Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አማካሪ እና ተማሪ አልተናበቡም

0 351

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሁን አሁን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የማሟያ ጥናቶች የሚከናወኑት ከተማሪው ተሳትፎ ውጪ እየሆነ መጥቷል። በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እና በአካባቢያቸው «የጥናት ጽሁፍ እናዘጋጃለን» የሚሉ ማስታወቂያዎችን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሳይቀሩ እጃቸው እንዳለበት ተማሪዎች ይናገራሉ። ይሁንና ከህገወጡ ተግባር በተቃራኒው በትክክለኛው መንገድ ዕውቀታቸውን ከአማካሪ መምህራቸው ገንቢ አስተያየት ጋር አጣምረው ለአገር የሚጠቅም ጥናት የሚያቀርቡ እንዳሉም አይካድም። እዚህ ላይ «በተገቢው መንገድ ጥናት ለማቅረብ ብንጥርም አማካሪዎቻ ችንን በበቂ ሁኔታ ባለማግኘታችን ችግር ገጥሞናል» የሚል ቅሬታ የሚያነሱ ተማሪዎች ደግሞ እየተበራከቱ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ተሾመ ታደሰ እንደሚናገረው ከሆነ፤ ለዲግሪ ማሟያ ጥናት በሚያዘጋጅበት ወቅት አማካሪ መምህሩን በወቅቱ እና በአስፈላጊው ጊዜያት ባለማግኘቱ ምክንያት በ2008 .ም መጨረስ የነበረበትን ትምህርት አሁን ላይ እየተማረ ይገኛል። ባለፈው ዓመት ጥናቱን በሚያዘጋጅበት ወቅት አማካሪው በሥራ ምክንያት ከተማ ውስጥ ባለመገኘታቸው ጥናቱን በአግባቡ ማከናወን አላስቻለውም። ይህም ደግሞ አንድ ዓመት በትምህርት ጊዜው ላይ እንዲጨምር አስገድዶታል። ከጊዜ ብክነት በተጨማሪ ለተጨማሪ የገንዘብ ወጪም ዳርጎታል።

መምህራኑ በተገኙበት ወቅት ገንቢ አስተያየት ለተማሪዎች የሚሰጡ ቢሆንም አንዳንድ መምህራን የመገኘት እድላቸው አነስተኛ ነው የሚለው ተማሪ ተሾመ «ይህን ችግርም ለዩኒቨርሲቲው ለማሳወቅ ጥረት አላደረግንም ምክንያቱም እራሳቸው አማካሪዎቹ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች በመሆናቸው ችግሩን ለማን እናሳውቃለን በሚል ከተማሪዎች ጥያቄ አይቀርብም» ይላል። ቢቀርብም ጥያቄው ዞሮ ዞሮ ለእራሳቸው ለአማካሪዎቹ ይደርሳል። ይህም መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት እንዲቀንስ አድርጓል። በመሆኑም ችግሩ በኔ ይብቃ እና ቀጣይ በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ሁሉ የዚህ ችግር ሰለባ እንዳይሆኑ ማስተካከል ይገባል የሚል ምክር ሰጥቷል።

ተማሪ ታረቀኝ መኮንን በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የሶስተኛ ዲግሪ(ዶክትሬት) ተማሪ ነው። አማካሪ እና ጥናት የሚያቀርበው ተማሪ ያላቸው ግንኙነት ወሰን እንደሚያስፈልገው ነው የሚናገረው። አብዛኛውን ጊዜ ሁሉን ነገር አማካሪው እንዲሰጠው እና እንዲሰራው የሚጠብቅ ተማሪ አለ። በዚህም ምክንያት ብዙ ነገር ከአማካሪያቸው ጠብቀው ያላገኙ ተማሪዎች ለጥናቱ ያላቸው ፍላጎት በእጅጉ እየቀነሰ ይሄዳል። ይህም የተማሪዎች ክፍተት በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ ይመክራል። ይሁንና ዋነኛው ሥራ የሚያስፈልገው ከተማሪው በመሆኑ ለዲግሪም ሆነ ዶክትሬት ማሟያ ጥናት ጽሁፍ ከፍተኛውን መረጃ ለመሰብሰብ እና ለማጠናቀር ጥረት ማድረግ ተገቢ አካሄድ ነው። በዚህም የአንበሳውን ድርሻ ጥናት አቅራቢው ከያዘ በተጨማሪ የአማካሪው ሥራ የሚሆነው የተወሰነ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ይሆናል። በመሆኑም ተመካሪ ያመጣውን መረጃ እና ጥናት አማካሪው አካል መንገድ የማስያዝ ሚና ብቻ እንዳለው መረዳት እንደሚገባ ያምናል።

«ይሁንና ሁሉም አማካሪዎች መልካም አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት አይደለም። አንዳንድ አማካሪዎች ጋር ለጥናቱ ትኩረት ያለመስጠት እና የማማከር አገልግሎቱን እንደ ትርፍ ሥራ የመቁጠር ችግር አለ። ለአብነትም የተማሪውን የጥናት ንድፍ ወረቀት ለረጅም ጊዜ ይዞ የሚያቆይ የዩኒቨርሲቲ መምህር ይታያል። ይህም የሚከሰተው አንዳንድ መምህሮች ከተቋማቸው የሚሰጣቸውን የሥራ ጫና ለመከላከል እጄ ላይ ሥራ አለለሚል ሰበብ ሊጠቀሙበት ሲፈልጉ ነው።ይሁንና ዩኒቨርሲቲው የሥራ ጫና እንዲቀንስ የተማሪውን ወረቀት ይዞ ማቆየት ተገቢ አይደለም » ይላል።

ከዚህ በተጨማሪም ኃላፊነት ላይ ያሉ አንዳንድ መምህራን ረጅም ጊዜያት ለሥራ ወደመስክ በመውጣታቸው ምክንያት ለአጥኚ ተማሪው የሚሆን ጊዜ ያጥራቸዋል። ይህም የተማሪውን የጥናት ጊዜ ያስተጓጉላል። በእነዚህ ምክንያቶች በሁለት እና ሶስት ዓመታት መጨረስ የነበረባቸውን የትምህርት ጊዜ እስከ አስር ዓመት ጊዜ የተራዘመባቸው የቀድሞ ተማሪዎች ይገኛሉ። በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ የትምህርት ዘርፎችን እያጠናከረ ቢገኝም ለዶክትሬት ተማሪዎች የሚያደርገው የግብዓት ድጋፍ ከክልል አቻ ተቋማት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን ነው የሚናገረው። የተለያዩ የአገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች ለዶክትሬት ተማሪዎች ቢሮ እና ነፃ ላፕቶፕ እንዲሁም የኪስ ገንዘብ ያዘጋጃሉ። ይህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ያልተሟላ ከመሆኑም በላይ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንኳ ደካማ በመሆኑ የሚፈለገውን መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። በዚህም ምክንያት የጥናት ሥራዎች ላይ ችግር ይፈጠራል። በመሆኑም በቀጣይ የተቋሙ ኃላፊዎች ሊያስተ ካክሉት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ነው ያሳሰበው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ በበኩላቸው፤ በድህረ ምረቃ ትምህርት ከ16 ሺ በላይ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንደሚገኙ ይናገራሉ። ከረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ ጀምሮ ያሉ መምህራንም በድህረ ምረቃ ትምህርቶች ላይ አስተማሪ እና የጥናት አማካሪ ሆነው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውሰው «በተማሪዎች ጥናት ማማከር ላይ መምህራን አይገኙም» የሚለው ወቀሳ ላይ ሁሉንም መምህራን ማጠቃለል እንደማይገባ ነው የሚጠቁሙት።

ምክንያቱን ሲያብራሩም «መምህራን ለምርምር ሥራ፣ በኮንፈረንሶች ላይ ለመካፈል እና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ተለያዩ አገራት መሄዳቸው የተግባራቸው አንድ አካል ነው። መምህራንም ሥራቸውን የሚያውቁ እና ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው። ይሁንና ችግሩ ቢኖር የሚፈታበት መንገድ በዩኒቨርሲው የተቀመጠ በመሆኑ ተማሪዎች ከአማካሪ ጋር ተያይዞ የሚያነሱትን ጥያቄ ከትምህርት ክፍል ኃላፊ ጀምሮ ችግሩን መፍታት ይቻላል። ችግሩ ከዚህ ካለፈም እስከ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ድረስ ጥያቄ አቅርቦ ማስፈታት ይገባል።»

ይሁንና አማካሪ በአግባቡ ማግኘት አልቻልኩም እና ተያያዥ ችግሮች አጋጥሞኛል የሚል ቅሬታ ከማንኛውም ተማሪ መቅረቡን እንደማያስታውሱ ነው የሚጠቁሙት። ችግሩ መኖሩ ከተማሪው ካልመጣ በጋራ ለመፍታት እንደሚያስቸግር ነው የተናገሩት።

«ችግሩ አይኖርም ማለት አይቻልም። ነገር ግን ችግሩ ተማሪው ጋር ወይም መምህሩ ጋር ሊሆን ይችላል» የሚሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነትምህርት ኮሌጁ መምህር ዶክተር አምቢሳ ቀነዓ ናቸው። በመሆኑም ችግሩን ሙሉ በሙሉ የአንድ ወገን አድርጎ መደምደም አይገባም። ተግባብተው የሚሰሩ ተማሪ እና መምህራን በመኖራቸው ጉዳዩ የሁሉም ችግር አድርጎ መውሰድ አይቻልም። ይሁንና በተማሪዎች በኩል ከአማካሪያቸው የጥናት አስተያየት ከተቀበሉ በኋላ ሁለት እና ሶስት ወራትን ቆይተው አማካሪያቸውን ለማግኘት ይዘጋጃሉ። የተለያዩ ተማሪዎች በአስተማሪነት እና በማማከር እንዲሁም በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ በመሆናቸውም ከአማካሪያቸው ጋር ለመገናኘት በቂ ጊዜ ያጥራቸዋል። በዚህም ምክንያት አማካሪው ቢገኝም አጥኚው አካል የማይገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ያምናሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ጥናቱን እንደጨረሰ አድርጎ ሪፖርት የሚያቀርብ ተማሪ በመኖሩ የአማካሪውን የመጨረሻ ሥራ እንደማያይ አድርጎ የመገመት ችግር ይከሰታል። አንድ ጥናት ሲከናወን የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ ከመነሻ ሃሳብ ጀምሮ እስከ መምደሚያ ሥራው ድረስ አማካሪውን ሊያሳትፍ ይገባል። በሌላ በኩል ለዶክትሬት ተማሪዎች በቂ ግብአት ማሟላት እንዳለበት ቢታመንም በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጁት ጥቂት የማረፊያ ክፍሎች ላይም ተማሪዎች አይገኙም። በመሆኑም ለጊዜውም ቢሆን የተዘጋጀውን ግብዓት በአግባቡ ተጠቅሞ ማሳየት እንደሚያስፈልግ ነው ዶክተር አምቢሳ የሚናገሩት።

«በአማካሪ በኩል ደግሞ አንዳንዱ ተማሪውን ጥናቱን ጨርሶ እንዲያመጣ የሚጠብቅ ይኖራል። ይህ ተገቢ አይደለም። በመሆኑም ወቅቱን ጠብቆ ገንቢ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም አማካሪዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ትምህርት ድረስ የሚገኙ ተማሪዎች በሚሰሩት ጥናት ላይ እንዲያማክሩ ይደረጋል። ይህ አስተማሪው ላይ የሥራ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ ለተመካሪው በቂ ጊዜ እንዳይሰጥ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት የጥናት ሥራው ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ይህ ወደፊት መታየት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው » በማለት ነው መፍትሄ ያሉትን የጠቆሙት።

ማንኛውም አካል ጋር ችግሩ ቢከሰት ተጠያቂው ማነው? የሚለውን ለመለየት የክትትል ሥራው መጠናከር አለበት። በመሆኑም የተጠያቂነት ስርዓቱ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ስለመኖሩ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በዚህም የየትኛው መምህር ተማሪዎች በጥናታዊ ሥራ ላይ አነስተኛ ውጤት አምጥተዋል ወይም ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል የሚለውን መፈተሽ ይገባል። ለዚህም አስፈላጊው የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ለውጤታማነት ይረዳል። ከክትትሉ ጋር ተያይዞ ተማሪው በክፍል ውስጥ ሲገኝ ስለመገኘቱ እንደሚመዘነው ሁሉ ወደ ጥናት ሥራ ከገባ በኋላም ስለመገኘቱ ክትትል ያስፈልጋል። ይህንንም መምህሩ ሪፖርት የሚያደርግበት እና በቂ ቁጥጥር የሚደረግበት መንገድ መመቻቸት አለበት።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy