Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ጠ/ሚ ኃይለማርያም

0 438

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በኡጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከፕሬዚዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ከሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር አካባቢያዊና አህጉራዊ ጉዳዮችም በመሪዎቹ ውይይት ተዳሷዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት፥ በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን የተደረገው ጥረት ውጤት አስመዝግቧልያሉ ሲሆን፥ ለዚህም በጥምረት የተደረገውን ጥረት አድንቀው፤ ኡጋንዳም ለከፈለችው መስዋዕትነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

“ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የተሰራው ስራ እና የተገኘው ውጤት አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ አቅም ለመፍታት የምታደርገው ጥረት ማሳያ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ሱዳንን ሰላም ለመመለስ በኢጋድ በኩል እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤታማ እስኪሆን ድረስ እንደሚቀጥል ነው የጠቆሙት።

“በጥምረት ለመስራት፣ ለምጣኔ ሃብታዊ ብልጽግና እና ለንግድ ልውውጥ ሰላም ያስፈልገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ በቀጣይም አህጉሪቷ ያሉባትን በርካታ ችግሮች በራሷ ልጆች የተባበረ ክንድ መፍታት እንደሚገባት ነው አጽንኦት የሰጡት።

የዓባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በተመለከተም “ሃብቱ የጋራ እንደመሆኑ ለጋራ ተጠቃሚነት በትብብር መስራት ይገባል” ብለዋል።

በኢትዮጵያና ኡጋንዳ መካከል የንግድ መግባባት መደረጉም ከእነርሱ አልፎ የአካባቢውን አገራትም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በአገሪቷ ስላደረጉት ጉብኝት አመስግነው፤ የሁለቱ መሪዎች ቆይታ ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬና የጉብኝቱ ተሳታፊ ሚኒስትሮች በመካከለኛው የአገሪቷ አካባቢ ኪሶዚ የሚገኘውን የፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ የከብት እርባታ ጎብኝተዋል።

በኡጋንዳ ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና ሽኝት ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ የሶስት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ ገብተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy