CURRENT

ከአዲስ አበባ ካርቱም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጀመረ

By Admin

March 12, 2017

ከአዲስ አበባ ሱዳን ካርቱም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ተጀምሯል።

አገልግሎቱ በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን፥ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት ከማጎልበት አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን፥ የትራንስፖርት ባለስልጣን ገልጿል።

በባለስልጣኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በላቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ የአገልግሎቱ መጀመር በካርቱም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችና በመካካለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሁለቱም ሀገራት ዜጎች አማራጭ የመገናኛ ዘዴ ይሆናል።

ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አገልግሎቱን ለማስጀመርም ከኢትዮጵያ በኩል አባይ፣ ኢትዮ ባስ፣ ጎልደንና የሰላም ልዩ አውቶብሶች ተመርጠዋል።

የአንድ ጉዞ ዋጋም 60 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ በኩል ለሚቆረጥ ትኬት በእለቱ የምንዛሬ ተመን መሰረት በኢትዮጵያ ብር መቁረጥ ይቻላል።

ከአዲስ አበባ የሚነሱት አውቶብሶችም መነሻቸው መስቀል አደባባይ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል።