እንግሊዝ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደምትፈልግ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ገለጹ።ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የእንግሊዙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆንሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ እንግሊዝ አገሪቷ በልማትና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የምታደርገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ በጋራ መስራት ትፈልጋለች።
አገሪቷ የምታከናውናቸውን የልማት ተግባራት በመደገፍ “የእንግሊዝ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ከመንግስትም ባለፈ በግሌም እጥራለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን በማጠናከር የእንግሊዝ ባለኃብቶች በአገሪቷ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል።የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል።
በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታትና ሰላም ለማምጣት ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት ድጋፏን እንደምትቀጥል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆንሰን ቃል መግባታቸውን አውስተዋል።