Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግና የምንግዴ አመራሩ ;ነፃ አስተያየት

0 471

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት “ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከድህነት የመውጣት ፍላጎቷ ጥልቅ ማሳያ ናቸው” በሚል ርዕስ ያወጣው መግለጫ እንዲህ ይላል፡- “በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እያንዳንዳቸው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት ይህን የህዳሴ ጉዞ የመምራትና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡”
ይህ መግለጫ፣ በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በትክክል የማይገልጽ፣ ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ራሳቸውን የሚያሞኙበት፣ ባለ ቁንጽል መረጃ ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡
ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ዘወትር እንደሚወተውቱን፣ በሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ከፍተኛ በጀት የተመደበላቸው የተለያዩ ግዙፍ (ሜጋ) የልማት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የፈለግነውን ያህል ልንክዳቸውና ልናጣጥላቸው ብንፈልግም  ጨርሶ ሊሳካልን የማይችል በገሀድ የሚታይ እውነታ ነው፡፡
እነዚህን የተለያዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ሰበብ ደግሞ በርካታ ቢሊዮን የህዝብ ገንዘብ እጅግ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በየዓመቱ ይባክናል፡፡ ይህ እኛ አሳምረን የምናውቀው ደረቅ እውነታ ነው፡፡ ለኢህአዴግና ለመንግስት ግን “ውሾን ያነሳ ውሻ” ተባብለው የሚማማሉበት፤ በየጊዜው በሚያወጡት የፕሮፓጋንዳ መግለጫ ጨርሶ ትንፍሽ የማይሉት “የውሽማ ሞት” ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መጠናቀቁን በማስመልከት መንግስት ያወጣው የ“አሳካሁት” ፕሮፓጋንዳ መግለጫና የግድቡ የህይወት ታሪክ የተፃፈበት ባህረ መዝገብ የያዘው እውነታ ለየቅል የሆነ፣ የሸገር ልጆች “ፍየል ቦሌ፤ ቅዝምዝም ጉለሌ” የሚሉት አይነት ነው፡፡ መንግስት የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆኑና ለማጠናቀቅ እየተረባረብኩባቸው ነው ያላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የሁለተኛው እቅድ አካል ሊሆኑ የቻሉት በአስማት ሳይሆን በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ሊያጠናቅቃቸው ባለመቻሉ ብቻ ነው፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ሀገሪቱ ተያይዘዋለች የተባለውን የህዳሴ ጉዞ የመምራትና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነቴን አጠናክሬ እቀጥላለሁ እያለ እየማለ ቢገዘትም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት ያላትን ጥልቅ ፍላጎት በግልጽ ያሳያሉ የተባሉትን የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እንዴት ያለ አመራር እየሰጠና  ምን ያህል ቢሊዮን ብር የህዝብ ሀብት እያባከነ እንደሚገኝ ሲታይ “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” ከማለት ውጭ ሌላ ለማለት ይቸግራል፡፡
ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ የኢህአዴግና የመንግስት የ‹‹አቦ ሰጡኝ›› አመራር ምን እንደሚመስልና በዚህ የተነሳም ምን ያህል የህዝብ ገንዘብ በአስደንጋጭ ሁኔታ እንደሚባክን ለማሳየት ማስረጃ ማቅረብ  ጨርሶ የሚገድ ነገር አይደለም። እንዲያው ነገሩን በቀላሉ ማስረዳት የሚያስችል አንድ ቀላል አብነት አቅርቡ ብንባል ግን የተንዳሆ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን መጥቀስ እንችላለን፡፡
የተንዳሆ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በ870 ሚሊዮን ብር ወጭ፣ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ታስቦ የተጀመረው በ1997 ዓ.ም ነበር። ልክ እንደ ሌሎቹ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሁሉ ይህም ፕሮጀክት ተጠናቀቀ የተባለው ከተያዘለት የሶስት ዓመት እቅድ ተጨማሪ አምስት አመታትን በልቶ በስምንት አመቱ ነው፡፡ የተንዳሆ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ የተባለው ከእቅዱ በላይ አምስት አመታትን በልቶ ብቻ ሳይሆን ከተያዘለት በጀት በላይ ከአራት ቢሊዮን ብር የላቀ የህዝብ ገንዘብ በተጨማሪ እምሽክ አድርጎ ነው፡፡
የተንዳሆ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከታቀደለት የጊዜ ገደብ በአምስት አመት ዘግይቶና ከተያዘለት በጀት ስድስት እጥፍ ወጪ አስወጥቶ ተጠናቀቀ መባሉ ምናልባት የተለመደ ሊሆንብን ይችላል። አስደናቂውና እጅግ አስደንጋጭ የሆነው ዋናው ጉዳይ ግን ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ አላግባብ የባከነበትና ለአመታት ሊዘገይበት የቻለበት ምክንያት ተብሎ የተገለፀው ነው፡፡
መንግስት በዋናነት ያቀረባቸው ምክንያቶች የልምድ ማነስ፣ ግንባታውን የሚያከናውኑት ተቋማት የአቅም ችግር፣ ግድቡ ያለ ዲዛይን መገንባቱና ግድቡን ለመገንባት የሚያስችል በቂ ጥናት አለመደረጉ የሚሉ ናቸው፡፡ ሌላው እጅግ አሳፋሪ የሆነው ጉዳይ ደግሞ መንግስት ከዚህ የ“እውር ድንብር” አመራሩ አገኘሁት ያለው ‹‹ትምህርት›› ነው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸውና በዶክተርነትና በኢንጂነርነት  ማዕረግ ጭምር የሚጠሩት የመንግስት ባለስልጣን የተገኘውን ትምህርት የገለፁት፤“ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የተንዳሆ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ትምህርት ሰጥቷል” በማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ገንዘብ አለአግባብ በማባከን የተገኘው ትምህርት ይኸው ነው፡፡ በአገርና በህዝብ ነገ ላይ መቀለድ   ይሏችኋል ይህ ነው፡፡
ከ1923 እስከ 1929 ዓ.ም ሰላሳኛው ፕሬዚዳንት በመሆን አሜሪካንን የመሩት ፕሬዚዳንት ካልቪን ኩልዲጅ ለአሜሪካ ኮንግረስ፣ ሰኔ 30 ቀን 1924 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር፤ “በህዝብ ገንዘብ አጠቃቀማችን ላይ ከፍተኛ ግዴለሽነትና አባካኝነት በግልጽ ይታይብናል፡፡ ይህ ያልሰለጠነ ህዝብና የበሰበሰ ስልጣኔ መገለጫ ነው፡፡ አሜሪካ ደግሞ ሁለቱንም አይደለችም” ብለው ነበር፡፡
እኛም ያልሰለጠነ ህዝብ አይደለንምና ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ከሚከተለው  የ“እውር ድንብር” አሰራርና  የህዝብ ገንዘብ አባካኝነት ሊታቀብና የተጠያቂነት ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን፤ በኢህአዴግና በሚመራው መንግስት የ‹‹አቦ ሰጡኝ›› አሰራር፣ በየዓመቱ እጅግ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ የሚባክነውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ “ይሁን ደህና” ብለው የሚሸከሙበትና ጫናውን የሚቋቋሙበት የጠና ጀርባና ወገብ የላቸውም፡፡ ይህን ለመሰለው አጓጉል የቅንጦት ጨዋታም ፈፅሞ አልደረሱም፡፡ admass

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy