Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኔስሌ በኢትዮጵያ ፋብሪካ የመክፈት ሐሳብ እንዳለው ይፋ አደረገ

0 513

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

– አትሌት ኃይሌን የብራንድ አምባሳደር በማድረግ ሰየመየስዊዘርላንዱ ኔስሌ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ በወተት ማቀነባበር መስክ ፋብሪካ የመክፈት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ፡፡በኢትዮጵያ ወደፊት እንደሚገነባ የሚጠበቀው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መቼ ዕውን ሊሆን እንደሚችል የሚወስኑት በአገሪቱ የሚገኘው የወተት ምርትና የአቅርቦት መጠን፣ የወተት ጥራት ደረጃና ጤንነት እንደሆኑ የገለጹት በኢኳቶሪያል አፍሪካ ቀጣና የኔስሌ የአፍሪካ ቀንድ ክላስተር ማናጀር የሆኑት አቶ ወሰንየለህ ፍቅሬ ናቸው፡፡

አቶ ወሰንየለህ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ የኔስሌ የወደፊት የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑ 20 አገሮች ውስጥ እንዲሁም ከአምስት አቅም ያላቸውና ምርጫው ካደረጋቸው አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ ትካተታለች፡፡ ይሁንና የፋብሪካው ምሥረታ መቼ ሊሳካ እንደሚችል ገና ያልታወቀ ሲሆን፣ ከዚህ ይልቅ የዱቄት ወተት ምርቶቹን እዚሁ ለማሸግ የሚያበቁትን ዝግጅቶች በማድረግ ይህንን የሚያከናውን ፋብሪካ መመሥረቱ እንደማይቀር አቶ ወሰንየለህ አረጋግጠዋል፡፡

የማሸጊያ ፋብሪካው በቅርቡ ዕውን ሊሆን እንደሚችል ቢገለጽም፣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥና በምን ያህል ወጪ ለሚለው ምላሹ ወደፊት እንደሚታወቅ የጠቀሱት አቶ ወሰንየለህ፣ ከዚህ ባሻገር ግን ኔስሌ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገሮች የሚታወቅበትን የኒዶ ዱቄት ወተት ምርት በአዲስ መልክ አሽጎ ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡ ይህንኑ በማስመልከት፣ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን የምርቱ አምባሳደር አድርጎ መሰየሙ ይፋ ተፈርጓል፡፡ ረቡዕ የካቲት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ኃይሌ የኒዶ ወተት የብራንድ አምባሳደር ለመሆን የአንድ ዓመት ስምምነት መፈጸሙን ይፋ አድርጓል፡፡

በመላው ዓለም ከ2,000 በላይ ብራንዶችን የሚያስተዳድረው ኔስሌ፣ ከ10 ሺሕ በላይ ምርቶችን በማምረት ከአንድ ቢሊዮን በላይ የምርት ሽያጭ የሚያከናውን የምግብና የመጠጥ አምራች ኩባንያ ነው፡፡ በአብዛኛው በውኃ፣ በወተት፣ በቡና እንዲሁም በልዩ ልዩ የበለፀጉ ምርቶቹ የሚታወቀው ኔስሌ፣ በኢትዮጵያ የውኃ ማዕድን መስክ ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር አብሮ ለመሥራት መስማማቱ ይታወሳል፡፡

ከኔስሌ ባሻገር ከቶታል እንዲሁም ከዜድቲኢ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ከሌሎችም ልዩ ልዩ ኩባንያዎች ጋር የብራንድ አምባሳደር በመሆን በማስታወቂያ ሥራ እየተሳተፈ የሚገኘው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ኒዶን ለማስተዋወቅ ምን ያህል እንደተከፈለው ከመናገር ተቆጥቧል፡፡ ገንዘቡን መግለጽ ለሥራው መበላሸት አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችልም ያምናል፡፡

ይሁንና ከዚህ ቀደም በ100 ሺሕ ዶላር ክፍያ የጆኒ ዎከር ዊስኪን ለማስተዋወቅ ያደረገው ስምምነት ትችትን እንዳስከተለበት ይታወሳል፡፡ ይህንኑ ያስታወሰው አትሌት ኃይሌ፣ የደረሰበት ወቀሳ የእሱን የሥራ ድርሻና ያደረገውን ስምምነት ካለመረዳት የመነጨ እንደነበር ገልጿል፡፡ ሆኖም ከስፖርታዊ ሰብዕናው በተጻረረ መልኩ መጠጥ ማስተዋወቁ ነበር ለኃይሌ ትችትን ያስከተለበት፡፡

ምንም እንኳ በማስታወቂያ ሥራዎች ውስጥ እየተሳተፈ ቢሆንም አትሌት ኃይሌ፣ በርካታ ቢዝነሶችን በማንቀሳቀስ ትልቅ የኢንቨስትመንት ካፒታል መገንባት የቻለ ሰው ለመሆን በቅቷል፡፡ በሆቴል መስክ የሚያስተዳድራቸው ሪዞርቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአስመጪነት መስክም ከጃፓኑ ሃዩንዳይ ኩባንያ የሚያስመጣቸውን ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችን የሚያከፋፍለውን ማራቶን ሞተርስ ኩባንያ መሥርቷል፡፡ የማር ምርት ወደ ውጭ በመላክ ላይ የጀመረውን የእርሻ ኢንቨስትመንትም ወደ ቡና በማስፋፋት ሰፊ የቡና እርሻ መሬት መግዛቱም ይታወቃል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy