Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ አገደ

0 571

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይካሄድ እንቅፋት ነበሩ ከተባሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው፣ የአገር አቀፉ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና የአመራሮች ምርጫ ተሰርዞ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡

የዘርፍ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ እንዲታገድና አዲስ ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ እንዲካሄድ የተወሰነው፣ የዘርፍ ምክር ቤቶችን ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከተውና ጉዳዩን ሲያጣራ በቆየው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡

ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ አገር አቀፉ የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ያገደው የምርጫ ሒደቱ ሕጋዊ ጥሰቶች ያሉበት መሆኑ በመረጋገጡ ነው፡፡ በተለይ ከዘርፍ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጭ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ በተደጋጋሚ የተመረጡ ግለሰቦች መኖራቸው ምርጫውን የሚያስደግም በመሆኑ፣ አዳዲስ አመራሮችን ለመምረጥ ድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ሊወሰን ችሏል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የተዋቀሩ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን ወቅታዊ ችግር በተመለከተ ንግድ ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ማክሰኞ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ የዘርፍ ምክር ቤቱ ምርጫ ስለመታገዱ አረጋግጧል፡፡

ይኸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደብዳቤ ላለፉት አሥር ዓመታት ዘርፍ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔርን ጨምሮ፣ አምስት የቦርድ አባላትን በስም በመጥቀስ ከመተዳደሪያ ደንባቸው ውጭ በተደጋጋሚ መመረጣቸው የሚያሳይ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን የሚያመላክት ጭምር ነው  ተብሏል፡፡

በንግድ ሚኒስቴር የአክሲዮን ማኅበራትና የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን መሐመድ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቀረበበትን አቤቱታ ይከታተል የነበረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባደረገው ማጣራት የመጨረሻ ውሳኔውን ሰጥቷል ብለዋል፡፡ ዕርምጃው የተወሰደውም ከዘርፍ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ከሁለት ጊዜ በላይ በምርጫ የተመረጡና ወደ አመራር የመጡ እንዳሉ በማረጋገጡ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዘርፍ ምክር ቤቱ ሁሉ ከታች ያሉ ምክር ቤቶች በአግባቡ ሳይወከሉ ወደ አመራር መጥተዋል ተብለው ቅሬታ በቀረበባቸው ንግድ ምክር ቤቶች ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ ተወስዷል ያሉት አቶ ኑረዲን፣ ከነዚህም ውስጥ በቀዳሚነት የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጠቅሰዋል፡፡ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫን በተመለከተ በተደረገ ማጣራት፣ የምርጫ ሕግንና የንግድ ምክር ቤቱን የምርጫ ደንብ ያልጠበቀ መሆኑን የአማራ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ በማረጋገጡ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲደገም ከሦስት ሳምንታት በፊት ውሳኔ ስለመሰጠቱም አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩት በተዋረድ ከታች ያሉ ምክር ቤቶች ምርጫ ያለመከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ በሆነ አሠራር ያላለፉ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ አሁን ግን በማጣራቱ ሥራ የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ምርጫዎቹ ከሥር ጀምሮ ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡

ምርጫዎቹንም ለማካሄድ ንግድ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች በጋራ በመሆን የተዋረድ ምርጫዎችን እንዲያስፈጽሙ ውሳኔ ላይ መደረሱን የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ ለዚህም አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል፡፡

የሕግ ጥሰት ታይቶባቸዋል የተባሉት ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ድጋሚ ምርጫ የሚያኬዱትም በንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅና በንግድ ምክር ቤቶቹ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ይሆናል፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮች እንዲሁም የአማራ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ እንዲህ ያለው ውሳኔ ላይ የደረሱት ከየንግድ ምክር ቤቶቹ አባላት በተደጋጋሚ የቀረቡትን ቅሬታዎች በመመርመር ነው፡፡ ከየክልሉ በቀረቡ ቅሬታዎች ምክንያት የዋናው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ሊካሄድ አልቻለም ያሉት አቶ ኑረዲን፣ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነው በአዋጁ በግልጽ እንደተቀመጠው በተዋረድ ምርጫዎች ባለመደረጋቸው ነው ብለዋል፡፡ ከታች በወረዳ፣ በዞንና በከተማ የሚገኙ ምክር ቤቶች ፍትሐዊና አሳታፊ የሆኑ ምርጫዎች መካሄዳቸው ሲረጋገጥም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከታች ያሉት በአግባቡ ምርጫቸውን ሳያካሂዱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል፣ ንግድ ምክር ቤት ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረውን ጉባዔና ምርጫ ንግድ ሚኒስቴር ማገዱን አስታውሰዋል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔው እንዳይካሄድ ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች በማጥራት ከ15 እስከ 30 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ጉባዔውን እንዲካሄድ የሚያደርግ መሆኑንም ንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በአንዳንድ ወገኖች ንግድ ሚኒቴርም ሆነ የክልል ንግድ ቢሮዎች በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለባቸውም የሚለውን አስተያየት ትክክል አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 341/95 እነዚህን ማኅበራት የማደራጀት፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው ለንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ ሚኒስቴሩ ይህንን ሥልጣኑን መጠቀም ይቻላል ተብሏል፡፡

በ2003 ዓ.ም. ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለሁለት ሲከፈል በአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ደግሞ የንግድ ዘርፉን በተመለከተ ንግድ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ደግሞ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲመራ መደረጉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

ስለዚህ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ 2009 ዓ.ም.  ድረስ አምስት የሚሆኑ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች አባላት በአዋጁ መሠረት ምርጫ አለማድረጋቸውንና በተመዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ሕጉን ሳይጠብቁ ምርጫዎች እየተካሄዱ ያለመሆኑን የሚገልጹ አቤቱታዎች የቀረቡትም በሕግ መሠረት የሚያገባው ንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

ቅሬታ የቀረበባቸውም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የትግራይ ክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የደቡብ ንግድ ምክር ቤት ምርጫዎች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሌላ በቀሪዎቹ ላይ ተመሳሳይ መረጃ እየተሰበሰበ ስለመሆኑም ከገለጻው ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአገሪቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሁን ያሉበት አቋም በርካታ ችግሮች የሚታይባቸውም ነው ተብሏል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ግን ንግድ ሚኒስቴር አልዘገየም ወይ?  የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኑረዲን፣ ንግድ ሚኒስቴር እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መከታተል የጀመረው በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ነው ብለዋል፡፡ ከዚያ በፊት ንግድ ሚኒስቴር ሲሠራ የነበረው ምርጫዎች ሲደረጉ መካሄዳቸውን፤ ከ2003 ወዲህ ደግሞ የጋራ መድረኩን የመምራት ሥራ ብቻ ነበር፡፡

አሁን ግን ባለፉት ሁለት ወራት የምናያቸው ነገሮች ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ከማቋቋሚያ አዋጁና ከራሳቸውም ደንብ የወጡ መሆናቸውን ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ንግድ ሚኒስቴር የመጨረሻ ውሳኔ እየሰጠ ነው ያሉት አቶ ኑረዲን፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው በመሆኑም ምርጫ እንዲራዘም ጭምር ውሳኔ እስከመስጠት ደርሰዋል ብለዋል፡፡ ለውሳኔው መዘግየታቸውን ግን አምነዋል፡፡

የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሉባቸው የተባሉትን ችግሮች ለመፈተሽ በማጣራት ሥራው ላይ ብዙ ችግሮች እንደገጠሟቸው የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ግን ንግድ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ዕርምጃ ሁሉ እንደሚወስድና በትክክል ምርጫዎች እንዲካሄዱ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉ አመራሮች ዕውን  ትክክለኛ ነጋዴዎች ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ጉዳይ የችግሩ ዋና ምንጭ መሆኑን በመጥቀስም፣ በንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግም በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች አሉን የሚሏቸው አባላት ላይም የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን በማረጋገጥ፣ ከዚህ በኋላ አደረጃጀታቸው እንዲስተካከል ይደረጋል ብለዋል፡፡ አሁን ግን ምክር ቤቶች ላሉባቸው ችግሮች አንዱ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

ስለዚህ ይህንን አዋጅ ለማሻሻል የመጀመሪያው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ በቅርቡም ውይይት ተደርጎበት እንዲፀድቅ ይደረጋል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ዕገዳ የተጣለበት የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ምርጫቸውን ለማካሄድ አልቻሉም፡፡

የተሰጠው የጊዜ ገደብ አንድ ሳምንት የቀረው ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመደረጉ ታውቋል፡፡ እንደውም በአቶ ጌታቸው አየነው የሚመራው  ቦርድ ቢሮው ይደገም ያለውን ትዕዛዝ በመቃወም ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ ደግሞ የክልሉን ምርጫ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዳይካሄድ እንቅፋት ሆኗል እየተባለ ነው፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ግን በሕጉ መሠረት በክልሉ ንግድ ቢሮ በኩል ምርጫው በአጭር ጊዜ እንዲካሄድ ይደረጋል ብሏል፡፡ ካልሆነም በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የምዝገባ ሰርተፍኬቱን እስከመሰረዝ የሚደርስ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል ተብሏል፡፡

አሁን በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ግን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የክልሉ ንግድ ቢሮ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ምርጫውን ለማስፈጸም ይሠራሉ ተብሏል፡፡ reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy