CURRENT

ኢትዮጵያን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

By Admin

March 29, 2017

በ2009 በጀት አመት ስድስት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያን ከጎበኙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለፀ።

ገቢው የተገኘው ከ439 ሺህ በላይ ከሚሆኑ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ነው።

የሚጠበቁ የእንስሳት ፓርኮችን ከጎበኙ ከ12 ሺ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችም ከ23 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ይህ የተገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ2009 በጀት አመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግምገማ ሲያካሂድ ነው።

በግምግማው ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም፥ ሀገራችን በአመት እስከ 1 ሚሊየን በሚደርሱ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ልትጎበኝ እንደምትችል የሚያመላክቱ ጥናቶች ቢኖሩም አፈጻጸሙ ግን ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

ለዚህም የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የሰው ሀይል እጥረት፣ ዘርፉ በቴክኖሎጂ አለመታገዙ እና የአስተርጓሚዎች ቁጥር እና ጥራት ማነስ በዘርፉ ላይ ከሚታዩ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል።

እነዚህን ችግሮች በመፍታት የሀገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪዎች ለማሳደግ ብሎም የቱሪስት ፍሰቱን እንዲጨምር ለማድረግ እና ከዘርፉም የሚፈለገውን ገቢ ለማግኘት በዘርፉ በሚታዩ ችግሮች ላይ ጥናቶች ለማካሄድ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።FBC