English

ባለፈው አመት ከ30 ሚ. ዶላር በላይ ያፈሩ 20 አዳዲስ ሚሊየነሮች ተፈጥረዋል

By Admin

March 11, 2017

በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ከ30 ሚ. ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው 20 አዳዲስ እጅግ ባለጸጋ ሚሊየነሮች መፈጠራቸውን “ናይት ፍራንክ” የተባለ አለማቀፍ የሃብት ጥናትና አማካሪ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው የ2017 አለማቀፍ የሃብት ስርጭት አመታዊ ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነው ተቋሙ፤ በ89 የአለማችን አገራት ውስጥ በሚገኙ 125 ከተሞች ላይ ያደረገውን ጥናት መሰረት በማድረግ፣ ለ11ኛ ጊዜ ባወጣው ሪፖርቱ፤ በአዲስ አበባ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው አዳዲስ ሚሊየነሮች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው በ10 በመቶ በማደግ፣ በ2016 አመት 20 መድረሱን የጠቆመ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በመጪዎቹ ዘጠኝ አመታት በእጥፍ በማደግ 40 ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016፣ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ሰዎች ቁጥር 800 መድረሱን የገለጸው ሪፖርቱ፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ሚሊየነሮች ቁጥር ደግሞ 40 ደርሷል ብሏል፡፡ ሪፖርቱ በአፍሪካ አህጉር በመጪዎቹ ዘጠኝ አመታት ከፍተኛ የሚሊየነሮች ቁጥር እድገት ይመዘገብባቸዋል ብሎ የጠቀሳቸው አገራት፡- ኢትዮጵያ፣ ሞሪሽየስ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ሲሆኑ፣ በመላው አለም ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ሰዎች ቁጥር በዘጠኝ አመታት ጊዜ ውስጥ በ43 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 በመላው አለም ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው 6 ሺህ 340 አዳዲስ ሚሊየነሮች መፈጠራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህን ያህል የሃብት መጠን ያላቸው የአለማችን ሚሊየነሮች አጠቃላይ ቁጥር 193 ሺህ 490 መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡ በሚሊየነሮች ቁጥር ከአለማችን አገራት ከፍተኛውን ጭማሪ ታስመዘግባለች ተብላ የምትጠበቀው ቬትናም ስትሆን፣ በአገሪቱ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ዜጎች ቁጥር በዘጠኝ አመታት ጊዜ ውስጥ በ170 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመትም ተነግሯል፡፡ admas