NEWS

ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ አዲስ የፖሊሲ አማራጭ እንደምትከተል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

By Admin

March 18, 2017

ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ስታራምድ የቆየችውን ፖሊስ በመቀየር ዘላቂ ሰላምን የሚፈጥር የፖሊሲ አማራጭ በቅርቡ ተግባራዊ እንደምታደርግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህንን የገለጹት ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

በምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡበት ጥያቄ፣ ‹‹የሻዕቢያ መንግሥት እኩይ ተግባርን እስከ መቼ ነው ማስታመም የምንችለው?›› የሚል ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝበት ፖሊሲ ማስቀመጥ እንዳለብን ግንዛቤ ተወስዷል፤›› ብለዋል፡፡ አዲስ የፖሊሲ አማራጭ ስላሉት ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም፣ ጥናቱ በአሁኑ ወቅት የተጠናቀቀ መሆኑንና የሚመለከተው አካል በቅርቡ ካፀደቀው በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገባ  ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ካበቃ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል የጦርነትና የሰላም አልባ ሁኔታ ተፈጥሮ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ኤርትራ ለምታደርገው እያንዳንዱ ትንኮሳ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ተመጣጣኝ ወታደራዊ ዕርምጃ እየወሰደች ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የተከተለችው ፖሊሲ የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዳላመጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹ላለፉት በርካታ ዓመታት ለሰላም የዘረጋናቸው እጆች ብዙም ተቀባይነት ማግኘት ባለመቻላቸው፣ እንዲሁም በኤርትራ መንግሥት ግትርነትና ማናለብኝነት ምክንያት እስካሁን ድረስ የምንፈልገውን ውጤት አላገኘንም፤›› ብለዋል፡፡ reporter