NEWS

አቸቶ ከአሲድ ጋር በመደባለቅ በመሸጥ የተጠረጠረችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች

By Admin

March 13, 2017

ከአሲድ ጋር በመደባለቅ በህገወጥ መንገድ 700 ደርዘን የአቸቶ ወይም የኮምጣጤ ምርት በመሸጥ የተጠረጠረችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች።

የንግድም ሆነ የጥራት ማረጋገጫ የሌለውን ጂ ኤች የተሰኘ የኮምጣጤ ምርት በተለምዶ ጀሞ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ

በመሸጥ ላይ እያለች በቁጥጥር ስር የዋለችው ገነት ይልማ ራምሶ አሁን በንፋስ ሰልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እየተካሄደባት ይገኛል።በመምሪያው የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ሀላፊ ምክትል ኮማንደር አየለ ላቀው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በአቸቶው ውስጥ የተገኘው የአሲድ መጠን በሰው ጤና ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የጉዳት መጠን ለማወቅ ምርቱ ለምርመራ ወደ ምግብ ደህንነት ማረጋገጫ ክፍል ተልኳል።

ሀላፊው አክለውም ፖሊስ በግለሰቧ ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማጠናቀር የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን፥ መጋቢት 14 ቀን 2009 ዓ.ም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቄራ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምርመራውን እያካሄደ ያለው የንፋሰ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስም ምርቱ በሌሎች አካባቢዎችም ላይ ተሰራጭቶ ሊሆን ስለሚችል ህብረተሰቡ ምርቱን ከመግዛት እንዲቆጠብና ለፖሊስ በመጠቆም ደህንነቱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል። FBC