Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተቋማት ሆይ መዝገቡን ግለጡ፤ ሳጥኑንም ክ…ፈ…ቱ!

0 676

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እርሶ፤ ከዓመታት የባህር ማዶ ቆይታ በኋላ ወደ ትውልድ ቀዬዎ ተመልሰው በባዕድ ምድር ያፈሩትን ጥሪት በኢንቨስትመንት ለማፍሰስ የተዘጋጁ አገር ወዳድ ‹‹ዳያስፖራ›› ነዎት እንበል፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖርዎት ቆይታና መርሃግብር በጣም የተጣበበና በጊዜ የተሰፈረ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም የሚባክን ደቂቃ እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ በዚህ ቁርጠኝነት ተሞልተው ስራዎችን ዛሬ ለመጀመር መንደርደር ይዘዋል፡፡ ለመፈፀም የሚጓጉትን ቁልፍ ጉዳይ በዚህች እለት ማሳካት ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ሆኖበታል፡፡

ሂደቱን ለማቀለጣጠፍ ወደሚችሉበት አንድ መንግስታዊ ተቋም መክነፍ ጀምረዋል፡፡ ከቅጥሩ መዝለቂያ በቂ ፍተሻ ተደርጎሎዎት ያልፋሉ፡፡ በመቀጠል ስለመጡበት አላማ የሚያብራሩለትን ሰው ቢሮ ለማወቅ ወደ መረጃ ክፍል ጎራ ይላሉ፡፡ ‹‹ቀጠሮ አለዎት?›› የመጀመሪያው ጥያቄ፤ ‹‹አዎ›› ይላሉ፤ ‹‹ቆይ ደውዬ ላረጋግጥ›› ቀጣዩ ምላሽ ይሆናል፡፡ ይጠብቃሉ፤ ደቂቃዎች ነጎዱ፡፡

እዚህች ጋር ትዕግስቶት መፈተን ይጀምራል፡፡ ምክንያቱም ምናልባት እርሶ የሚያውቁት በባለጉዳይ እና በጉዳይ ፈፃሚ መካከል ቀጥተኛ የሆነ የግንኙነት መስመር መኖሩን ይሆናል፡፡ ስለዚህ የመረጃ ሰጪዋ ምላሽ ግራ ቢያጋባዎት አይፈረድም፡፡ ከአሎት ጠባብ ጊዜ አንፃር የደቂቃዎች ሽርፍራፊ ሳትቀር ዋጋ እንዳላት ስለሚረዱ ይቁነጠነጣሉ፡፡ አምስቱ ደቂቃ 50 ደቂቃ ሊሆንብዎትም ይችላል፡፡ ሰዓቶትን በተደጋጋሚ ይመለከታሉ፡፡

የመረጃ ባለሙያዋ እርሶን አቁማ አብሯት የሚሰራውን ሰው በስልክ ወግ ጠምዳለች፡፡ የዛሬ ዓመት ያገኘችው እስኪመስል ድረስ ‹‹እንዴት ነህ ታዲያ? ያልከኝ ነገር ተሳካልህ?›› ትለዋለች፡፡ እርሱ ዘንድ ስልክ ለመደወል የተፈጠረው አጋጣሚ ያስደሰታት ትመስላለች፡፡ በመጨረሻም ስልኩን ዘግታ ቀና በማለት ‹‹ትንሽ ይጠብቋቸው፤ ስብሰባ ሊገቡ ነው›› የሚል አቃጣይ መልስ ትሰጣለች፡፡ ‹‹ኡ…ፍ…ፍ…!!!›› ይበሽቃሉ፡፡ መረጃ ሰጪዋ ምንም እንዳልተፈጠረ እርሶን ትታ ከጎኗ ከተቀመጠ ባልደረባዋ ጋር የደራ ወግ ትጀምራለች፡፡ ይሄ ደግሞ ይበልጥ ያናድዶታል፤ ግን ይችሉታል፡፡

‹‹ከስብሰባ ስንት ሰዓት ይወጣሉ?›› ይጠይቃሉ፡፡ የሴትየዋ መልስ ፈጣንና አጭር ነበር፡፡ ‹‹አልነገ ሩኝም›› የሚል፡፡ በውስጥዎት እንዲያ ያለው ቤተሰባዊ ወግ ላይ ቆይታ የስብሰባውን ማብቂያ ሳትጠይቅ መዝጋቷ ይገርሞታል፡፡ ከመግረምም አልፎ ዳግም ያናድዶታል፡፡ ሰዓቱ እየበረረ ነው፡፡ ለመሄድ በመወሰን እና በመቆየት መካከል ሆነው ሲያመነቱ ስብሰባ ማለቁ ከመረጃ ክፍሉ ባለሙያዎች ይነገሮታል፡፡

ይገባሉ፡፡ ቢሮ ውስጥ ባገኟቸው የስራ ኃላፊ የእንግዳ አቀባበል ግን ግራ ይጋባሉ፡፡ ለካስ ሰውዬው እርሶን ከማግኘታቸው በፊት በነበረው ስብሰባ ምክንያት ትንሽ በስጨት ብለዋል፡፡ ገብተው ገና እጅ ከመንሳትዎ፤ የስራ ኃላፊው በዚያው ስሜት ውስጥ እንዳሉ ‹‹በሚቀጥለው ሳምንት ብቅ በል!›› ሲሎት ሌላ ድንጋጤ፡፡ ሲጣደፉ የመጡበት ጉዳይ ፍሬ ሳያፈራ በገቡበት በር መልሰው ይወጣሉ፡፡ እንግዲህ ከአሎት አጭር ጊዜ ላይ ግማሽ ቀን ተቃጠለ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሊወጡ ሲሉ በሩ ላይ አንድ ትልቅ መዝገብና መለስተኛ ሳጥን ይመለከታሉ፡፡

እያመነቱ መዝገቡ ጋር ይደርሳሉ፡፡ ይገልጡታል፡፡ መተንፈሻ ስላገኙ በተወሰነ ደረጃ ደስ አሰኝቶታል፡፡ ብዕሮትን ያሾሉና ረጅም የብሶት አስተያየትዎን ካሰፈሩ በኋላ ‹‹…እባካችሁ አሰራራችሁን አሻሽሉ! ራሳችሁን ፈትሹ! ባለጉዳይን በቀጠሮ አታሰልቹ!›› በማለት ይደመድማሉ፡፡ የመዝገቡ አልበቃ ብሎት፤ ተመሳሳይ አስተያየቶትን በብጣሽ ወረቀት ያሰፍሩና ጠቅልለው በሳጥኑ ያሾልኩታል፡፡ ከዚያም ተቋሙ አስተያየቱን ያነብና በቀጣይ ተገቢውን የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ያመጣል የሚል ተስፋ ሰንቀው ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ በእርግጠኝነት ግን ሳጥኑ ስለመከፈቱ ሊያረጋግጡ የሚችሉበት መንገድ የሎትም፡፡

በአገራችን ይሄ ችግር ዓመታት የተሻገረ ነው፡፡ የተለያዩ ተቋማት (የመንግስትም ሆነ የግል) በቅጥራቸው መዝለቂያ ወይም በቢሯቸው ጥግ እንደነገሩ የሚያስቀምጡት አንድ ሳጥን በአግባቡ ቢጠቀሙበት ፋይዳው የላቀ ነበር፡፡ የተገልጋዮቻቸውን የአገልግሎት እርካታ በእውነት ላይ ተመስርቶ በሚሰጥ አስተያየትና ግብረ መልስ የለውጥ ማምጫ መንገድ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በአብዛኞቹ ተቋማት ዘንድ የአስተያየት መስጫ ሳጥን እንዲሁም ብዕርና ዳጎስ ያለ መዝገብ ማስቀመጡ የተለመደ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ግን ምን ያህሎቹ ተቋማት አስተያየቶቹን ተከታትለው የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ያሻሽላሉ? የሚለው ነው፡፡ ሳጥኖቹንም ሆነ መዝገቦቹን ገልጦ ‹‹ችግሬ ምንድን ነው?›› በማለት ለመልሱ የሚጨነቁ ተቋማት ብዙም አይደሉም፡፡

የተቋማት የአስተያየት መቀበያ መንገድ በኢትዮጵያ መቼ እንደተጀመረ በግልፅ የሚያስቀምጥ መረጃ ፍለጋ ሰነድ ባገላብጥም ምንም አላገኘሁም፡፡ ለነገሩ በአገራችን አልኩ እንጂ የአስተያየት መስጫ ሳጥን የት እና መቼ ተጀመረ? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ የሚያረካ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ነገር ግን ሳገላብጥ ያገኘኋቸው አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአስተያየት መስጫ ሳጥን አገልግሎት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አንድ ምዕተ ዓመት አልፎታል፡፡ ይኸውም እ..1909 መጀመሪያ አካባቢ በአሜሪካ ሲያትል በሚገኝ አንድ ፋብሪካ መሆኑን ነው፡፡

እንደሚባለው ከሆነ በበለጸጉት አገሮች (ሄጄ ባላረጋግጥም) የአስተያየት መስጫ ሳጥን የቀጣይ አገልግሎት ማቀላጠፊያ ቁልፍ መሣሪያቸው ነው፡፡ በተለይም እንዲህ በአለው አስተያየት መቀበያ ደንበኞች በሚሰጣቸው መስተንግዶ ልክ እርካታቸውንም ሆነ ወቀሳቸውን ገለልተኛና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንደሚያሰፍሩ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ተቋሙን ለመጉዳት ብቻ በማሰብ የማይታይበትን ችግር ከመስጠት ተቆጥበው በእውነተኛው (በሚገነባው) ጉዳይ ላይ ያተኩራሉ፡፡

ብልሆቹ ተቋማት ይሄን አጋጣሚ ‹‹ተከድኖ ይብሰል!›› ብሎ ማለፍን አይመርጡም፡፡ ይልቁኑም በሚገባ ይመረምሩታል፡፡ ጎዶሎ ጎናቸውን ይመለከቱ በታል፡፡ ጠንካራውን አስጠብቀው ደካማውን ይቀርፉበታል፡፡ ከዚያም አልፈው በዓመቱ መጨረሻ የአገልግሎት አሰጣጥ ዓመታዊ አፈጻጸማቸውን የሚፈትሽ መለስተኛ ጥናት ያደርጋሉ፡፡ ታዲያ ከዚህ የተሻለ መልካም አጋጣሚ እንዴትና ከየት ሊያገኙ ይችላሉ? ከዚህ በመነሳትም በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች እንደሚያብራሩት አስተያየት መቀበያ ሳጥን በስራ ቦታ ማስቀመጥ የተለያዩ ጥቅሞች አሉት፡፡

የመጀመሪያው ጥቅም በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ወይም በመዝገቡ ተገልጋዮች ያለምንም መሸማቀቅ በግልፅ ሃሳባቸውን ስለሚሰጡ ለተቋሙ አዳዲስ የፈጠራ ግብዓት ይለግሳሉ፡፡ ሁለተኛው ጥቅም አስተያየቶቹን ተከትሎ በሚመጡ ለውጦች ሰራተኞችን ከማነቃቃት ባሻገር የስራ አካባቢ ድባብን በአዳዲስ አስተሳሰቦች መሙላት ያስችላል፡፡ ሦስተኛው ጥቅም በተቋሙ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች (ማኔጅመንት) የታደሱ ምልከታዎችን ተቀብለው በለውጥ ስሜት መቃኘት ይችላሉ፡፡ በመጨረሻም በተቋሙ አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ ፖሊሲዎችን እስከ ማሻሻል በሚደርስ መልኩ አተገባበሮችን ማስተዋወቅ ያስችላል፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁሉ ጥቅሞችን ማግኘት ማን ይጠላል?

በእርግጥ ከአስተያየት መስጫ ሳጥኑ የሚወጡት ጠቃሚ ግብረ መልሶችን በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው እርባና ቢስ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡ በተለይም ተገልጋዮችና ደንበኞች አስተያየቱን ለመስጠት ነፃነት እንዲሰማቸው ማድረግ ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ አለዚያ ሀሳባቸውን ማስፈር ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ አስተያየቶች ሁሉ ትክክል ላይሆኑ እንደሚችሉ መረዳትም ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ለማሾፍ በሚል የሚሰጡ አስተያየቶችን በአግባቡ መርምሮ መለየት ያስፈልጋል፡፡

አስተያየት መስጫ ሳጥኖች እንደዋዛ የሚቀመጡ ቢመስልም በአግባቡ ለሚጠቀምባቸው ተቋም መፍትሄ ጠቋሚና ወደ ስኬት የሚመሩ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ይሄን መንደርደሪያ ይዘን ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንተረጉመው ግን አተገባበሩ በአብዛኞቹ ተቋማት ትኩረት ያገኘ አይመስልም፡፡ ከተገልጋይ የሚሰጡ ግብረ መልሶችን እየተከታተሉ በመዳሰስ በኩል ያለው ተሞክሮ ደካማ ነው፡፡ አስተያየቶቹን መመልከትም ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በአስተያየቱ ልክ ለለውጥ መትጋት ከምንም በላይ መሰረታዊ ነጥብ ነው፡፡ ምክንያቱም በአዲስ አስተሳሰብ መትጋት ወደ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመራ እርምጃ ነው፡፡

ታዋቂው ሳይንቲስትና የዘመናዊ ዓለም የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን ለውጥን በተመለከተ አንድ አባባል አለው፡፡ አባባሉ ‹‹ሁሌም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ተግባር እየፈጸምክ አዲስ ውጤት መጠበቅ የዋህነት ነው›› የሚል ጭብጥ አለው፡፡ እስማማበታለሁ፡፡ ተቋማት የባለጉዳዮቻቸውን የአገልግሎት እርካታ ደረጃ የማወቅ ፍላጎት ካላቸው ቁልፉ መንገድ ነፃ አስተያየት መስጫ ሳጥን ቢሆንም፤ በአስተያየቱ ልክ እራሳቸውን ካልፈተሹ ሳይንቲስቱ እንዳለው ‹‹ተመሳሳይ ነገር ፈፅሞ አዲስ ነገር መጠበቅ›› ይሆናል፡፡

ስለዚህ ተቋማት ሆይ በመጀመሪያ ደረጃ መዝገብ የምትገልጡበት ወይም ሳጥን የምትከፍቱበት ቋሚ ጊዜ ይኑራችሁ፡፡ ምክንያቱም በየተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታ መጓደል የአገሪቱ አንድ ችግርና የመልካም አስተዳደር ማነቆ መሆኑ በመንግስት ተገምግሟል፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት ‹‹ኮሚቴ ይቋቋም ወይም የጥናት ቡድን ይዋቀር›› የሚል የጊዜ ቀጠሮ ከዚህ በኋላ መቀጠል የለበትም፡፡ ከምንም በላይ ለለውጥና ለመታረም የሚያስፈልገው ተጨባጭ ግብዓት ከሳጥኑ ወይም ከመዝገቡ ታገኛላችሁ፡፡ እርሱን አይታችሁ ተለወጡ፡፡ ብሩክ በርሄ press

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy