Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዲስ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ እንደማይኖር አስተዳደሩ አስታወቀ

0 610

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመኖሪያ ቤትን እጥረት ለመቅረፍ መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክትን ይፋ ባደረገበት 1997 ዓ.ም. የተመዘገቡትን ጨምሮ በ2005 ዓ.ም. በድጋሚ የተመዘገቡት ዜጎች ተጠናቀው የቤት ባለቤት ሳይሆኑ፣ አዲስ ምዝገባ እንደማይጀመር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ይህን ያስታወቁት፣ ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የተመረቁትን 39,249 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አስመልክቶ በጽሕፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

አቶ ድሪባ እንደገለጹት በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 ፕሮግራሞች ለተመዘገቡ ከስምንት መቶ ሺሕ በላይ ቤት ፈላጊዎች በመገንባት ላይ ያሉትንና ወደፊትም በሚገነቡ ቤቶች ባለዕድል ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው ምዝገባ ላመለጣቸው ቤት ፈላጊዎች ደግሞ አስተዳደሩ የኪራይ ቤቶችን በመገንባትና በማከራየት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ አንድ ተከራይ ከሚያገኘው ገቢ 30 በመቶ በላይ መብለጥ እንደሌለበት የተናገሩት ከንቲባ ድሪባ፣ በአጠቃላይ የቤት ኪራይን በሚመለከት የፌዴራል መንግሥት ሕግ እያዘጋጀ በመሆኑ ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን አሁን የሚታየው ችግር የሚፈታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ የቤት ችግርን ለመፍታት የተለያዩ አማራጮች እየታዩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አስተዳደሩ በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 ፕሮግራሞች በድምሩ 317,863 ቤቶችን የገነባና እየገነባ መሆኑን የገለጹት አቶ ድሪባ፣ 653.3 ሔክታር መሬት ከሊዝ ነፃ ማቅረቡንና 17.5 ቢሊዮን ብር ቀጥታ ድጎማ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሚመለከት ማለትም ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት በክራውንና ሠንጋ ተራ በተገነቡት 1,292 ቤቶች ላይ መገናኛ ብዙኃን በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ከንቲባ ኩማ በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. ለአስተዳደሩ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት የተጠቀሱት 1,292 ቤቶች 96.12 በመቶ መጠናቀቃቸውን ገልጸው፣ ‹‹በቅርቡ ይተላለፋሉ›› ማለታቸውን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ቤቱን የምናስተላልፈው እኛ አይደለንም፡፡ አስተዳደሩ ገንብቶ የሚያስረክበው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ አሁን ወደ መጠናቀቁ ላይ በመሆኑ ባንኩ በቅርቡ ያስተላልፋል፤›› ሲሉ ያለፈውን በሪፖርታቸው ያሉትን ደግመውታል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው ደግሞ፣ የ40/60 እና የ20/80 የቤቶች ግንባታ አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የሆነውም በፋይናንስ (ክፍያ) አለቃቀቅ ላይ ንግድ ባንክ አዲስ አሠራር በመጀመሩ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ከንቲባ ድሪባ ስለፋይናንስ ችግር ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ደግሞ፣ ከታኅሳስ ወር በፊት የፋይናንስ ችግር እንደነበረ አምነው ከጥር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ባንኩ አዲስ አሠራር ተግባራዊ በማድረጉ ችግሩ መቀረፉንና ሥራዎችን በርብርብ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በሁሉም ፕሮግራሞች ግንባታዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ የ40/60 ቤቶች ለባንኩ መቼ እንደሚተላለፉና ዕጣቸው መቼ እንደሚወጣ ቁርጡን መናገር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በሁለቱ ሳይቶች የተገነቡት ከ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ለመንግሥት ተሿሚዎች ለመስጠት ለመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ (አሁን የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ለሚባለው) ተሽጠዋል ስለመባሉ ጥያቄ የቀረበላቸው ከንቲባ ድሪባ፣ ‹‹የተሸጠ ቤት የለም!›› በማለት አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች 160 ሺሕ መሆናቸውንና 16 ሺዎቹ መቶ በመቶ መቆጠባቸውን ያረጋገጡት ከንቲባው፣ የዕጣ አወጣጡን በሚመለከት በተቀመጠው ፖሊሲና ስትራቴጂ መሠረት ሙሉ በሙሉ የቆጠቡ በቅድሚያ እርስ በርስ ተወዳድረው የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል፡፡ ሁሉም ተመዝጋቢዎች እንደ ቁጠባቸው የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አክለዋል፡፡

ሌላው በቦሌ አራብሳ የተገነባው 13.1 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ጉዳይ ሲሆን የወጣበት ወጪ እጅግ የተጋነነ፣ በአንድ ኪሎ ሜትር ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ከመስቀል አደባባይ አስከ ቦሌ ጫፍ ከተሠራው አስፋልት መንገድ ወጪ ጋር (በኪሎ ማትር 60 ሚሊዮን ብር) በማነፃፀር ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ከንቲባ ድሪባ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ለቦሌ አራብሳ የኮብልስቶን ንጣፍና (ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተሠራ 21.5 ኪሎ ሜትር) የአስፋልት ግንባታ ወጪ በአግባቡ የወጣ ነው፡፡ በኮንትራት ሕግ መሠረት የተሠራ ነው፡፡ ተጋነነ የሚለው በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ትርፍ የወጣ ነገር የለም፤›› ያሉ ሲሆን፣ ሁለቱን መንገዶች ማወዳደርም እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አንድ መንገድ ተቆፍሮ የሚወጣው አፈር፣ የአለት መጠንና የተቆፈረበትን ቦታ ለመሙላት የሚፈጀው ግብዓት ስለሚለያዩ አንድን ኪሎ ሜትር ከሌላ ኪሎ ሜትር ጋር ማወዳደር ትክክል እንዳልሆነና ሳይንሳዊ አለመሆኑንም አቶ ድሪባ ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ መንገድ የራሱ የሆነ አሠራር ስላለው ስህተት መሆኑን አክለዋል፡፡በቦሌ አያት፣ ቦሌ አራብሳ፣ ቂሊንጦና ኮዬ ፈጬ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አሠራራቸው ጥራት እንደሚጎድለው ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ ከሌሎች አገሮች ልምድ በመውሰድ በጥራት የተገነቡና ብቃት ባላቸው ኮንትራክተሮች የተገነቡ በመሆናቸው ምንም ዓይነት የጥራት ችግር እንደሌለባቸው ከንቲባ ድሪባ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በአሥረኛው ዙር ከተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቱሉ ዲምቱ ከተዘረጋው መሠረተ ልማት 2.5 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ መገንባቱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ስለመጥፋቱ የተጠየቁት አቶ ድሪባ፣ ‹‹አስፋልቱ ተጀምሮ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ እያንዳንዱ ግንባታ ባለቤት አለው፡፡ አስፋልቱ አለመኖሩ ወይም አለመሠራቱን በሚመለከት የደረሰኝ ሪፖርት የለም፡፡ ነገር ግን የታቀደው ነገር ካልተፈጸመ ታይቶ ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ብለዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy