Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተፎካካሪ ፓርቲዎች የክርክርና የድርድር ዕድሉን መጠቀም አለባቸው

0 362

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ የዴሞክራሲ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ፤ መንግሥት በዴሞክራሲ አኳኋን እንዲሠራና እንዲደራጅ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያምናል። ዴሞክራሲ በመንግሥት ተቋማት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አለመሆኑንም አሳምሮ ያውቃል። የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች፤ ሚዲያው እንዲሁም የሙያና የብዙኀን ማኅበራት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ፤ በስርዓቱም ውስጥ ተገቢ ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ኢህአዴግ በየፖሊሲ ሰነዶቹ ውስጥ በአጽንኦት ሳያስቀምጥ ያለፈበት ጊዜ የለም።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አላማን ለማሳካት፣ ተቋማዊ መሰረቱን ለማስፋት እና የጋራ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ብሎም እምነትን ለመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ድርጅቶችንና ተቋማትን መፍጠር፣ ማጠናከርና ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲፈጽሙ ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን ኢህአዴግ ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲያሰምርበት የኖረ ጉዳይ ነው። ዛሬ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ወይም ስጋት አልያም አጣብቂኝ ሰበብ ማራመድ የጀመረው አዲስ አቋም ሳይሆን ሲመራበት የኖረና ወደፊትም የሚመራበት ፖሊሲው ነው።

ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱና መጫወትም እንደሚገባቸው በጥልቀት ይገነዘባል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎችን መብቶችና ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አጀንዳዎችንና አማራጭ ሃሳቦችን ያመነጫሉ። ከዛም እነዚህ ሃሳቦች በአጠቃላይ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ በመጣር ሃሳቦቹ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑ በመታገል ከፍተኛ የአመራር ተልዕኮ እንዳላቸው ያምናል። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደዚህ አይነት ብቃት ያለው አመራር አግኝተው መብትና ጥቅማቸውን በዴሞክራያዊ አካሄድ ለማስጠበቅ የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚፈጥሩ በኢህአዴግ ዘንድ የታወቀ ነው። ፓርቲዎች በግልጽነትና በተጠያቂነት መሰረት ላይ በሚገባ የተተነተኑ ሃሳቦችን ይዘው በስርዓቱ ውስጥ የሚያደርጉት ቀጥተኛና ሰፊ እንቅስቃሴ ወደ ነቃ ተሳትፎ እንዲሸጋገር የሚያስችል ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ጥርጥር የሌለው አቋም ነው።

ፓርቲዎች የተደራጀ አመራር ሰጥተው የህዝቡን ድጋፍ ሲያገኙ የመንግሥት ስልጣንን ይዘው ሃሳባቸውን ተግባራዊ በማድረግ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ባለው ጽኑ እምነት መሰረትም ከተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት አሳይቷል። ፓርቲዎችን ለድርድርና ክርክር ጋብዟል። «ኑ ተገናኝተን እንወያይ» ሲል ጥሪ አቅርቧል። በሆደ ሰፊነትና በልበ ሙሉነት ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ከፓርቲዎች ጋር ተገናኝቷል። ፓርቲዎች ያላቸውን ሃሳብ አዳምጧል፤ በሚስማማባቸው ላይ ተስማምቷል። እስከዚህ ርቀት ድረስ መሄድ በራሱ ትልቅ እመርታ ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በዚህ የክርክርና የድርድር ዕድል መጠቀም መቻል አለባቸው። ክርክርና ድርድር የአልጋ ባልጋ መንገድ አይደለም። አባጣ ጎርባጣ የበዛበት ኮረኮንች የሞላበት ሰጥቶ የመቀበል አሰራር ነው።

«እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን…አለዚያ ረግጬ እወጣለሁ» የሚባልበት አይደለም። የራስን ሃሳብና አቋም እየሰጡ የሌላውን ሃሳብ እያዳመጡ በመግባባትና በመቻቻል መሥራትን የሚጠይቅ አካሄድ ነው። በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያሉ በዋናነት ተሳታፊ ከሆኑት ውስጥ ህዝብ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና ፓርቲዎች ተጠቃሽ ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ ለማስቻል በተለይ እንደ እኛ ባሉ አዳጊ አገራት ላይ የሚገኙ ፓርቲዎችን ለማደርጀት በመልካም አቀባበል ወደ ሰላማዊ የስልጣን ሸግግር ለማብቃት መንግሥት ብዙ ሚና ሊጫወት ይችላል። የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ፓርቲዎች ሃሳባቸውን የሚገልፁበት መድረክ ማግኘት አለባቸው። ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለማቋቋም ባይታደሉም ከህዝቡና ከሚወክሉት ማኅበረሰብ ጋር የሚገናኙባቸው ልሳኖች ሊያጡ አይገባም። ከመንግሥት ሚዲያም ጥቂት የአየር ሰዓት ማግኘት አይበዛባቸውም። ፓርቲዎች ጉዳያቸውን የሚከውኑበት እስከ ወረዳ ድረስ የሚዘልቁ ቢሮዎች እንዲያገኙ ሊደገፉ ይገባል።

አባሎቻቸውን የሚመለምሉበት አግባብ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባሎች የማይዋከቡበትና የማይሸማቀቁበት ሁኔታ መኖር አለበት። ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እያሳወቁ ለማድረግ ያላቸው በህገ መንግሥት የተረጋገጠ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፤ በማንኛውም ድጋፍ መጠናከር አለባቸው። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ሩጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን ለዓመታዊ ሥራቸው የሚበቃቸውን የበጀት ድጎማ ያድርግላቸው። ለቢሮ የሚሆን ቤተ መንግሥት ይስጣቸው፤ ወይም በቅናሽ ዋጋ ያከራያቸው። አቅማቸውን አጠናክረው በራሳቸው መንቀሳቀስ እስኪችሉ ድረስ መንግሥት ለዴሞክራሲ ስርዓቱ ግንባታ ሲል ማጠናከሪያ ቢያደርግላቸው ምንም ማለት አይደለም።

ይህ ሁሉ «ይደረግላቸው» ስንል ፓርቲዎቹ የዴሞክራሲ ባህል እንዲበለጽግ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲያብቡና እንዲጠናከሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ የአመራር ሚና ይኖራቸዋል በሚል እሳቤ ላይ ተመሥርተን ነው። ፓርቲዎች የአመራር ሚናቸውን ሊጫወቱ የሚችሉት ደግሞ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ባህርይ ሲኖራቸው ነው። ይህ ማለት ደግሞ ፓርቲዎቹ በእርግጥም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆን አለባቸው ማለት ነው። በአጭሩ ፓርቲዎቻችን አንድን የፖለቲካ ዓላማ ለማራመድ፣ በዚሁ የፖለቲካ ዓላማ ስር ለመሰባሰብ የሚፈልጉ ዜጎችን በሙሉ ለማቀፍ የሚሰሩ መነሻና መድረሻቸውም ይህን የፖለቲካ ዓላማ ያደረጉ ድርጅቶች ሆነው መገኘት አለባቸው። በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብና ማህተም በኪሳቸው፤ ሞባይል በጆሮአቸው አንጠልጥለው በፓርቲነት ስም ለመነገድ መሆን የለበትም።

ፓርቲያቸውን ለማራመድ የራሳቸውን ዓላማ ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆን አለባቸው። በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዲችሉ አማራጮችን ለመተንተን፣ ለማቀናበርና ለህዝብ ለማቅረብ አቅም ያላቸው እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ማለት ፓርቲዎች አመለካከታቸው እምነታቸውና አሠራራቸው ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት። ማለትም የራሱ ውስጠ -ፓርቲ አሠራር ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፋይዳ ያለው አስተዋጽኦ ማበርከት አይችልም። ፓርቲዎች በህዝቡ ውስጥና መካከል በመሰረታዊ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አቅጣጫና በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ አንድ የጋራ አገራዊ እምነትና አመለካከት እንዲፈጠር የሚሰሩ መሆን አለባቸው። ፓርቲዎች በራሳቸው መካከልም ጤናማ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል። የጋራ ብሔራዊ ራዕይ ያስፈልጋቸዋል።

በብሔራዊ መሰረታዊ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ አገራዊ አመለካከትና እምነት መያዝ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ከሌለ የህዝብን ሃሳብ የምናንፀባርቅና ለህዝብ ጥቅም የምንሰራ ፓርቲዎች ልንሆን አንችልም። መሆን የምንችለው በህዝብ ስም የሚነግድ ሳንቲም አሳዳጅ የፓርቲ ኩባንያ ብቻ ነው። ገንዘብ ለማግኘትና ለመክበር የምንፈልግ ከሆነ ማድረግ ያለብን ከፖለቲካው ወጥተን ወደ ንግዱ ዓለም መግባት ነው። ገንዘብ ያለው እዚያ ነው፤ እዚህ ያለው ደግሞ የህዝብ ጥቅም ነው። በፓርቲ ስም ከመንግሥት ጋር እየተሞዳሞዱ በሚፈጥሩት ሽርክና በአቋራጭ ለመክበር መሯሯጥ የህዝብ አመኔታን ያሳጣል፤ ህዝቡ ያውቃል። ከህዝብ የሚሰወር አንድም ነገር የለም። ህዝቡ የስርዓቱ ግንድ ነው፣ ያለ ግንዱ እውቅና ደግሞ ተበጥሳ የምትወድቅ አንዲትም ቅጠል የለችም። ያወቀ ህዝብ በበኩሉ በድምፁ ይቀጣል፣ በምርጫ ጊዜ ድምፁን ይነፍጋል። ስለዚህ ፓርቲዎቻችን ዛሬ ላይ ሆነው የሚሠሩት ሥራ በሙሉ ነገ ላይ ባለው ምርጫ የህዝብን ድምጽ አግኝቶ ስልጣን ለመያዝ የሚያስችላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፤ ይህ ከፓርቲዎች የሚጠበቅ ነው። መንግሥት በበኩሉ ተጨማሪ እርምጃ ወደፊት ሄዶ ፓርቲዎቹን ማበረታታት አለበት። ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ለመፍጠር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን አብሮ እየፈታ አቅም ኖሯቸው ራሳቸውን ችለው ወይም ህብረትም ሆነ ግምባር፤ ጥምረትም ሆነ መድረክ ፈጥረው ወግ ባለው አደረጃጀትና ህዝቡን ግራ በማያጋባ ቁመና ላይ ሆነው ለመታገል እንዲችሉ የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል። ለፓርቲዎች ጥቅም ብሎ ሳይሆን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ሂደት ሊያበረክቱ ለሚችሉት አስተዋጽኦ ሲል መደገፍ አለበት። ለፓርቲዎች ቅዠትና ራስ ምታት ሊሆኑ የሚችሉ ፈተናዎችን ሊያቃልላቸው ይገባል። የታሰሩ አመራሮቻቸውና አባሎቻቸው ካሉ ለክርክሩና ለድርድሩ ስኬት ሲል ቢፈታላቸውም ጥሩ ነው። በእርግጥ በፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥ መስዋዕትነት አለ።

ዋጋ የሚያስከፍሉ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ይህን ማንም ተራ ፖለቲከኛ ያውቃል። «አመራሬ ታስሮብኛልና አልታገልም» ማለት የዋህነት ነው። አንዱ አመራር ቢታሰር ሌላ አመራር እየተኩ መታገል ነው፣ የጨዋታው ህግ የፓርቲ አመራር ወይም አባል መሆን እንደፈለጉ መሆንን አያመለክትም። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው !ቢሆንም… ቢሆንም …! መንግሥት የክርክሩንና የድርድሩን አድማስ ለማስፋት ሲል ጥሪውን እዚህ ላሉት ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭ ሆነው ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጭምር የሰላም እጁን ዘርግቶ ለመነጋገር ፍላጎት ካላቸው ጋር ሁሉ መድረክ ቢኖረው መልካም ነው። በአንድ በኩል አገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ተጠናክረው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ የህዝቡን አመኔታ ያተርፍለታል። ጠንካራ ፓርቲዎችን ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባት ከፍተኛ ትግልና ጥረት፣ ጥንቃቄና ብቃት ያለው የአፈፃፀም ስልት የሚጠይቅ መሆኑን የሚያውቀውና የሚያምነው ገዥው ፓርቲና መንግሥት ይህን ማድረግ ሊከብደው አይችልም። ከኢህአዴግ የፖሊሲ ሰነዶች የተረዳነውም ይህንኑ ነው።   ግርማ ለማ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy