Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ ስምምነቱን ብትፈርም ምን ትጠቀማለች፣ ምን ታጣለች?

0 383

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዕምሯአዊ ንብረት ስምምነት ህግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ውጤቶች ጥበቃ የሚያገኙበትን ሥርዓት ለመቀየስና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት የተፈረሙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደ አብነት ይጠቀሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአዕምሯአዊ ንብረት መብት ጥበቃ መስክ በህግና በተቋም ግንባታ በብሄራዊ ደረጃ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ አሟልታ መገኘቷ በዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም ለመቀላቀል ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላት ይጠቀሳል፡፡

የዓለም አቀፍ የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ማቋቋሚያና ድርጅቱ ከሚያስተዳድራቸው ስምምነቶች መካከል የማራካሽና የፓሪስ ኢንዱስትሪያዊ ንብረት እንዲሁም የማድሪድ ዓለም አቀፍ የንግድ ምልክት ስምምነቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች እንዲፈረሙ የብሄራዊ የአዕምሯዊ ንብረት ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በፖሊሲው ላይ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አዕምሯአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግብዓት እያሰባሰበ ነው፡፡

ጽህፈት ቤቱ ሰሞኑን በኢሊሊ ሆቴል ለግማሽ ቀን ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ የፓሪስ ኮንቬንሽን አባልነትና የማድሪድ ፕሮቶኮልን ብትፈርም ልታጣ የምትችላቸው ነገሮች እንዳሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ፀድቆ ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊት በደንብ ሊፈተሽና በጥናትም ሊደገፍ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች የትሬድ ማርክና ፓተንት ወኪልና አማካሪ አቶ ደበበ ለገሠ «የፓሪስ ኮንቬንሽን አባል ለመሆንና የማድሪድ ፕሮቶኮልን ለመፈረም በዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል ዝግጅት ተደርጎ እንደሆነ ፤ ከኢትዮጵያ አየርመንገድ ተሞክሮ ወይም ልምድ መገኘቱን፤ አየርመንገዱ የራሱ ማሠልጠኛ ተቋም ቢኖረውም እንኳ በአሁኑ ጊዜ የስታር አልያንስ አባል በመሆኑ ደረጃውን ለማሟላት የሚያደርገው ጥረትና ተግዳሮት ምን እንደሆነ፤ ከአፍሪካ አገራት መካከል ስምምነቱን የፈረሙ ምን ያህሉ እንደሆኑ፤ እንዲሁም ያገኙት ጥቅምና ጉዳት በደንብ መፈተሽ አለባቸው» በማለት አባል የመሆኑ አስፈላጊነት በደንብ መታየት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የተወከሉት አቶ ወንዱ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪን ከሌሎች የመቅዳት እንጂ የማፍለቅ ደረጃ ላይ አለመድረሷን በማስታወስ ከቴክኖሎጂ መጠቀም ጋር ተያይዞ ችግር እንዳይገጥማት ስጋታቸውን በመግለጽ እንደ ደቡብ ኮሪያና ቻይና ያሉ አገሮች ተሞክሮ እንዲዳሰስ እንዲሁም የአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ፣ አዋጅና ደንቦችም ከሌሎች ማስፈጸሚያዎች ጋር የተናበቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ስምምነቱን መፈረም አንዳንድ ጥቅሞችንም እንደሚያሳጣ በመጥቀስ ገለፃቸውን የጀመሩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል በስብሰባው የተገኙት ዶክተር ብሩክ ኃይሌ «እንደ አገር ሲታይ ከምናገኘው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፤ እኛ ገና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በመሸጋገር ላይ ነን፤ ስምምንቱን መፈረም ያሉንን ትናንሽ ፈጠራዎች እንዳያሳጣን፤ ያደጉት የማድሪድ ፈራሚ አባል አገራት በፈለጉት መንገድ ጠምዝዘው ሊጠቀሙብንም ይችላሉ» ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስና መገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተከበሩ በቀለች ታዬ የፓሪስ ኮንቬንሽን አባል መሆንና የማድሪድ ፕሮቶኮልን መፈረም ተግዳሮቶች ቢኖሩትም ከዓለም ተገልሎ ለብቻ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ግንዛቤ ሊኖር እንደሚገባና ወደ መስመሩ ለመግባት የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አዕምሯአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ እሸቴ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንዳስረዱት፤ ኢትዮጵያ የፓሪስ ኮንቬንሽን አባል በመሆኗና የማድሪድ ፕሮቶኮልን በመፈረሟ የሚቀጭጭ ኢንዱስትሪም ሆነ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አይኖርም፤ ከሃያ ዓመት በፊት የአነስተኛ ፈጠራና የኢንዱስትሪ ዲዛይንን አካቶ የወጣውን ህግ ተፈጻሚነትንም የሚጋፋ አይሆንም፤ በህጉ ላይ የተቀመጡት ደንቦች ይከበራሉ፤ ስምምነቱ የውጭና የአገር ውስጥ አመልካቾች በሰለጠነ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ማመቻቸት እንጂ የአገራትን የንግድ ምልክት ደረጃ አያስቀርም፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም የሐረር፣ የይርጋጨፌና ሲዳሞ ቡና የንግድ ምልክቶችን ለማስመዝገብ ከአገር አገር በመዞር የተከፈለውን ዋጋ አስታውሰው፤ ለእጅ ጓንት መስሪያ ተፈላጊ ለሆነ የበግ ቆዳ የንግድ ምልክት ባለመኖሩ የኢትዮጵያ ያጣችውን ጥቅም ጠቅሰው፤ እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርትና አገልግሎቶች እንዳይታወቁ እንዳደረገና ጥቅሞችንም እያሳጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የንግድ ምልክት ማመልከቻ ሥርዓት ውስጥ መግባት ከስጋቱ ይልቅ ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ተቋሙን በሰው ኃይል ማደራጀትና አሰራሩን ማዘመን በተመለከተ በአስተያየት ሰጭዎቹ የተሰነዘሩትን ሃሳቦች በመቀበል የማሻሻል እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ የፓሪስ ኮንቬንሽን አባልነትና የማድሪድ ፕሮቶኮልን ብትፈርም ምን ትጠቀማለች፣ ምንስ ታጣለች፣ እስከ ዛሬስ ባለመፈረሟ ምን ቀረባት የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከዓለምአቀፍ ስምምነቶቹ መካከል የፓሪስ ኢንዱስትሪያዊ ንብረት ስምምነት አንዱ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ.በ1883 በፓሪስ ከተማ መፈረሙን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ይህንን ስምምነት ሳትፈርም ቆይታለች፡፡

ለምለም መንግስቱ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy