ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ በሚፈጸም ማጭበርበር ምክንያት በየዓመቱ ማግኘት የሚገባትን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ እንደምታጣ ተነገረ።
ኢትዮ ቴሌኮም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸው፥ የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመቆጣጠር በቴክኖሎጂ የታገዘ የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
የኩባንያው የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱራሂም አህመድ፥ መልኩን እየቀያየረ የመጣው የቴሌኮም ማጭበርበር ተግባር ከመደበኛ ስልክ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ትኩረቱን እንዳደረገ ተናግረዋል።
የወንጀል ድርጊቱ በሃገራዊ ደህንነት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት አቶ አብዱራሂም፥ በእንዲህ መልኩ ገቢዉን የሚያገኙ አካላትም በአብዛኛው ለሽብር ድርጊት የሚያውሉ መሆናቸውን አለም አቀፍ ተሞክሮዎች ይጠቁማል ብለዋል።
ከሀገር ውስጥ ጀምሮ በመላው አለም መረባቸዉን የዘረጉ ህገወጥ አካላት ሀገሪቱ ማግኝት የሚገባትን ገቢ እያሳጧት ይገኛሉ ያሉት አቶ አብዱራሂም፥ በዚህ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችን አድኖ ለህገ ለማቅረብና የወጣውን አዋጅ በማስተግበር ረገድ በዚህ አመት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራትም 12 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ብለዋል።
ከፌደራል ፖሊስ እና ከብሄራዊ መረጃ መረብ ደህነት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ወንጀሉን በጥምረት ለመከላከል እየተሰራ ሲሆን፥ በህገ ወጥ ተግባሩ ላይ የተሰማሩ ተጨማሪ አካላት ላይ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ አብዱራሂም ገልፀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት በቴሌኮም ማጭበርበር ከኢንተርኔት የባከነ ገቢ መጠንን ከ2 በመቶ በታች ለማድረስ አቅዶ 0 ነጥብ 13 በመቶ ማድረሱን አስታውቋል።
የአሰራር እና ሲስተም ቁጥጥር ማከናወን፣ የሁሉም ደንበኞች የውል ስምምነት በመረጃ ቋት ውስጥ እንዲያዝ ማድረግ እና ከቴሌኮም ኦፕሬተሮች ጋር የውል ስምምነትን ማጠናከር እንዲሀም ሀገር አቀፍ የዲጅታል መታወቂያን ማዘጋጀት ለችግሩ በመፍትሄነት የተቀመጡ ናቸዉ።
ለደንበኞች አሰተማማኝ አገልግሎት መስጠትም ቀጣይ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ነው።
ተቋሙ እነዚህን ተግባራት በተጠናከረ መልኩ በማከናወን እየተፈጸሙ ያሉ ማጭበርበሮችን በመከላከል ሃገሪቱ ተገቢውን ገቢ እንድታገኝ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም ዘርፉ ለአጭበርባሪዎች የተጋለጠ መሆኑ የደረሰበት በ1994 ዓ.ም እንደሆነ ነው ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።
በወቅቱም 14 ግለሰቦች መደበኛ ስልኮችን ከውጭ በህገወጥ መልኩ ካስገቡት መሳሪያ ጋር በማስተሳሰር መንግስትን ከፍተኛ ገቢ እንዳሳጡ በመረጋገጡ በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።