Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቢሮክራሲው እጁን ከመገናኛ ብዙኃን ያንሳ!

0 398

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሁን ላይ «መገናኛ ብዙኃን  አልሰራም፣ ተገቢውን ሕዝባዊ አገልግሎት አልሰጠም፣ ችግሮችንና በደሎችን ተከታትሎ አያወጣም፣ አድርባይ መገናኛ ብዙኃን ነው ያለው፣ የምርመራ ጋዜጠኝነትን መስራት አለበት፣ የመገናኛ ብዙኃን ለውጥ ያስፈልገዋል» የሚሉት ሃሳቦች ከተሀድሶው ጋር ተያይዘው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየደረጃው እስካሉ ኃላፊዎች ድረስ በሰፊው ሲደመጡ የከረሙ ተደጋጋሚ ሃሳቦች ናቸው፡፡ ይህ ማለት በመሰረታዊነት ዘርፉ እንዲለወጥ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡

ጋዜጠኛው በበኩሉ በነጻነት ለመስራት ትልቁ እንቅፋት በየቢሮክራሲው ውስጥ ተጠልለው ሚዲያውን አላንቀሳቅስ ያሉት የመረጃ ከልካዮች እንደሆነ መግለፅ ጀምሯል፡፡ መገናኛ ብዙኃን   መረጃዎችን ሚዛናዊ አድርጎ ሲጽፍ ለምን እንተቻለን፣ ለምን ስማችን ተነሳ፣መገናኛ ብዙኃን ስማችንን አጥፍቷል በሚል  የሚያፈጡም ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ እነዚህ በሕገመንግሥቱ በጸደቀው የፕሬስ ነጻነት ላይ ጦር ሰብቀው የሚወረውሩትን ለዴሞክራሲውም ሆነ ለጋዜጠኛው በነጻነት መስራት ታላቅ እንቅፋት መሆናቸውንም ሙያተኛው ራሱ  ይናገራል፡፡ እንግዲህ የዘርፉ ትግል ተጠናክሮ እየተፋፋመ ያለው በነዚህ ሁለት ኃይሎች መካከል ሆኗል፡፡

በመሰረቱ እንደአገር የተጀመረው ጥልቅ ተሀድሶም ሆነ ራሱ የህዳሴው ጉዞ  ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ሙሉ በሙሉ መከበር አለበት፡፡ በነጻነት መጻፍ፣ በነጻነት መተቸት፣ሚዛናዊና ተጨባጭ ዘገባዎች መስራት አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ለመንግሥትና ለህዝብ ዓይንና ጆሮ የሆኑ መረጃዎች እንዳይቀርቡ መሰናክል የሆኑ በመንግሥት ውስጥ ያሉ ኃይሎችን ግን  መንግሥት ሃይ ሊላቸው ይገባል፡፡ ህዝቡም በመንግሥትም ውስጥ ሆነ በራሱ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የተዛቡ አስተሳሰቦችን አጥብቆ መታገል ይኖርበታል ፡፡

አንዳንድ ፀረ ዴሞክራት የሥራ መሪዎችና በድሮ በሬ ማረስ የሚፈልጉ ኋላቀሮች የመስሪያ ቤታቸውን ጉዳይ  የሚመለከት አንዲት እንከን  በጋዜጣ ወይም በመጽሄት ታትሞ ሲወጣ ስልክ ደውለው ይዘልፋሉ፣ ያስፈራራሉ፡፡ ከዚያም አልፈው የመገናኛ ብዙኃን  እና ጋዜጠኛው ይከሰስልን የሚሉ ስለፕሬስ ነጻነት ምንነት ቅንጣትም ግንዛቤ የሌላቸውን ግለሰቦች ተሸክሞ ፈቀቅ ማለትና ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡

ለሕዳሴው ጉዞም ሆነ አሁን ለተጀመረው ተሃድሶ  የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራርና ሂደት እንቅፋቶች የሆኑ እነዚህን የመሳሰሉ አስተሳሰቦች አሁንም ብርቱ ትግልን ይሻሉ፡፡ ለውጥ እየዘመሩ በሌላ ጎኑ ለውጡን የሚወጉ ኃይሎችን ሁላችንም አምርረን መታገል አለብን፡፡ በየቦታው  የለውጥ  ሂደት አደናቃፊ ኃይሎች መቀፍቀፍ ውሎ አድሮ አገራዊ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ተረድቶ ብርቱ ትግል ማድረግ ያለበትም ራሱ መንግሥት ሊሆን ይገባል ፡፡

በእርግጥ ለሃሳብ ነፃነት መሸራረፍ የአድርባዮች ሞልቶ መትረፍረፍም   አንዱ  የለውጡ እንቅፋት ነው፡፡ በመሰረቱ በተለይ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተደቅኖበት ለቆየው አድርባይነትና ሚዛናዊነት መጓደል  የህዝቡ የኖረ አስተሳሰብም ተፅዕኖ አድርጓል፡፡  በኖሩት ሥርዓቶች ውስጥ የነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድና ውሸትም አሻራው ገና ተራግፎ አላለቀም ፡፡

በነባራዊው ዓለም ግን  መገናኛ ብዙኃን  ታላቅ ኃይል ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን  በኀብረተሰቡም ሆነ በተቋማት ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን በማስረጃ ገላልጦ የሚያሳይ መስተዋት ነው፡፡ ይሁንና የእኛን አገር ጨምሮ በበርካታ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ይህ እንዲሆን ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ሹማምንት አይፈቅዱም፡፡ የዴሞክራሲ ባሕሉና ግንዛቤው እጥረት ያለባቸውም  በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር በአገራችን አንጋፋውና ብቸኛው በየቀኑ የሚታተመው  አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሕዝብ ልሳን  እንጂ የግለሰቦችና የሹማምንት ልሳን አይደለም፡፡ ስለሕዝብ ይጽፋል፣ ይዘግባል፡፡በማስረጃ ይተቻል፡፡ ከማንም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ወይም ተቋም ጋር የግል አጀንዳ፣ የግል ጉዳይ የለውም፡፡ ስለአገር ስለሕዝብ ያለውን እውነት ይጽፋል፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ የቅርብ ጊዜ የለውጥ ጥረቶቹ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይሁንና መንግሥት ራሱና የሚመለከታቸው አካላት ቢሮክራሲው ሕጉንና ሥርዓቱን በመተላለፍ መገናኛ ብዙኃንን ጠልፎ ለመጣል የሚያደርገውን መንከላወስ ሊያስቆመው ይገባል፡፡

በመሰረቱ ጋዜጠኛው በነጻነት እንዳይሰራ፣ እንዲሸማቀቅና ምናልባትም እንዲያጎበድድ፣  የሕሊናና የመንፈስ ባሪያ እንዲሆን ጫና ለማሳደር በዚህም አንገቱን ደፍቶ ተላላኪ እንዲሆን የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፡፡ ይህን ህግ የማይፈቅደውን ተግባር ብሎም  የሙሰኞችና የኪራይ ሰብሳቢዎችን አካሄድ  ከእንግዲህ መሸከም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

በእነሱ እምነት ጋዜጠኛው ውዳሴ ዜማ እያሰማ ከበሮ እየደለቀ ምናልባትም እያሸበሸበ ‹‹ሥራችሁ ሁሉ ያማረና የተዋበ ነው እንከን አልባ ናችሁ›› እያለ እንዲያሞካሻቸው የሚሹ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ለምን ተነካን የሹም ዶሮ ነን የሚባልበት ጊዜ ማለፉን አላወቁ ከሆነም አልሰሜን ግባ በለው ማለቱ ይቀላል፡፡

ጋዜጠኛው እንደባለሙያ ሊያስጨንቀው የሚገባው በሙያው መርሆ፣ በአገሪቱ ህግና የሞራል ግዴታዎች ላይ ተመስርቶ ስለመስራት ብቻ መሆን አለበት፡፡ በተለይ በመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 መሰረት ብቻና ብቻ ሥራዎች መሰራታቸው ከተረጋገጠ ከበቂ በላይ  ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ዘገባ እገሌን ያስከፋል ወይም ያስደስታል ወደሚል አድሎአዊ ውዝግብ ውስጥ ከገባ ያለጥርጥር የህዝብን ጥቅም አሳልፎ ይሰጣል፡፡አገሪቱ ለጀመረችው ጥረትም አንዳች አስተዋፅኦ ሊኖረው አይችልም፡፡

ስለሆነም የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኛው ለሕዝብ ጥቅም መከበር በደል፣ ብሶት፣ ቅሬታ፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት አለ በተባለበት  ጥቆማ በደረሰው  ቦታ ሁሉ መገኘት አለበት፡፡ ማስረጃ እንሰበስባለን፣ ስሕተት እንዳይፈጠርም ግራና ቀኙን እናጣራለን፣ ቃለመጠይቅ እናደርጋለን፣ በመጨረሻም አትመን ሕዝብና መንግሥት እንዲያውቀው እናደርጋለን የሚል ሙሉ እምነት መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ለምን ይህንን አደረጋችሁ የሚል አካል  ከመጣ በሕጉና በደንቡ መሰረት መልስ እንሰጣለን፡፡

ከዚህ አንፃር ለማንም ቢሆን ካለጥፋቱ የመገናኛ ብዙኃንና  ጋዜጠኛውን እየከሰሱ ሥራ ከማስፈታት ቀድሞ ሥራን በንጹህ እጅ መስራት ተገቢ መሆኑን ልናሰምርበት እንወዳለን፡፡ ሕዝብ መረጃ የማግኘት ስለመሪዎቹም ሥራና ተግባር ጭምር የማወቅ መብትም ሆነ ነጻነት አለው፡፡ ሽፍንፍን እና ድብቅ አሰራር ከእንግዲህ የትም አያደርሱም፡፡ ተቋማት ሁሉ አሰራራቸውን በግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ላይ ተመርኩዘው መስራት እንዳለባቸው ጥልቁ ተሀድሶ አስምሮበታል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኛው በተገቢው ማስረጃ ተደግፎ ሚዛናዊ ሆኖ ሕግና ስርዓቱን አክብሮ ሙሰኞችን የመልካም አስተዳደር ጠንቆችን በአገርና በሕዝብ ሀብት ሲያላግጡ የኖሩትን፤ በየመስሪያ ቤቱ በየቢሮው አድብተው የሚቦጠቡጡትን በማስረጃ እየተከላከለ ማጋለጡን ለሕዝብ ማሳወቁን ይቀጥላል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኛውን በመክሰስ፣ በማሳደድ፣ በማሸማቀቅ፣ እንዳይሰራ ሞራሉን ለማላሸቅ እጃቸውን የሚወነጨፉትን በጋራ መታገል ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም ሙያው ጠንካራ አደረጃጀትና ህብረት ስለሌለው እንጂ የሕዝብን ጥቅም የሚጻረሩ፣ የጥቅመኞችን ሴራ የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኛው ዳር እስከዳር በአንድነት በመቆም ያመክነው እንደነበር አምናለሁ፡፡ አሁንም ከመንግሥትም ጋር በመሆን ለእውነት ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም መከበር ጸንቶ በመቆም ሙያውን የመታደግ ኃላፊነት የሁላችንም እንደሆነ እየተገነዘብን መጥተናል ፡፡

ስማችን ተነካ ለምን ተጻፈብን፣ ለምን ተዘገበ የሚሉ ወገኖች ቁስላቸው ሲነካ መጮሃቸውና መወራጨታቸው ድሮም ዘንድሮም የተለመደ በመሆኑ እንግዳ ነገር የለውም፡፡ ስማቸውን ሥራቸው ላይ ይፈልጉት፡፡ ለክስ ፍርድ ቤት ከመሄድ በመገናኛ ብዙኃን እና በመረጃ ነጻነት ሕጉ መሰረት በዚያው ጉዳዩ በወጣበት ጋዜጣ ወይም መጽሔት ላይ በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡

ከዚህ አልፎ ለክስ ፋይል መክፈቱ አገሪቷ በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የከፈተችውን ትግል ለማኮላሸት እንዲሁም መገናኛ ብዙኃንን አንገት ለማስደፋት የተጠነሰሰ የቢሮክራሲው ሴራ ስለሆነ ቢሮክራሲው በመገናኛ ብዙኃን ላይ የከፈተውን እኩይ ዘመቻ ሊያቆመው ይገባል፡፡

እጃችን ላይ የገቡትን መንግሥትና አገርን ጉድ የሚያሰኙ የተለያዩ ተቋማትን ጸያፍና ነውረኛ ሥራዎች የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢዎች ዘረፋና ብልሹ አሰራር በየደረጃው ማጋለጡ የሚቀጥል ሲሆን ይህ ታላቅ ኃላፊነትና የሙያ ግዴታ  የወደቀው በመገናኛ ብዙኃን ላይ መሆኑን ሁሉም ወገን ልብ ሊለው ይገባል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞችን በመክሰስ የተሃድሶውን ሂደትና ዴሞክራሲያዊ ትግሉን ማደናቀፍ አይቻልም፡፡ መንግሥትም ሆነ የመንግሥት አካላት ሕዝቡም በሕገመንግሥቱ የጸደቀው የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ የፕሬስ ነጻነት ለዘለአለም ይኑር !! መሐመድ አማን

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy