በኢትዮጵያ በተለያዩ አካላት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የኤች አይ አይ ቪ ስርጭት የመቀነስ ተግባራት የቫይረሱን ስርጭት እንደ ሃገር ከአስር በመቶ በላይ የነበረውን የቫይረሱን ስርጭት መጠን ወደ አንድ ነጥብ ሁለት በመቶ ማውረድ ተችሏል። የወረርሽኙ ስርጭት የተገታበት ሁኔታም ተፈጥሯል ፡፡
ይሁንና የኤች አይ ቪ ስርጭትን በመቀነስ የተገኘውን ይህን ስኬት በመመልከት በሕብረተሰቡ ዘንድ ቫይረሱ ጠፍቷል የሚል እሳቤ መፈጠሩን በቫይረሱ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ተቋማትም እየጠቆሙ ናቸው። ይህም አመራሩም ሆነ ሕብረተሰቡ ለመከላከልና መቆጣጠር ስራው የሚሰጡትን ትኩረት እንዲቀንሱ ማድረጉን ይናገራሉ።
ወጣት ማሬት ጌትነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽ/ቤት ሰሞኑን በጃን ሜዳ የወጣቶች ማዕከል ባዘጋጀው የወጣቶች ጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ የንቅናቄ መድረክ ተሳትፋለች። ወጣቷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትሪካል አርት ተማሪ ናት።«በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ ተረስቷል።ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም» ትላለች ፡፡
ወጣቷ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የቫይረሱን መዛመት ለመቀነስ ሰፊ ንቅናቄ ይደረግ እንደነበር ታስታውሳለች።ወጣቷ እንዳለችው፤ በመገናኛ ብዙሃን ከሚተላለፉ የግንዛቤ ማሳደጊያ መልእክቶች በተጨማሪ ጥንቃቄ ለማድረግ ብሎም ቫይረሱን ለመከላከል አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የተለያዩ በራሪ ወረቀቶችና ሌሎች የሕትመት ውጤቶች ተከታታይነት ባለው አኳሃን ይሰራጩ ነበር፤ አሁን መሰል ጥረት አይታይም ።
በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ብሎም የቫይረሱን ስርጭት በመግታት በሽታውን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ቀደም የነበራቸው ሚና ቀንሷል፤፤ጉዳዩን ትተውታል እያለችም ነው ፡፡
በአድማስ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪ ወጣት አብዪ አሰፋ ወጣቱ መገናኛ ብዙሃንን አስመልክታ የሰነዘረቸውን ሀሳብ ይጋራል ፡፡ቫይረሱን የመከላከልና መቆጣጠሩ ስራ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰፊ የሚድያ ሽፋን አላገኘም ይላል፡፡
«የበሽታው መከላከል እና መቆጣጠር ስራ አንድ ወቅት ላይ ነጥሮ በመውጣት የመገናኛ ብዙሃን ኣብይ ጉዳይ ሆኖ ነበር» ሲሉ ወጣቶቹ ይገልጻሉ፤፡ ወጣቶቹ እንደሚሉት፤ አሁንም በዜጎች ላይ የሚስተዋለውን መዘናጋት በመቀነስ ዜጎች ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ከፍ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቀጣይነት ያለው ቅንጅት በመፍጠር ጠቃሚና አጋዥ መልእክቶችን ማድረስ ይኖርባቸዋል ፡፡
የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራቸውን የተወሰነ ወቅት በመጠበቅ የመስራት አዝማሚያ እንዳላቸው የምታስረዳው ወጣት ማሬት፣ ወቅት በመንተራስ መሰል የግንዛቤ ማሳደጊያና የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረትን ተከታታይና ወጥ እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስልግ ትጠቁማለች ፡፡ይህን በማድረግም የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ባይ ናት ፡፡
ወጣቷ ጋብቻ ለመፈጸም እንዲሁም ደም ለመለገስ ከሚደረገው የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ ወጣቶች የራሳቸውን ጤነኝነት ለማረጋገጥ ብሎም የቫይረሱን መተላለፍ ለመቀነስ በራስ ተነሳሽነት የመመርመር ልምድ ማዳበር እንዳለባቸዉም ነው ምክሯን የምትለግሰው፡
ወጣት አብዪ አሰፋ እንደሚለው፤ የከተማዋ ወጣቶች ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ መተላለፍያና መከላከያ መንገዶች ግንዛቤ ቢኖራቸውም፣ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ግን ተጨማሪ የንቃተ ህሊና ስራ ያስፈልጋቸዋል ፡፡ በወጣቶች መካከል የሚኖር አቻ ግፊት ጥንቃቄ የጎደለው ግንኙነት እንዲያደርጉ የሚገፋፋ በመሆኑ ወጣቶች በቫይረሱ የመጠቃት ዕድላቸው ሰፊ ነው ፡፡
በወጣቶች ዘንድ በሽታውን ችላ የማለትና መዘናጋት የግንዛቤ ማሳደጊያ እና ስለ በሽታው ምንነት ዕውቀት ማስጨበጫ ልዩ ልዩ የተግባቦት ስራዎች ከመገናኛ ብዙሃን በመጥፋታቸው የተፈጠረ ነው የሚል ሃሳብ ወጣቶቹ አላቸው።
ወጣት አብዩ እንደሚለው፤ ስለ በሽታው ምንነት፣ወጣቶች የበሽታው ሰለባ እንዳይሆኑ ሊተግብሩዋቸው ስለሚገቡ ነገሮች የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨባጫ ስራ በቀጥታ ገለፃ ከሚሆን ይልቅ እያዝናና ሊያስተምር የሚችል አቀራረብን የተከተለ ቢሆን ውጤታማ መሆን ያስችላል ፡፡
« ከማንም በላይ ወጣቶች ለህይወታቸው ዋጋ በመስጠት፣ ራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል በጥንቃቄና በማስተዋል ነገሮችን ማከናወን እንደሚኖርባቸው አስገንዝቦ ፣ የወጣቶች ጤንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ትልቁን ድርሻ መውሰድ ያለባቸው ራሳቸው ወጣቶች መሆናቸውም ይጠቁማል፡፡
በአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፅህፈት ቤት የማሕበረሰብ ንቅናቄና ሜይንስትሪሚንግ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወንድሙ ደንቡ የቫይረሱን ስርጭት ዝቅ ማድረግ ተችሎ እንደነበረ አስታውሰው፣ አሁን ላይ ለመከላከልና መቆጣጠሩ እየተሰጠ ያለው ትኩረት እንደቀደሙት ዓመታት እንዳልሆነም ይጠቁማሉ ፡፡ በዚህ የተነሳም የቫይረሱ ስርጭት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ ።
«የባህሪ ለውጥ ለማምጣትና ዜጎች ራሳቸውን ከቫይረሱ የሚከላከሉባቸውን መንገዶች እንዲተገብሩ ለማድረግ በተለያዩ የተግባቦት መንገዶች ተከታታይ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል »የሚሉት አቶ ወንድሙ፣ ይህም በመገናኛ ብዙሃን ከሚተላለፉ መልእክቶች በተጨማሪ የማማከር አገልገሎቶችና የሕብረተሰቡ ንቃተ ህሊና ማሳደግን እንደሚያጠቃልል ይገልጻሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ወጣቶች ስለ ቫይረሱ መከላከያ ዘዴዎች ግንዛቤ ቢኖራቸውም የመርሳት ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ለዚህም ሁሌ ማስታወስና ቅስቀሳ ማድረግ ተገቢ ነው። መዘናጋቱ እያደገ የመጣውም የሃብት ውስንነት በመኖሩ ዘለቄታዊና ያልተቆራረጠ የግንዛቤ መድረኮችና የንቅናቄ ስራዎችን ማካሄድ ስላልተቻለ ነው።
እንደ አቶ ወንዱሙ ማብራሪያ፤ በቅርብ ዓመታት ባዮ ሜዲካል ተብሎ የሚጠራው ሌላኛው የቫይረሱ መከላከያና መቆጣጠርያ ስትራቴጂ ትልቁ የመንግስት የቫይረሱ መከላከያና መቆጣጠርያ መንገድ ሆኗል ፤፤ ይህ ስትራቴጂ ተመርምሮ ራስን በማወቅ፣ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በማድረግ፣ ኮንደም የመጠቀም ልምድን ለማሳደግ በመስራትና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን ሰዎች በምርመራ በመለየት ፀረ–ኤች አይ ቪ መድሃኒት እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያስችላል፡፡ የቫይረሱን መተላለፍና በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚጠቅም ስትራቴጂ ነው ።
አቶ ወንዱሙ አሁን መዘናጋትና በሽታውን ችላ ማለቱ የቫይረሱ ስርጭት እንዲጨምር ማድረጉ ታምኖበታል ይላሉ።ይህን ተከትሎም ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች በተለይ ወጣቶች ለህወታቸው ዋጋ እንዲሰጡና ለበሽታው የሚያጋሉጡዋቸውን ባህሪዎች እንዲቀንሱ ለማድረግ በሽታውን አስቀድሞ ለመከላክል የሚያስችሉ አዲስ ተጨማሪ ግንዛቤ ማሳደጊያ የተግባቦት ስራዎችን መጨመርና የንቃተ ህሊና ማበልጸግ ስራዎች አስፈላጊ ሆነው በመገኘታቸው ትኩረት ተሰጥቶዋቸዋል፡፡
ወይዘሮ ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠርያ ጽ/ቤት የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራሞች የስራ ሂደት መሪ ናቸው።«የቫይረሱ ዋና የመተላለፍያ መንገድ በወሲብ አፈፃፀም ሂደት የሚፈጠር ጉድለት እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ፈለቀች ፣ወጣቶች ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚያደርጉዋቸውን ልምዶች እንዲያስወግዱ ተከታታይ የማስታወስ ስራ ማከናወን እንደሚገባ ይናገራሉ ።ይህም በመቀነሱ ቫይረሱ ጠፍቷል የሚል አስተሳሰብ መፈጠሩን ገልጸው፤ ይህም የቫይረሱ ስርጭት መልሶ የሚያገረሽበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረጉን ያመለክታሉ ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ የወጣቶች ፍልሰት አንዱ የቫይረሱ ተጠቂ ወጣቶች ቁጥር እንዲጨምር እያደረገ ይገኛል ፡፡ በተለይ በበሽታው አጋላጭ ድርጊቶች ላይ ግንዛቤያቸው አነስተኛ የሆነ ከገጠር ወደ ትልልቅ ከተማዎች የሚመጡት ወጣቶች የቫይረሱ ተጋላጭ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው ።
የስራ ሂደት መሪዋ የወጣቶች ባህሪ የመቅረጽና ለበሽታው የሚጋለጡባቸውን ድርጊቶች እንዲቀንሱ ብሎም ራሳቸውን ከበሽታው ጠብቀው ሃገራቸውን የሚረከቡ ወጣቶችን እንዲሆኑ ለማድረግ በወጣት ማእከላት ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በእነዚህ ማእከላት በሚዘጋጁ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች በአንድ ጊዜ በርካታ ወጣቶችን ማሳተፍ እንደሚያስችልም ጠቅሰው፤ ፅህፈት ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚያከናውነው ተግባር እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በሪሁ ብርሃነ