Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያና ቻይና በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ በመስጠት ሊተባበሩ ነው

0 425

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያና ቻይና ቢያንስ በአንድ ዓመት በሚያስቀጣ የወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን በመስጠት ሊተባበሩ መሆኑ ታወቀ፡፡ሁለቱ አገሮች ይህንን ትብብር ለመጀመር ስምምነት የተፈራረሙት በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ ስምምነቱ ማክሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆነው የሁለቱ አገሮችን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም የሁለቱ አገሮች ሉዓላዊ እኩልነትን በማስጠበቅ ወንጀልን ለመከላከል ብቻ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ በማከል እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያ ያላትን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የንግድ ግንኙነትና ወደፊት ሊኖራት የሚችለውን ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን የመለዋወጥ ስምምነት እንደምታደርግ ይገልጻል፡፡

ከቻይና ጋር የተደረገው የወንጀለኞች ልውውጥ ስምምነትም በተጠቀሰው መርህ መሠረት የተፈረመ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱ፣ ዜጎችም ይህንን ዕድገት ተንተርሰው በቀላሉ ወደ ሁለቱም አገሮች መግባትና መውጣት መቻላቸው ታሳቢ ሲደረግ ስምምነቱን መፈራረም፣ ብሎም ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል፤›› በማለት ማብራሪያው ያስረዳል፡፡

ስምምነቱ በፓርላማ ከፀደቀ በኋላ ተፈጻሚነቱን የሚከታተለው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚሆን ረቂቅ አዋጁ ይገልጻል፡፡ አሳልፎ ለመስጠት የሚያበቃ የወንጀል ድርጊት ማለት፣ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄው በቀረበበት ወቅት በሁለቱም አገሮች ሕግ ቢያንስ በአንድ ዓመት ቀላል እስራት ሊያስቀጣ የሚችል የወንጀል ድርጊት መሆን እንዳለበት በረቂቁ ተካቷል፡፡ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄው የቀረበው በፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈ በኋላና ውሳኔውን ለማስፈጸም በሚሆንበት ጊዜ፣ ቀሪው የቅጣት ጊዜ ቢያንስ ስድስት ወራት ሊሆን እንደሚገባ በረቂቁ ተቀምጧል፡፡

ጥያቄው የቀረበለት አገር አሳልፎ የመስጠት ጥያቄውን ውድቅ ሊያደርግ የሚችለው ጥያቄው በቀረበለት አገር የወንጀል ድርጊቱ ፖለቲካዊ ይዘት አለው ተብሎ ሲታመን ወይም በዘሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በዜግነቱ፣ በፖለቲካ አመለካከቱና በመሰል ምክንያቶች ክስ ሊመሠረትበት ስለመሆኑ በቂ መረጃ ሲኖረው እንደሚሆን ረቂቁ ያመለክታል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተወያየው ፓርላማው ረቂቁን ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ አመራር እንደገለጹት፣ ስምምነቱ የአገሪቱን ጥቅም ለማስከበር ፋይዳው የላቀ ነው፡፡

ከቡቲክ ባለቤቶች እስከ ከፍተኛ ጥቅል አስመጪዎች ድረስ ቻይና የማይጓዝ አለመኖሩን የሚገልጹት ባለሥልጣኑ ከጉምሩክና ከውጭ ምንዛሪ ማጭበርበር ጋር የተገናኙ ወንጀሎችን ለመግታት ብሎም ግለሰቦችን በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና በፍትሐ ብሔርና ንግድ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ያደረጉትም ስምምነት ለፓርላማው ቀርቦ ለዝርዝር ዕይታ ተመርቷል፡፡  reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy