አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
የኢትዮጵየ አየር መንገድ የተመሠረተበትን 70 ዓመት በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ አየር መንገዱ ራዕይ 2025 የተባለ የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር በመቅረፅ በፍጥነት በማደግ ላይ ነው፡፡ ዘመናዊና አዳዲስ አውሮፕላኖችን በመግዛት፣ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ተርሚናልና ባለአራት ኮከብ ሆቴል በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን አካዳሚ በ100 ሚሊዮን ዶላር ገንብቶ አስመርቋል፡፡ አየር መንገዱ ባካሄዳቸው መጠነ ሰፊ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ አየር መንገዱ የገጠሙት በርካታ ፈተናዎች አሉ፡፡ ግዙፍ ከሆኑ የመካከለኛው ምሥራቅና ሌሎች አየር መንገዶች የሚገጥመው የገበያ ፉክክር እየጠነከረ መጥቷል፡፡ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ፣ የተለያዩ አገሮች ገንዘብ ምንዛሪ ለውጥና የፖለቲካ አለመረጋጋት አየር መንገዱን ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ቃለየሱስ በቀለ በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት እያከበረ ይገኛል፡፡ አየር መንገዱ ያስመዘገባቸው ዋና ዋና ስኬቶች ምንድናቸው?
አቶ ተወልደ፡- ሰባ ዓመት ረዥም ጊዜ ነው፡፡ በእነዚህ 70 ዓመታት አየር መንገዱ በሚገባ ተደራጅቷል፣ በርካታ ስኬቶችም አስመዝግቧል፡፡ ኩባንያው ረዥም ጉዞ ተጉዟል፡፡ የመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት የምሥረታ ጊዜ ነበሩ፡፡ ትራንስ ወርልድ ኤርላይን በተባለው የአሜሪካ አየር መንገድ በመታገዝ የአየር መንገዱ መሠረት የተጣለበት ወቅት ነው፡፡ ትልቅ ዕርምጃ የተራመደው እ.ኤ.አ. በ1960 በአፍሪካ የመጀመሪያውን የጀት አውሮፕላን በረራ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ወቅት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ የመጀመሪያውን ጀት አውሮፕላን ቦይንግ ቢ720 ሲያመጣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበት ወቅት ስለነበር ታሪካዊ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ በ1980ዎቹ የመጀመሪያውን ቦይንግ ቢ767 አውሮፕላን ወደ አፍሪካ በማስገባት ቀዳሚነቱን አረጋግጧል፡፡ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ቢ767 በወቅቱ ዘመናዊ አውሮፕላን በመረከብ ከእስራኤሉ ኤልአል ቀጥሎ በዓለም ሁለተኛ ነበር፡፡ በመቀጠል በ1990ዎቹ ቦይንግ ቢ757 አውሮፕላኖች በማስገባት ቀዳሚ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 ቦይንግ 777-200LR አውሮፕላን ባለቤት በመሆን ከአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ ለመሆን ችሏል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን እ.ኤ.አ. በ2012 የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሆነውን ቢ787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በመረከብ ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ከዓለም ከጃፓን ቀጥሎ ሁለተኛ ለመሆን በቅቷል፡፡ በወቅቱ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ትልቅ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ በተጨማሪም ባለፈው ሰኔ ወር የኤርባስ አዲስ ዘመናዊ አውሮፕላን ኤ350 ወደ አፍሪካ በማምጣት ቀዳሚ ለመሆን ችሏል፡፡ አየር መንገዱ የ70 ዓመት ባለፀጋ ቢሆንም በፍጥነት ያደገው ግን ባለፉት አሥር ዓመታት ነወ፡፡ የአውሮፕላኖች ቁጥር እየጨመረ፣ የመዳረሻ አድማሱን እያሰፋና የሚያጓጉዘው መንገደኛ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችም እያካሄደ ይገኛል፡፡ የአየር መንገዱን የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር ራዕይ 2025 ባዘጋጀንበት ወቅት በርካቶች ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡ ምክንያቱም የዕድገት መርሐ ግብሩ የተጋነኑ የሚመስሉ ዕቅዶች ያቀፈ ስለሆነ ነው፡፡ በእርግጥም መርሐ ግብሩ ትልልቅ ቁጥሮች የያዘ በመሆኑ የሚያስጨንቅና ጠንክሮ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይኸው መተግበር ከጀመርን ስድስት ዓመት ተቆጥሯል፡፡ የተቀመጡትን ዕቅዶች በየዓመቱ እያሳካን ነው፡፡ ራዕይ 2025 አየር መንገዱን ወደፊት ያስወነጨፈ ትክክለኛ የዕድገት መርሐ ግብር መሆኑ እየተረጋገጠ ነው፡፡ በዚህም ባገኘነው ስኬት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበርና በሌሎች የአቪዬሽን ተቋማት የተመሰከረለት ነው፡፡
በአውሮፕላን ቁጥር፣ በመዳረሻዎች ብዛት፣ በዓመታዊ ገቢና ትርፍ እንዲሁም በመንገደኞች ቁጥር ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ነው፡፡ ዕድገቱ ያስገኘው ፋይዳ ብዙ ነው፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ የሠራተኞቻችን ቁጥር ከ4,500 ወደ 12,000 አድጓል፡፡ ባለፉት ዓመታት ከ6,000 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወንድሞችና እህቶቻችን የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል፡፡ አየር መንገዱ የአገሪቱን ወጪ ንግድ በከፍተኛ መጠን እያገዘ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያንና አፍሪካን ከሰሜንና ከደቡብ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስያና ከመካከለኛ ምሥራቅ በማገናኘት ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢኮኖሚ ኮሚሽንና ሌሎች ዓለም አቀፍና ክልላዊ ድርጅቶች ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ በመሆኗ፣ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ሲካሄዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካና በሌሎች አኅጉሮች ባሉት ሰፊ የበረራ መዳረሻ መረብ ተጠቅሞ የጉባዔ ተሳታፊዎችን ከያሉበት ያለምንም ችግር ወደ አዲስ አበባ አምጥቶ ይመልሳቸዋል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕደገት፣ ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና ንግድ መስፋፋት ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ 95 ዓለም አቀፍና 20 የአገር ውስጥ በረራ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ የ82 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ የአየር ትራንስፖርት ዕድገት ለኢኮኖሚ ልማት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ በሌሎች በርካታ አገሮች የታየ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመርቂ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡ በአጠቃላይ አየር መንገዱ በጥሩ የዕድገት ጎዳና ላይ እየተጓዘ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- አየር መንገዱ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2016 በጀት ዓመት ስላስመዘገበው የፋይናንስ አፈጻጸም ሊነገሩን ይችላሉ?
አቶ ተወልደ፡- በሰኔ 2008 ዓ.ም. በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ታሪካዊ ገቢና ትርፍ አስመዝግበናል፡፡ ወደ 55 ቢሊዮን ብር ገቢና ስድስት ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝተናል ይህ በአየር መንገዱ ታሪክ ትልቁ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ አየር መንገዱ 7.6 ሚሊዮን መንገደኞችና 270,000 ቶን ጭነት አጓጉዟል፡፡ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ገቢው በአሥር በመቶ ትርፉ ደግሞ በ70 በመቶ አድጓል፡፡ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዲስትሪ በርካታ ፈተናዎች የተከሰቱበት ዓመት ቢሆንም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ መልካም ዓመት ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በበጀት ዓመቱ የተከሰቱ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ የተለያዩ አገሮች ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ መክረዋል፡፡ ይህ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ይነገራል፡፡ በአየር መንገዱ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ አሳድሯል?
አቶ ተወልደ፡- የምንነጋገረው ስለ 2015 እስከ 2016 በጀት ዓመት ነው፡፡ በጀት ዓመቱ የተጠናቀቀው በሰኔ 2008 ዓ.ም. በመሆኑ የተከሰተው አለመረጋጋት ተፅዕኖ አላሳደረብንም፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የተከሰቱ ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች ግን ነበሩ፡፡ የነዳጅ ዋጋ በድንገት ማሽቆልቆሉ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ከነዳጅ ጋር የተቆራኘ እንደ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ካሜሩን፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቻድ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሱዳንና ግብፅ ያሉ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ በመሆኑም ለአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ያላቸው ፍላጎት ተቀዛቅዟል፡፡ የእኛም ሽያጭና ገቢ በእነዚህ አገሮች ተቀዛቅዟል፡፡
ከዚህ የበለጠው ፈተና ግን በተጠቀሱት አገሮች በነዳጅ ዋጋ መውረድ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከስቷል፡፡ በመሆኑም በእነዚህ አገሮች ገንዘብ የሸጥነውን ሽያጭ ወደ ዶላር ቀይረን ማውጣት (ወደ ኢትዮጵያ መላክ) አልቻልንም፡፡ በተለይ በናይጄሪያ፣ በአንጎላ፣ በሱዳንና በግብፅ ያለንን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ በጣም ተቸግረናል፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 220 ማሊዮን ዶላር በእነዚህ አራት የአፍሪካ አገሮች ታግቶብናል፡፡ ይህ በገንዘብ ዝውውራችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበርና የአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ማኅበር የተያዘውን ገንዘብ ለማስለቀቅ እየሞከሩ ነው፡፡ እኛም ከመንግሥታቱ ጋር በመነጋገር ላይ ነን፡፡ በየጊዜው አነስተኛ ገንዘብ ይለቁልናል፡፡ ነገር ግን በቂ አይደለም፡፡ አሁንም ትልቅ ገንዘብ ተይዞብን ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የኤምሬትስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰር ቲም ክላርክ አየር መንገዳቸው ከናይጄሪያ ገንዘቡን ማስተላለፍ ባለመቻሉ በረራችንን ልናቋርጥ እንችላለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
አቶ ተወልደ፡- እኛ እንደዚያ ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ አላሰብንም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓን አፍሪካ አየር መንገድ ነው፡፡ ናይጄሪያ ውስጥ አራት መዳረሻዎች አሉን፡፡ ሌጎስ፣ አቡጃ፣ ካኖና ኢኑጉ ከተሞች እንበራለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በናይጄሪያ ትልቅ አየር መንገድ ነው፡፡ እንደ ብሔራዊ አየር መንገድ የሚታይ ነው፡፡ ወደ ናይጄሪያ መብረር የጀመርነው ከቅኝ ግዛት እንደወጡ ነው፡፡ ባለፉት ረዥም ዓመታት በጥሩና በመጥፎ ጊዜ ሁሉ ከናይጄሪያውያን ተለይተን አናውቅም፡፡ ጊዜያዊ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ አብረን ሆነን መፍትሔ ለማበጀት እየጣርን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካዊ አየር መንገድ በመሆኑ በክፉ ጊዜ ናይጄሪያን ጥሎ አይወጣም፡፡ በረራችንንም ለመቀነስ አላሰብንም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ የተፈጠረው ሁከት ሥራችሁን አላስተጓጎለም?
አቶ ተወልደ፡- ተፅዕኖ አላሳደረም ማለት አይቻልም፡፡ አነስተኛ ተፅዕኖ አሳድሮብናል፡፡ እንደምታየው ገቢያችንና ትርፋችን አድጓል፡፡ ከእኛ መንገደኛ ፍሰት ውስጥ ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚሆነው ትራንዚት መንገደኛ ነው፡፡ በአብዛኛው በአዲስ አበባ በኩል ወደ ሌሎች አገሮች የሚጓዝ ነው እንጂ ወደ ኢትዮጵያ በቀጥታ የሚገባ አይደለም፡፡ በመሆኑም አለመረጋጋቱ የጎላ ተፅዕኖ አላሳደረብንም፡፡ ሆኖም በዚህ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በሚመጣ የመንገደኛ ቁጥር ላይ አነስተኛ ቅናሽ ተመልክተናል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ያን ያህል የጎላ ተፅዕኖ አላሳደረብንም፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ኤርባስ ኤ350 የተባለውን አዲስ አውሮፕላን አስገብታችኋል፡፡ አዲስ አውሮፕላን ሲገባ የሚፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ በኤርባስ 350 ላይ የታዩ ችግሮች ምንድናቸው?
አቶ ተወልደ፡- አውሮፕላኑን ከመቀበላችን በፊት ያደረግናቸው ዝግጅቶች አሉ፡፡ እንደ ዕድልም ሆኖ ኤ350 አውሮፕላን ያለምንም ችግር ተቀላቅሏል፡፡ አንዳንድ የተፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በጥሩ ሁኔታ ገብቶ እየሠራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቦይንግ በመሥራት ላይ ያለውን ቢ777 ኤክስና የኤርባስ አዲስ ምርት የሆነውን ኤ350-1000 አውሮፕላኖች ስትገመግሙ ቆይታችኋል፡፡ ውሳኔ ላይ አልደረሳችሁም?
አቶ ተወልደ፡- እኛ የምንገዛውን አውሮፕላን የምንመርጠው ለነደፍነው ዕቅድ ትክክለኛ አውሮፕላን የቱ ነው ብለን ነው፡፡ ካሉን አውሮፕላኖችም ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት፡፡ ለአውሮፕላኑ የቴክኖሎጂና የነዳጅ አጠቃቀም ትልቅ ቦታ እንሰጣለን፡፡ በራዕይ 2025 ለደንበኞች ምቹ፣ ነዳጅ ቆጣቢ፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ሊኖሩን እንደሚገባ አስቀምጠናል፡፡ አውሮፕላኖችን ከነዳጅ አጠቃቀምና ከጥገና አንፃር ወጪ ቆጣቢ መሆን ይገባቸዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት ቢ787 ድሪምላይነርና ኤርባስ 350 የወደፊቱ ዘመን አውሮፕላኖች እንደሚሆኑ ወስነናል፡፡ ለአየር መንገዱ ስኬታማነት የአውሮፕላኖቹ ዓይነት ወሳኝነት አለው፡፡
ከመካከለኛ አውሮፕላኖች ቦይንግ 737 ማክስን መርጠናል፡፡ ቢ777 ጥሩ አውሮፕላን ነው፡፡ የተሻሻለው ቢ777 ኤክስ አውሮፕላን በመገምገም ላይ ነን፡፡ ነገር ግን ያሉን ቢ787-8 እና በቅርቡ ያዘዝናቸው ቢ787-9 የምንፈልገውን ርቀት ሊሸፍኑልን ይችላሉ የሚለውን ማየት እንፈልጋለን፡፡ ቢ777-7 ኤክስ ትልቅ አውሮፕላን ሆኖ በጣም ረዥም ርቀት የሚጓዝ ነው፡፡ ይህ አውሮፕላን ያስፈልገናል የሚለውን ማጥናትና ትንታኔ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ሌላው ያዘገየን ምክንያት ኤርባስ A350-1000 በመሥራት ላይ በመሆናቸው በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎች እየሰጡን ነው፡፡ ይህንንም አውሮፕላን መገምገም ይኖርብናል፡፡ አሁን ያለን ኤርባስ 350-900 አውሮፕላን እንደ አዲስ ዋሽንግተን ያሉ በረራዎችን እንደሚሸፍንልን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ለሁሉም አውሮፕላኖች ፈተና የሆነው ከአዲስ አበባ ከፍታ ተነስቶ ረዥም ርቀት በረራ መሸፈን ነው፡፡ ይህን ሁሉ በዝርዝር ማጥናት ይኖርብናል፡፡ አሁን ጥናቶቹን እያጠናቀቅን ነው በቅርቡ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን፡፡
ሪፖርተር፡- ቦምባርድየር ሲ ሲሪየስና ኦምብሬር አውሮፕላኖችም እየገመገማችሁ ነው፡፡ በዚያ ላይ ምን አዲስ ነገር አለ?
አቶ ተወልደ፡- የተለያዩ አውሮፕላኖችን ስናይ ቆይተን ሲ ሲሪያስና ኢምብሬርን ለይተን አስቀርተናል፡፡ ከኤርባስና ከቦይንግም አነስተኛ አውሮፕላኖችን እያየን ነው፡፡ በሲ ሲሪየስ ወይም ኢምብሬር ለማገልገል ያሰብነው ገበያ ወደ ቢ737 ሊያድግ ይችላል የሚለውን ማየት እንፈልጋለን፡፡ ገበያውን አሳድገን በቢ737 አውሮፕላን ማስተናገድ ከቻልን ሌላ አዲስ ዓይነት አውሮፕላን መግዛት ላያስፈልገን ይችላል፡፡ አሁን ያለን ቦምባርዲየር Q400 78 መቀመጫ ያለው ነው፡፡ በመቀጠል ቢ737-800 150 መቀመጫ አለው፡፡ ቢ737 ማክስ ደግሞ 160 መቀመጫ አለው፡፡ ስለዚህ አነስተኛ ገበያዎችን ተደራሽ ለማድረግ 100 መቀመጫ ያላቸው አውሮፕላኖች ያስፈልጉናል? ወይስ ቢ737-700 (120-135 መቀመጫ ያሉት ) ማስተናገድ እንችላለን? የሚለውን ማጥናት አለብን፡፡ በቢ737 ማስተናገድ ከቻልን ሌላ አዲስ ዓይነት አውሮፕላን መግዛት ላይኖርብን ይችላል፡፡ ገበያው ግን በቢ737 መስተናገድ የማይችል ከሆነ በሲ ሲሪየስና በኢምብሬር የጀመርነውን ጥናት መቀጠል ይኖርብናል፡፡
ሪፖርተር፡- የሚትሱቡሺ (MRJ) እና ሱኮይ 100 አውሮፕላኖችንም ስታዩ ነበር፡፡
አቶ ተወልደ፡- ሚትሱቡሺ ለእኛ ትንሽ አውሮፕላን ነው፡፡ ሱኮይ ደግሞ የተለየ አዲስ ቴክኖሎጂ ስለሚሆን ከምርጫችን ውጪ አድርገናቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በሽርክና ለመሥራት ከርዋንዳ፣ ከዴሞክራቲክ ኮንጎና ከኡጋንዳ ጋር የተጀመሩ ድርድሮች አሉ፡፡ ከምን ደርሰዋል?
አቶ ተወልደ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ያስመዘገበው ስኬት የበርካታ አፍሪካ መንግሥታትን ቀልብ ስቧል፡፡ የአብረን እንሥራ ጥያቄዎች ከተለያዩ አገሮች እየቀረቡልን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደ ጥሩ አርዓያ በመቁጠር ብሔራዊ አየር መንገዶቻቸው እንደ አዲስ ለማቋቋም ወይም ያሉትን ለማጠናከር እንድናግዛቸው ወይም በሽርክና እንድንሠራ ይጠይቁናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ አሥር ያህል ፕሮጀክቶች እያየን ነው፡፡ ሩዋንዳም ከእነዚህ አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ ከዛምቢያ፣ ከዚምባቡዌ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከቦትስዋናና ከማዳጋስካር መንግሥታት ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ ከቻድ መንግሥትም ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ አሁን እየተነጋገርን ባለንበት ወቅት የናይጄሪያ መንግሥት ባቀረበልን ጥያቄ መሠረት አንድ ቡድን ወደ ናይጄሪያ ልከን በመነጋገር ላይ ይገኛል፡፡ የቀረቡልን ጥያቄዎች በርካታ በመሆናቸው እንደ ፕሮጀክቶቹ ዓይነት ቅደም ተከተል አውጥተን መሥራት አለብን፡፡ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ከኮንጎ ኤርዌይስ ጋር በመሥራት ላይ ነን፡፡ በራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብራችን ላይ አፍሪካ ውስጥ በርካታ ክልላዊ መናኸሪያዎች ሊኖሩን እንደሚገባ አስቀምጠናል፡፡ ከዚህ ውስጥ በዴሞክራቲክ ኮንጎ የመካከለኛ አፍሪካ ቀጣና መናኸሪያችንን እንደምናደርግ ወስነናል፡፡
ከሩዋንዳ አየር መንገድ ጋር በጥገናና በሥልጠና ተባብረን በመሥራት ላይ ነን፡፡ ሽርክና ለመመሥረት የጀመርነው ንግግር ግን ብዙም አልገፋም፡፡ እነርሱ በቅርቡ ኤርባስ 330 ትልቅ አውሮፕላን ገዝተዋል፡፡ በማደግ ላይ ያለ አየር መንገድ በመሆኑ በራሳቸው ለመቀጠልም የሚያስችላቸውን መንገድ እያዩ ነው፡፡ ነገር ግን ድርድሩ እንደቀጠለ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማደግ ላይ መሆኑ ብዙዎች የተስማሙበት ነጥብ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሥጋት አላቸው፡፡ አየር መንገዱ የሚያድግበት ፍጥነት ሥጋት የፈጠረባቸው ግለሰቦች አየር መንገዱ ተለጥጦ የሰው ኃይልና የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ገብቶ በሚሰጠው አገልግሎት ጥራት ላይም ችግር እንዳይፈጠር ያሳስባሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
አቶ ተወልደ፡- ይህ ተገቢ ሥጋት ነው፡፡ እውነት ነው አየር መንገዱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው፡፡ ማኔጅመንቱ ዋና ሥራው ይህን ዕድገት ማስቀጠል ነው፡፡ ማኔጅመንቱ አየር መንገዱ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲያድግ ታምኖበትና ታቅዶ የተሠራ የዕድገት መርሐ ግብር የወለደው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዝቅተኛ ደረጃ ተነስቶ በፍጥነት በማደግ ላይ ነው፡፡ ከዜሮ ስለጀመርን በፍጥነት ማደግ ይኖርብናል፡፡ ድህነትን በፍጥነት በመቅረፍ የሥራ ዕድል መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት በፍጥነት በማደግ ላይ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበርና በሌሎችም የአቪዬሽን ተቋማት መለኪያ ብትመለከት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕድገት በቀዳሚነት ተቀምጦ ታገኘዋለህ፡፡ የመጀመሪያዎቹን 60 ዓመታት ተኝተን ነበር፡፡ ማደግ የነበረብንን ያህል አላደግንም፡፡ የተወዘፈ ሥራ ነው እየሠራን ያለነው፡፡
በፍጥነት እያደግን ያለነው እኔና ባልደረቦቼ ማደግ ስለሚያስደስተን አይደለም፡፡ በአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ውስጥ የኩባንያህ መጠን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ተወዳዳሪ ለመሆን መጠን ወሳኝነት አለው፡፡ የስታር አሊያንስ ቡድን አባል ለመሆን የቻልነው በማደጋችን ነው፡፡ አለበለዚያ ዞር ብለው አያዩንም ነበር፡፡ መጠንህ በጨመረ ቁጥር የመደራደር አቅምህ ከፍ ይላል፡፡ ለአሥር አውሮፕላንና ለ30 አውሮፕላን መለዋወጫ ስታዝ ዋጋው አንድ አይሆንም፡፡ መጠንህ ሲያድግ ነጠላ የማምረቻ ወጪ ይቀንሳል፣ ተወዳዳሪም መሆን ትችላለህ፡፡
እነ ኤምሬትስ ዛሬ ቀዳሚ ሊሆኑ የቻሉት በፍጥነት በማደጋቸው ነው፡፡ እኔ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ትምህርት ቤት ተመርቄ የዛሬ 32 ዓመት ሥራ ስጀምር ዱባይ አየር መንገድ አልነበራትም፡፡ ኤምሬትስ ከተመሠረተ 31 ዓመቱ ነው ዛሬ፡፡ ያለበትን ደረጃ ተመልከት፡፡ የ220 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 70 ዓመቱ ነው፡፡ 82 አውሮፕላኖች ብቻ አሉት፡፡ ኤምሬትስ ከተመሠረተ ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመት ሲያድግ ነው የኖረው፡፡ ኤምሬትስ ከ30 ዓመት በፊት ሥራ የጀመረው ከፓኪስታን ኤርዌይስ ሦስት አውሮፕላኖች በኪራይ አምጥቶ ነበር፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሻሉ አውሮፕላኖች ነበሩት፡፡ ዛሬ ከኤምሬትስ ጋር ልዩነታችንን ተመልከት፡፡ ኢትሂድና ኳታር ኤርዌይስ ከተመሠረቱ አሥር ዓመታቸው ነው፡፡ ነገር ግን በፍጥነት እያደጉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ አየር መንገዶች ግን መንግሥታቶቻቸው ትልቅ ገንዘብ እያፈሰሱባቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡
አቶ ተወልደ፡- በእርግጥ እነርሱ ገንዘብ አላቸው፡፡ እኛ ደግሞ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለን፡፡ ተሰጥኦ ያላቸውና በሚገባ የሠለጠኑ ባለሙያዎች አሉን፡፡ በሰው ኃይላችን እንተማመናለን፡፡ ከእነዚህ ግዙፍ አየር መንገዶች ጋር ለመወዳደር በፍጥነት ካላደግን ይውጡናል፡፡ በፍጥነት ማደጋችን የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አየር መንገዱ በሚያደርገው መስፋፋት የአውሮፕላን ግዥ ትልቅ ዕዳ ውስጥ እየተዘፈቀ ነው ይባላል፡፡ ዕዳውን ለመክፈል ከማይችልበት ደረጃ እየደረሰ እንደሆነ ሥጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
አቶ ተወልደ፡- የዕዳው መጠን ከዕድገት መርሐ ግብሩ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ራዕይ 2025 ሲነደፍ አየር መንገዱን በፍጥነት ለማሳደግ የሚያስፈልጉ የአውሮፕላኖች ብዛት፣ የሰው ኃይል ቁጥርና መገንባት ያለባቸው መሠረተ ልማቶች በጥናት ተሠርተው ሰፍረዋል፡፡ ብድሩ የሚውለው በዋነኝነት ለአውሮፕላን ግዥ ነው፡፡ አውሮፕላን ጥሬ ገንዘብ ከፍለህ አትገዛም፡፡ አውሮፕላን በብድር ነው የሚዛው፡፡ ኤምሬትስም በብድር ነው የሚገዛው፡፡ ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል፣ የጥገና ማዕከላትና ባለ አራት ኮከብ ሆቴል እየገነባን ነው፡፡ ከአፍሪካ ትልቁ የሆነውን የአቪዬሽን አካዴሚ በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ገንብተናል፡፡ እነዚህ ሁሉ በብድር የሚሠሩ ናቸው፡፡ ብድር በራሱ ችግር የለውም፡፡ መክፈል እስከቻልክ ድረስ፡፡ የዕዳና ንብረት ምጣኔ ንፅፅር የአንድ ኩባንያ ጤንነት ለመመርመር ወሳኝ መሥፈርት ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕዳና ንብረት ምጣኔ ንፅፅር ሲታይ ሁለት ለአንድ ነው፡፡ ይህ በኢንዱስትሪው ጤናማ የሚባል ነው፡፡
ትርፋችን በየዓመቱ እያደገ በመምጣቱ ዕዳችንን በአግባቡ መክፈል እንችላለን፡፡ የሒሳብ መዝገባችን ጠንካራ የሚባል ነው፡፡ አውሮፕላኖች ለመግዛት ብድር ስናፈላልግ ጨረታ በምናወጣበት ወቅት ከአሥር እስከ 15 ታዋቂ ዓለም አቀፍ ባንኮች ይቀርባሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የሒሳብ መዝገባችንን ጥንካሬ ስለሚያውቁ፣ ትርፋማነታችንን ስለሚከታተሉና ጥሩ የክፍያ ታሪክ ስላለን ነው፡፡ ለጊዜው የሚያሠጋ ነገር የለም፡፡ ቀላል አይደለም ጠንክሮ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን የዕዳችን መጠን ከአቅማችን በላይ አይደለም፡፡ ዕድገት እንዲሁ አይመጣም፡፡ ተሯሩጠህ፣ ተጨንቀህ፣ ቀንና ሌሊት ደክመህ ነው፡፡ ቀለል ያለ ሕይወት ከፈለግህ፣ ዘና ያለ ሕይወት ከፈለግህ በሕይወትህ ብዙም ለውጥና ዕድገት አታገኝም፡፡
ሪፖርተር፡- አየር መንገዱ ያለበት የዕዳ መጠን ምን ያህል ነው?
አቶ ተወልደ፡- ትክክለኛው ቁጥር አሁን እጄ ላይ የለም፡፡ ነገር ግን ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ልንቆጣጠረው፣ ልንከፍለው የምንችለው ነው፡፡ ብዙም የሚያስጨንቅ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ የጀመራችሁት የአገር ውስጥ የግብርና አምራቾችን የማበረታታት ፕሮግራም አለ፡፡ የአየር መንገዱ የምግብ ዝግጅት ክፍል ለተለያዩ ግብዓቶች ግዥ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል፡፡ ከዚህ ውስጥ አሥር በመቶ ብቻ በአገር ውስጥ አምራቾች የሚቀርብ ሲሆን፣ የተቀረው ከውጪ የሚገዛ ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ ስለጀመራችሁት ጥረት ቢነግሩን?
አቶ ተወልደ፡- እንደዚህ ልንቀጥል አይገባም፡፡ ይህን ያልተመጣጠነ የንግድ ሥርዓት መቀየር አለብን፡፡ ከውጭ የምናስገባውን ምርት በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ይኖርብናል፡፡ ይህን ብናደርግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንችላለን፡፡ ሁለተኛ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንችላለን፡፡ የአገራችን የግብርና ዘርፍ በዘመናዊ መንገድ አላደገም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት የአገር ውስጥ ምርቶችን ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡ የምንፈልገውን ያህል ምርት በምንፈልገው የጥራት ደረጃ ከአገር ውስጥ ገበያ አናገኝም፡፡ ይህ ያገጠመን አንድ ፈተና ነው፡፡ ነገር ግን የማይቻል ነገር የለም፡፡ የአገር ውስጥ አምራቾችን አቅም በመገንባት ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ ይቻላል፡፡
ዝዋይ አካባቢ የሚገኙ መቂ ባቱ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ማኅበር የተወሰነ እገዛ አድርገንላቸው፣ ዛሬ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አትክልትና ፍራፍሬ እያቀረቡ ነው፡፡ ከእኛም አልፈው ኤክስፖርት እንዲያደርጉ እገዛ እያደርግንላቸው ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው የአገር ውስጥ አምራቾች ከእኛ አልፈው ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ማብቃት ነው፡፡ በዚህ ላይ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ክልል ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሠራተኞች የሥራ እርካታ ላይ ማኔጅመንታችሁ ምን ያህል እሠራ ነው? አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች ከክፍያ ጋር የተያያዘ ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ፓይለቶች ከውጭ አገር ፓይለቶች እኩል ችሎታ እያለን እነሱ የበለጠ ይከፈላቸዋል ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡
አቶ ተወልደ፡- ደመወዝ ሁልጊዜም አንፃራዊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ካየኸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች ድርጅቶች የተሻለ ክፍያ ይከፍላል፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ ካየኸው ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ነገር ግን የክፍያ መጠን እንደየአገሩ ይለያያል፡፡ አንድ ዶላር አዲስ አበባና ዱባይ ላይ ያላት የመግዛት አቅም ይለያያል፡፡ ይህንን ከግንዛቤ መክተት ያስፈልጋል፡፡ ማኔጅመንቱ ባለው አቅም የክፍያ መጠንና የሥራ ሁኔታ ለማሻሻል ይሞክራል፡፡ ክፍያ ደመወዝ ብቻ አይደለም፡፡ ማኔጅመንቱ የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተለያዩ አማራጮችን እያየ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ከደመወዝ ክፍያ በተጨማሪ የቤት፣ የሕክምና፣ የትራንስፖርት፣ የነፃ ትኬትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አሉ፡፡ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አንገብጋቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞቹ 1,200 መኖሪያ ቤቶች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የቤቶቹ ግንባታ 85 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይመረቃሉ፡፡ በሁለተኛ ዙር የቤቶች ግንባታ 7,000 የአፓርትመንት መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ዝግጅት ላይ ነን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሠራተኞቹ መኖሪያ ቤት በመገንባት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቸኛው ድርጅት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእነዚህና በሌሎች ሠራተኛው የተደላደለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችሉትን ነገሮች እያመቻቸን ነው፡፡ በፓኬጅ ካየኸው አየር መንገዱ ለሠራተኛው ከሌሎች ድርጅቶች የተሻለ ክፍያ ይከፍላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች አየር መንገዱ ለሠራተኞቹ ሕይወት መሻሻል ምን ያህል እንደሚያስብ ያሳያል፡፡ ነገር ግን ብዙ ማሻሻል ያለብን ነገሮች እንዳሉ እናምናለን፡፡
ወደ ፓይለቶች ጥያቄ ስትመጣ አየር መንገዱ አንድ ፓይለት ለማሠልጠን ወደ 100,000 ዶላር ወጪ ያወጣል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎቹን ምንም ዓይነት ክፍያ ሳያስከፍል ያሠለጥናል፡፡ በውጭው ዓለም ይህ የተለመደ አይደለም፡፡ ፓይለቶች በራሳቸው ከፍለው ሠልጥነው ነው የሚቀጠሩት፡፡ ብዙ አየር መንገዶች የማሠልጠኛ ትምህርት ቤትም የላቸውም፡፡ ፓይለቶች ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም ከገቡም በኋላ ከአንድ አውሮፕላን ዓይነት ወደሌላ አውሮፕላን ሲሸጋገሩ ከ30,000 እስከ 40,000 ዶላር ይወጣል፡፡ ይህ ሁሉ በአየር መንገዱ የሚሸፈን ነው፡፡ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው አብራሪዎቹ አሉን፡፡ እነርሱን ስንቀጥር በኮንትራት በተለየ ውል ነው፡፡ ዝርዝር ሒሳቦቹን ብናወራርድ ኢትዮጵያውያኑ ከውጭ ዜጎች አብራሪዎች ያነሰ አይከፈላቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- የበረራ አስተናጋጆችም ክፍያችን አነስተኛ ነው የሚል ቅሬታ አላቸው፡፡
አቶ ተወልደ፡- የእኔም ደመወዝ በቂ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ከኤምሬትስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቲም ክላርክ ደመወዝ ጋር ሲወዳደር ነው?
አቶ ተወልደ፡- የቲም ክላርክን ተወውና የእኔ ደመወዝ ከኬንያ ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደመወዝ ጋር ብታወዳድረው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ከውጭ አየር መንገዶች ኃላፊዎች ጋር ስገናኝ ስለደመወዝ አላወራም፡፡ ምክንያቱም አፍራለሁ፡፡ እዚህ የምሠራው ለገንዘብ አይደለም፡፡ እኛ የተሸከምነው የተለየ አገራዊ ተልዕኮ ነው፡፡ ሁላችንም አየር መንገዳችንን የማገልገል ብሔራዊ ግዴታ ነው የተጣለብን፡፡ እያገለገልን ያለነው ብሔራዊ አየር መንገዳችንን ነው፡፡ አየር መንገዳችን ሰንደቅ ዓላማችንን አንግቦ በመላው ዓለም በመብረር ብሔራዊ ኩራት የሚያጎናፅፈን፣ ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን አየር መንገድ በማገልገላችን ልንኮራ ይገባል፡፡ ለውጥ እያመጣን በመሆናችን ልንደሰት ይገባል፡፡ በእርግጥ ብዙ እንደክማለን፡፡ ቅዳሜ እሑድ ሳልል በቀን በአማካይ ከ14 እስከ 15 ሰዓት እሠራለሁ፡፡ ከቤተሰቤ ጋር የማሳልፈው በቂ ጊዜ የለኝም፡፡ የአየር መንገዱን ዕድገት ስመለከት ገንዘብ ሊያመጣው የማይችለው እርካታ ይሰማኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ረዥም ሰዓት እንደሚሠሩና ከልጆችዎ ጋር በቂ ጊዜ እንደማያሳልፉ እንሰማለን፡፡ ከቢሮ እስከ እኩለ ሌሊት እንደሚሠሩ ሰምተናል፡፡ በቂ እንቅልፍ ይተኛሉ? የጤናዎ ሁኔታ እንዴት ነው?
አቶ ተወልደ፡- ደህና ነኝ፡፡ ሥራው በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ማጋነኔ አይደለም ሙሉ ሕይወትህን የምትሰጥለት ሥራ ነው፡፡ ምን ይፈጠር ይሆን የሚል ሥጋት ሁሌም ያባንንሃል፡፡ ክፉ ዜና ከእንቅልፍህ ይቀሰቅስሃል፡፡ ጠዋት ስትነቃ የነዳጅ ዋጋ ንሮ ወይም አንዱ አገር ጦርነት ፈንድቶ እንዳደረ የሚያረዳ ዜና ይጠብቅሃል፡፡ ጦርነት ከተከፈተ የአየር ክልል ይዘጋል፡፡ ስለዚህ የበረራ አቅጣጫዎች መቀየር ይኖርብሃል፡፡ የበረራ አቅጣጫ ስትቀይር የነዳጅ ፍጆታ ይጨምራል ወጪህ ይንራል ማለት ነው፡፡ እንደ ኢቦላ፣ ሳርስ፣ ሜርስ ወይም ዚካ የመሳሰሉ ወረርሽኞች ይከሰታሉ፡፡ ይህ ሥራችንን ያወሳስብብናል፡፡ የትም አገር የሚፈጠር የፖለቲካ አለመረጋጋት በሥራችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድርብናል፡፡
የአየር ንብረት መለዋወጥ ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ አዲስ አውሮፕላን ገዝተህ ካሉህ አውሮፕላኖች ጋር ማዋሀድ ከባድ ሥራ ነው፡፡ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ፈተና ነው፡፡ ሥራችን ዕረፍት የለሽና የሚያሳቅቅ ነው፡፡ ነገር ግን አስደሳች ሥራ ነው፡፡ አሰልቺ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ስለእርስዎ የሰማነው ወሬ አለ፡፡ በቅርቡ በጡረታ ከኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ሊለቁ ነው የሚል፡፡ እውነት ነው?
አቶ ተወልደ፡- በፍጹም እንደዚያ ለማድረግ አልወሰንኩም፡፡ ያልጨረስናቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ ራዕይ 2025 መተግበር ከጀመርን ስድስት ዓመት ሆኖናል፡፡ ዘጠኝ ዓመት ይቀራል፡፡
ሪፖርተር፡- እስከ 2025 ይቀጥላሉ ማለት ነው?
አቶ ተወልደ፡- የሚቀሩን ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ አየር መንገዱ ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ነው፡፡ በጠንካራ መሠረት ላይ መቆሙን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ሙሉ በሙሉ አቅሜ ተሟጦ እስከሚደክመኝ ድረስ ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ መቼ ነው በጡረታ የምትገለለው የሚለው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ እስካሁን ግን ለመሰናበት አላሰብኩም፡፡
ሪፖርተር፡- ስለፉክክር ካነሱ ዘንዳ ከቱርክ አየር መንገድ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አየር መንገዶች የሚገጥማችሁ ፉክክር እንዴት ነው? አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አየር መንገዶች ከገበያው እየወጡ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካና የኬንያ አየር መንገዶች ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንደተዘፈቁ እየተነገረ ነው፡፡
አቶ ተወልደ፡- ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በታሪካችን አይተን የማናውቀው ፉክክር እየገጠመን ነው ያለው፡፡ ከባድ የፈተና ወቅት ላይ ነን፡፡ በተለይ በዚህ ዓመት የተለየ ፉክክር ነው የገጠመን፡፡ የጠከስካቸው አየር መንገዶች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር አፍሪካ ውስጥ የዋጋ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የትኬት ዋጋ በቀን ሁለት ጊዜ ለመቀየር እንገደዳለን፡፡ የዋጋ ጦርነት ውስጥ ገብተናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኅብረተሰቡን ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ የአፍሪካ ገበያ ደገሞ ለዚህ ዓይነት ፉክክር ዝግጁ አይደለም፡፡
እነዚህ ግዙፍ አየር መንገዶች የአፍሪካን ገበያ እየተቆጣጠሩ ነው፡፡ የሚያሳዝነው አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከአፍሪካ አየር መንገዶች ይልቅ ለውጭ አየር መንገዶች ሰማያቸውን ይከፍታሉ፡፡ የአፍሪካን ገበያ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ክፍት ያደርጋል ተብሎ የተዘጋጀው የያማሱኩሮ ስምምነት አተገባበር ዘገምተኛ በመሆኑ ተጎድተናል፡፡ አንዳንድ አገሮች ለእኛ የበረራ ፈቃድ ከልክለው ከውጭ ለመጣ አየር መንገድ ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ስለዚህ በራሳችን አቅም እየታገልን ነው፡፡ እንደምታውቀው እነዚህ አየር መንገዶች (የመካከለኛው ምሥራቅ አየር መንገዶች) ከበስተጀርባቸው ድጋፍ አላቸው፡፡ የሚያሳስበን ፉክክሩ ብቻ ሳይሆን የውድድር ሜዳው እኩል አለመሆኑ ነው፡፡ እየጎዳን ያለው ጉዳይ የምንወዳደረው በተስተካከለ ሜዳ ላይ አይደለም፡፡ እነዚህ አየር መንገዶች ትልቅ የገንዘብ አቅም አላቸው፡፡
ይሁን እንጂ እኛም ባለን የሠለጠነ የሰው ኃይል ተቋቁመንን ጠንክረን ዕድልም ተጨምሮበት ጥሩ እየሠራን ነው፡፡ የወደፊቱን ስንመለከት ብዙ ፈተና ይጠብቀናል፡፡ በፉክክር ብቻ ሳይሆን የሚፈለገውን ካፒታል ለማግኘት ችግር ሊገጥመን ይችላል፡፡ በአሜሪካ አዲስ አስተዳደር በትረ ሥልጣኑን ይዟል፡፡ በአሜሪካው ኤግዝም ባንክ አገልግሎት ላይ የሚያስተላልፈው መመርያ ምን እንደሚሆን አናውቅም፡፡ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት በአውሮፓ ክሬዲት ኤጀንሲዎች ላይ የሚያስከትለውን ለውጥ ገና አልታወቀም፡፡ ይህ ለእኛ ምን ማለት ነው? አውሮፕላን መግዣ ብድር አናገኝም ማለት ነው፡፡ ተፎካካሪዎቻችን ግን በቀላሉ ከአገራቸው የገንዘብ ምንጭ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከፊታችን ከባድ ፈተና ይጠብቀናል፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ዕግድ የተጣለባቸው የሰባት አገሮች ዜጎች ጉዳይ ያሳደረባችሁ ተፅዕኖ ምን ይመስላል?
አቶ ተወልደ፡- ዕግድ ከተጣለባቸው ሰባት አገሮች ሦስቱ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ሁለቱ ሱዳንና ሶማሊያ ጎረቤቶቻችን ናቸው፡፡ ዕግዱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፅዕኖው አልተሰማንም፡፡ ከዕግዱ በላይ ግን ተፅዕኖ ያሳደረው ግራ መጋባት ነው፡፡ ማን ወደ አሜሪካ መግባት ይችላል? ማን አይችልም የሚለው ጉዳይ በግልጽ ባለመቀመጡ ትርምስ ፈጥሯል፡፡ አሁን ደግሞ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛው ውሳኔውን አግደውታል፡፡ ነገ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም፡፡ የጉዞ ክልከላው ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዕገዳው በኋላ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ መንገደኞች ቁጥር መቀነስ ታይቷል?
አቶ ተወልደ፡- ያን ለመናገር አጭር ጊዜ ነው፡፡ በእርግጥ በመንገደኞች ቁጥር ላይ ያን ያህል የጎላ ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ መንገደኞች ከሌሎች አገሮች የሚነሱ ናቸው፡፡ የጎላ ቁጥር መቀነስ አላየንም፡፡ ነገር ግን እንደ አይኦኤም (ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት) ያሉ መሥሪያ ቤቶች ያስመዘገቡትን ጉዞ ሰርዘዋል፡፡ አይኦኤም ወደ አሜሪካ ለማጓጓዝ በግሩፕ ያስመዘገባቸውን ስደተኞች ጉዞ ሰርዟል፡፡