡፡ ይህ ዘመናትን የተሻገረው ኋላቀር አስተሳሰብና አሰራር በጋምቤላ ህዝቦች ላይ ለተከሰተው ተደጋጋሚ ጥቃት ሰበብ ሆኗል ባይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ሁለቱ አገራት ድንበር በሚጋሩት አካባቢ መሰረተ ልማት ያልተዘ ረጋበት፣ ጥቅጥቅ ጫካዎች የሚበዙበት መሆኑ ለጎሳዎች ግጭት መባባስ ምክንያት እንደሆነም ያነሳሉ፡፡

«በተለይ በኑዌርና በሙርሌ ጎሳዎች መካከል ለዘመናት ሲካሄድ የቆየው ከፍተኛ ግጭት የአገሪቱ ዜጎችን ለሞትና ለስደት ዳርጓል» የሚሉት አቶ ካህሳይ፤ ከሁለት አመት በፊት ያስተናገዱት የእርስ በእርስ ግጭት ዛሬም ድረስ ለዘለቀው አለመረጋጋት ሌላ መንስኤ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህም ደግሞ አገራቱ ከድንበርተኝነታቸው ባሻገር የጋራ ህዝቦች ያላቸው እንደመሆኑ አለመረጋጋቱ የዜጎቻቸውን ህልውና ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል የሚል እምነት አላቸው፡፡

«ደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለው አለመረጋጋት እኛን በቀጥታ እንደሚነካን ሰሞኑን የደረሰው ጥቃት አብይ ማሳያ ነው» የሚሉት የፖለቲካ ምሁሩ፤ ይህ እየታወቀ ለችግሩ መንስኤ ትናንት የተመሰረተችውንና የተረጋጋ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቅኝት የሌላትን አገር ብቻ ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢ አይደለም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ካለፈው ተመሳሳይ ክስተት ተምሮ የማያዳግም እርምጃ ተወስዷል የሚል እምነትም የላቸውም፡፡

እንደ አቶ ካህሳይ ገለፃ፤ ሁለቱ አገራት የሚዋሰኑት ረጅም ድንበር እንደመሆኑ አካባቢውን በብረት አጥር ማጠር አይቻልም፡፡ በመከላከያ ሰራዊት ብዛትም ደህንነቱን ማስጠበቅ አዳጋች ነው፡፡ ይሁንና አገራቱ በሚጋሯቸው የጋራ ህዝቦች አማካኝነት ማህበራዊ ትስስሩን የማጠናከር ስራ አለመሰራቱ፣ ጥቃት ፈፃሚዎቹ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት መረጃ እንዳይገኝና የአካባቢው ነዋሪዎችም ራሳቸውን አስቀድመው እንዳይከላከሉ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም አካባቢው ጥቅጥቅ ጫካ ያለበትና መሰረተ ልማት ያልተዘረጋበት እንደመሆኑ ሰራዊት ለማሰማራት ቢያስቸግርም፤ ጠንካራ የደህንነት መዋቅር መዘርጋት ይገባ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ «ይህ ጉዳይ በዲፕሎማሲ ወይም ደግሞ ጁባ በተቀመጠው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ብቻ የምንከታተለው አይደለም» የሚሉት አቶ ካህሳይ፤ መፍትሄው የሁለቱ አገሮች የተቀናጀ ትስስር መጠናከር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተመጣጣኝ ልማት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ በላሶ፤ በአቶ ካህሳይ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ በተለይም በአካባቢው በቂ የመሰረተ ልማት ያለመዘርጋቱ ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላ በአፋጣኝ እርምጃ እንዳይወሰድ አድርጎታል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኑሮውን ጫካ ላደረገው የሙርሌ ጎሳ ምቹ መደላደል የፈጠረለት መሆኑን በመጥቀስ፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንዳ በተለይም ከ2003 .ም ወዲህ የፌዴራል እገዛ ቦርድ በመንግስት ተቋቁሞ ነዋሪውን በመንደር የማሰባሰብ ስራ በስፋት መሰራቱን፤ በዚህም በበርካታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን አቶ ሽመልስ ይጠቅሳሉ፡፡ ከሰሞኑም ከጋምቤላ እስከ ደቡብ ሱዳኑ ዲማ ከተማ ድረስ የመንገድ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ጥናቶች ተጠናቀው በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በተጨማሪም በአኮቦ ወንዝ ላይ የድልድይ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ከቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት አንፃርም የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረው፤ «ይሁንና ከነዋሪው ቁጥር አኳያ የተሰሩት ስራዎች በቂ አይደሉም፡፡ በተለይም በድንበር አካበቢ የሚኖሩ የክልሉን ነዋሪዎች ህይወት መታደግ የሚያስችሉ ሰፋፊ የልማት ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል» ሲሉም አክለዋል፡፡

«ለተከሰተው ችግር የፕሬዚዳንት ሳልቫኪር መንግስት ብቻ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት የለኝም» የሚሉት ደግሞ በኢትዮጽያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ጥናት ኢንስቲትዩት የፀጥታ ጉዳዮች ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ አበበ አይነቴ ናቸው፡፡ በተለይም ካለፈው ክስተት ተሞክሮ በመውሰድ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቁ ረገድ ክፍተት መኖሩንም ይጠቅሳሉ፡፡ በተጨማሪም የሁለቱ አገራት የድንበር ኮሚሽን የፀጥታ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ስለመስራታቸው ሊፈተሽ እንደሚገባ በመጠቆም፡፡

አቶ አበበም ሰፊ የጋራ ድንበር ባላቸው አገራት መካከል የሚከሰቱ መሰል ችግሮች መከለካያ ሰራዊት በማቆም ይፈታሉ ብለው አያምኑም፡፡ በተለይም የደቡብ ሱዳን መንግስት በሁለት እግሩ ባልቆመበትና የአገሪቱም ዜጎች በየቀኑ በስደት በሚጎርፉበት ሁኔታ ውስጥ ወታደር አቁሞ መጠበቁ የማያስኬድ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ «ይህ ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በሁለቱ አገራት መካከል የተመሰረቱ በፀጥታና በጋራ ጉዳዮች ላይ የተቋቋሙ ኮሚሽኖችን ይበልጥ አጠናክሮ በየጊዜው ተከታተይ የሆኑ ስራዎችን በመስራት ብቻ ነው» ይላሉ፡፡

በተመሳሳይ የክልሉ መንግስት እንደ ክልል የራሱን ነዋሪዎች ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለበት በተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ ይተቻል፡፡ በተለይም ደግሞ በቅርቡ ያሰለጠናቸው ሚሊሻዎችን መሳሪያ አለማ ስታጠቁ ጥቃቱን ለመከላከል እንዳላስቻለ ይገለፃል፡፡ አቶ አበበ ደግሞ «በእርግጥ እዚያ አካባቢ የጋምቤላ መንግስት ምን ያህል እየሰራ ነው? ችግሩንስ በምን ያህል ደረጃ ለመከለካል ጥረት አድርጎ ነበር? ከአቅሙ በላይ ሆኖ ነው? ወይስ ችግሩ ዳግም አይከሰትም በሚል ተዘናግቶ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በደንብ መገምገምና መፈተሽ ይጠይቃል» ይላሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ካህሳይ ተጠይቀው «በእርግጥ የክልሉ መንግስት ፀጥታውን ለማስጠበቅ ሚሊሻዎችን ማሰልጠኑ ተገቢና የሚጠበቅ ነው፡፡ ይሁንና በክልሉ ያሉትን የአኝዋክና ኑዌር ህዝብ ግጭት ባላስቆመበት እንዲሁም በሚሊሻ ሃይሉ ላይ መተማመን ባልተፈጠረበት ሁኔታ ትጥቅ ማስታጠቁ የራሱ አደጋ አለው» ይላሉ፡፡ ይህም እዛ አካባቢ የተሰራው ህገ መንግስት የማሳወቅና ለዚህም ተገዢ የሆነ ማህበረሰብ የመፍጠር ስራ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ አመላካች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት በአሸባሪው አልሻባብ ላይ የወሰደውን እርምጃ አይነት ሊወስድ እንደሚገባ የተለያዩ አካላት ያነሳሉ፡፡ አቶ ካህሳይ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት ተጠይቀው «በሶማሊያው አልሸባብ ላይ ጠንካራ አቋምና እርምጃ መወሰዱ ተገቢና ወሳኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም በይፋ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ይዞ የተነሳ ሃይል በመሆኑ ነው፡፡ እንደ መንግስት ይህንን ማስታገስ ባይቻል ኖሮ የአገሪቱ ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባ ነበር» ይላሉ፡፡

ምንም እንኳ በሁለቱ አገራት ያጋጠሙት ችግሮች መነሻቸው የተለያየ ቢሆንም ተሞክሮ መውሰድ አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያውያን ሶማሌ ህዝቦች አማካኝነት ጠንካራ የደህንነት መዋቅር መዘርጋት መቻሉና ይህንን ተልዕኮ ይዘው በመስራታቸው ለስኬት እንዳበቃ ሁሉ በደቡብ ሱዳንም በኑዌር ህዝብ አማካኝነት የደህንነት ስራው ሊሰራ ይቻል እንደነበር በማስታወስ፡፡

በሌላ በኩልም እንደ አሻባሪ ቡድኖች በደቡብ ሱዳን ያለውን ትርምስ ተጠቅመው ኢትዮጵያን ያጠቃሉ በሚል ሰፊ ሰራዊት በአካባቢው ማስፈር ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ይሁንና የኢትጵያን ልማትና ሰለም የማይሹ ሃይሎች እንዲሁም የጥቅም ጥያቄ ያላቸው እንደ ግብፅ ያሉ አገራት ይህንን ሁኔታ እንደ ጥሩ እድል አይጠቀሙበትም ብሎ ማመን የዋህነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተለይም የግብፅ መንግስት ሰሞኑን በአካባቢው የሚያደርጋቸው ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ ማየቱ ከአንድ ጠንካራ መንግስት የሚጠበቅ ነው ባይ ናቸው፡፡

«የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ብዙ የውጭ ሃይሎች እጃቸውን ለማስገባት እድል የሚፈጥርም ነው፡፡ የኤርትራም ሆነ የግብፅ እጅም አለ፡፡ እንደ ግብፅ ያሉ አገሮች ቀዳዳ ከተፈጠረላቸው የማይተናኮሉበትና የማይተነ ኩሱበት ሁኔታ አይኖርም» በማለት የአቶ ካህሳይን ሃሳብ ያጠናከሩት አቶ አበበ ናቸው፡፡ የእነዚህንም ሃይሎች እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ማየት ይገባል ሲሉም ይመክራሉ፡፡

ምሁራኑ ይህንን ይበሉ እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ «እንደዚህ አይነት ግምታዊ ስጋቶች በጣም የተጋነኑ ናቸው» ይላሉ፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት ኢትዮጵያ የሯሷን ሉአላዊነት ማስከበር የምትችል አገር በመሆኗ፤ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም እንኳ አያሰጋትም፡፡ በራሷ በኩል የዜጎቿን ደህንነት ለማስጠበቅ የተሟላና አስተማማኝ አቅም ያላት አገር ነች፡፡

«ከዚህ አልፎ ለሚመጣው ነገር ዋናው ተጠያቂ የደቡብ ሱዳን መንግስት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሁለቱ አገራት በቅርበት እየሰሩ ሲሆን በቅርቡም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ ስምምነቶች ተደርገዋል» ይላሉ፡፡ ለአብነትም ሁለቱን አገራት የሚያገናኙ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከስምምነት ላይ መደረሱን ነው የጠቆሙት፡፡ በዲፕሎ ማሲው ረገድም በአሁኑ ወቅት የተወሰዱ ህፃናትን የማስመለሱ ጥረት በጥንቃቄ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም የደቡብ ሱዳን መንግስት በሙሉ ፍቃደኝነት ከኢትዮጽያ ጋር እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተደማጭነት በመጠቀም በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ ጫና ልታሳድር እንደሚገባት የሚሞግቱ አሉ በተለይም እንደ ሱዳን ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር በመጣመር በደቡብ ሱዳን ያለውን ውጥረት ማስታገስ እንደሚገባ ይመክራሉ፤ አቶ ካህሳይ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ «በቀጣናው ተቀባይነት ስላለን፤ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ሃይል የተሻልን ስለሆንን አካባቢያችንን መደፍጠጥ አለብን ብዬ አላምንም፡፡ ደግሞም ዲፕሎማሲ ማለት የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የህዝብ ትስስርም ጭምር እንደመሆኑ የሰላም ወዳዱን ደቡብ ሱዳናዊ መብትና ክብር ማስጠበቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የህዝቡን ጥቅም ካስጠበቅን ለእኛ አላማ የማይተባበርበትና አብሮን የማይሰራበት ምክንያት አይኖርም» ይላሉ፡፡

አቶ አበበ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ «ለኢትዮጵያ ያነጣጠረው አደጋ ለሌሎችም መትረፉ ስለማይቀር ጎረቤት አገራቱ በጋራ መስራታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም አብዛኞቹ አገራት የጋራ ድንበር ኮሚሽን አቋቁመው ሰላም አዋኪዎችን በጋራ እየታገሉ ነው የሚገኙት» በማለት ይከራከራሉ፡፡ በመሆኑንም ደቡብ ሱዳን ለቀጣናው መታወክ ሰበብ መሆንዋን እስካላቆመች ድረስ አገራቱ የጋራ አቋም ይዘው በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በማስገንዘብ፡፡

«እሾህን በሾህ» እንደሚባለው ሁሉ የደቡብ ሱዳን መንግስት ከራሱ አልፎ ለሌሎች አገራት ፀጥታ መታወክ ምክንያት እንደመሆኑ፤ ኢትዮጵያም ወታደራዊ አቅሟን ተጠቅማ ልታጠቃ እንደማይገባት አቶ ካህሳይ ይናገራሉ፡፡ «ይህ አካሄድ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ሊያዋጣ ይችላል፤ ይሁንና ሌሎች የተሻሉ አማራጮች ባሉበት ሁኔታ ወደእዚህ እርምጃ መግባቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል» ባይ ናቸው፡፡

የኤርትራ መንግስትን በማሳያነት በመጥቀስም «ሻቢያ ቀጣናውን የማተራመስ አጀንዳ ስላለው እኛም ኤርትራን በማተራመስ ብድር አልመለስንም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ነው ጥረት ያደረግነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው የሻቢያ መንግስት የቱንም ያህል ቢጥር ስኬታማ ሊሆን ያልቻለው» በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህንን መንገድ በደቡብ ሱዳኑ ጉዳይ ላይም መድገም እንደሚቻል በመጥቀስ፡፡ ይህ ማለት ግን አልፎ የሚመጣና የዜጎችን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥል ከሆነ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና ይህ ሁኔታ የመጨረሻው አማራጭ መሆን እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

«ይሄ ጉዳይ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው ባለመሆኑ አስቀድሞ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል የሚል እምነት እኔም የለኝም» የሚሉት ደግሞ አቶ አበበ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ሁለቱ አገራት በመነጋገር በአካባቢው ካሉ አስተዳደሮች በቅርበት በመስራት ችግሩን መፍታት ይቻላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በቂ ተሞክሮ መኖሩ ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡ ይሁንና ደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለው ችግር ካልተፈታ ሂደቱ አዝጋሚ ሊሆን ይችላል፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ ጉዳዩን አስመልክተው ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል። በተለይም ችግሩን ከመሰረቱ በመመርመር መንግስት የአካባቢውን የፀጥታ ጉዳይ በተመ ለከተ የሚጠበቅትን ያደርጋል፤ እንዲሁም ሁለቱን አገራት በልማት ለማስተሳሰር ይሰራል። ከዚህ አንጻርም የተጀመሩ የመንገድ፣ ህዝቡን በመንደር የማሰባሰብ እንዲሁም ለህዝቡ ጥበቃ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ጥቃቱን ያደረሱት ታጣቂዎች የትኛውንም መንግስት አይወክሉም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ችግሩን ለመፍታት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ይገልፃሉ። ደቡብ ሱዳን አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስትም በድንበር አካባቢ ያለው ጥበቃ እንዲጠናከር ቢሰሩም አሁንም ችግሮች መከሰታቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

በደቡብ ሱዳን በኩል ከአመለካከት አንጻር ስራዎች እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እና የክልሉ ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርጉ ያመለክታሉ፡፡ ትልቁ ጉዳይም አካባቢውን ማልማት በመሆኑና ችግሮች ሲፈጠሩም በቀላሉ ለመድረስ እንዲቻልም መሰረተ ልማት መሟላት እንዳለበት ይጠቁማሉ። «መንግ ስትም ለተፈጠረው ችግር አስፈላጊውን ምላሽ እየሰጠ ችግር ፈጣሪዎቹን ለህግ ያቀርባል» ብለዋል፤ በዘላቂነት ችግሩ እንዳይፈጠርና እንዳይደገም እንደሚሰራ ነው ያስገነዘቡት፡፡

እንደ አቶ ካህሳይ ገለፃ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፌዴራል ሥርዓቱ ሁሉንም የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች በተጨባጭ ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት በመኖሩ ብቻ የአገርን ደህንነት ማስጠበቅ ስለማይቻል የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ማጠናከሩ በቀጣይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከዲፕሎማሲ ስራው ጎን ለጎን ለብሄራዊ ደህነትም ለጥሩ ጉርብትናው ቀጣይነት ጠንካራ የደህንነት ስራው አስፈላጊነት ታይቶ ጥረቱ መጠናከር አለበት፡፡ በዚያ አካባቢ የሚሰራው የፖለቲካ ስራ ለሰላማችንም፣ ለመረጋጋታችንም፣ ለኢኮኖ ሚያችንም አቅም ይፈጥራል፡፡ ይህንን መስራት ካልተቻለ ግን ኢትዮጵያ ድንበር ዘለል የምትገነባው ሥርዓት ስለሌለ የግድ ፈተና ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ ብሄራዊ የደህንነት ጥቅሟም ሊጎዳ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

«አካባቢው ያልተረጋጋ፣ የመሰረተ ልማት መዋቅር የሌለውና ያልለማ በመሆኑ ለአሸባሪዎች ማሰልጠኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ለኢትዮጵያም ሆነ ለጎረቤት አገራት የስጋት ቀጣና ሊሆን ይችላል» ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የግብፅ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ እንዲሁም በቀጣናው የበላይ ሆኖ መቀጠል ስለሚሻ ይህንን አላማውን ለማሳካት እድል የሚፈጥርለት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም የተዳከመች ኢትዮጵያ እስከሌለች ድረስ ከአገሪቱ ጠላቶች ጋር በማበር በቅርበት ለማጥቃት እድል ስለሚፈጠር ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ማህሌት አብዱል

 

  1. Mulugeta Andargie says

    Guys!!! Minister Siraj Fegessa explained about the situation. Before hunting the criminals there are some other things to be done in government side. That answer is very much satisfactory!!!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy