ዳንኤል ካሊናካ ይባላል። የኡጋንዳው ዴይሊ ሞኒተር ዘጋቢ ነው። ስለአባይ ወንዝ እና ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጥብቆ ያስባል። ለረጅም ዓመታት በዚህ ወንዝ ላይ ግዙፍ ግድብ ለመገንባት ስታልም የቆየችው ኢትዮጵያ፤ በ1980ዎቹ የረሃብና የድህነት መገለጫ በሆነው የህፃን ልጅ ፖስተር ትታወቅ እንደነበርና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቀጣይ ዘመንዋን ብሩህ ለማድረግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን በዘገባው ያትታል።
እንደ ዘጋቢው፣ ሀገሪቷ ከስድስት ዓመት በፊት ከ6 ሺ በላይ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ግድብ በአባይ ወንዝ ላይ እንደምትገነባ ማንም ባልጠበቀው መልኩ ይፋ በማድረግ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በርካታ ኢንጂነሮችና ሌሎች የግንባታ ሰራተኞችን በማሰማራት ወደ ግንባታው ተሸጋግራለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ሀገሪቱ የፋብሪካዎቿን የኤሌክትሪክ ሃይል ጥማት ከማርካት አልፋ፤ ለአካባቢው ሃገራት ጭምር የኤሌክትሪክ ሃይል በርካሽ ዋጋ ለማቅረብ እቅዱ አላት። ሀገሮቹም ይህን እድል ለመጠቀም የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት ርብርብ እያደረጉ ናቸው። ግብፅና ሱዳን ግንባታውን አስመልክቶ ለዘመናት ሲያራምዱ የቆዩትን አፍራሽ አቋም ወደ ጎን በመተው ይህን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።
«የዩጋንዳ ፖሊሲ አውጪዎችና ፈፃሚዎች የኢትዮጵያውያንን እግር እንድትከተሉ ትመከራላችሁ፤ ጥቂት ቃል በመግባት በርካታ የልማት ሥራዎችን መተግበር እንዴት እንደሚቻል ኢትዮጵያውያንን ልትጠይቋቸው ይገባል» ያለው ዘገቢው፣ ይህም የማይጨበጥ ንድፈ ሃሳብ እንዳልሆነም አስፍሯል።
ወደ አገራችን የመገናኛ ብዙሃን አውነታ ስንመለስ ግን ሀፍረት እንዲሰማን የሚያደርግ እውነታ እንመለከታለን። በሳምንት የ1 ደቂቃ “ቋሚ” ጊዜ መድቦ ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ታላቅነት ለመመስከር ዩጋንዳዊ መሆን ብቻ በቂ ይመስላል። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ልዩ ስፍራ ይኖረዋል።
የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተአምራዊ መስታወታችን ነው ሲባል ምን ማለት ስለመሆኑ የመገናኛ ብዙሃኖቻችን የተረዱት አይመስልም። ፕሮጀክቱ የቆምንበትን፣ የምንሄድበትን፣ ያለፍንበትን፣ የምናስበውን፣ የምናልመውን የምናይበት ሀገራዊ መስታወታችን ነው። መልካችንና ልካችን በደማቁ የሰፈረበት ውድ ገፃችን ነው። ሀገር የሚያስተሳስር ብሔራዊ መዝሙራችን ነው። ቢነበብ፣ ቢተረክ፣ ቢወሳ፣ ቢሞገስ የማይሰለች፤ በየሬዲዮኑ፣ በየቲሌቪዥኑ፣ በየጋዜጣውና በየመፅሄቱ፣ በየስብሰባው፣ በየገበታው፣ በየአልጋው፣ በየጫካው፣ በየተራራው ቢወራለት ቢዘመርለት የማይሰለች ጣፋጭ ሀገራዊ እውነታችን ነው!!!
በመገናኛ ብዙሃኖቻችን ግን ይህ እውነታ በገሀድ አይንፀባረቅም። ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ መገናኛ ብዙሃኑ የህዳሴውን ግድብ በሚያሳፍር መልኩ ችላ ብለውታል። ይህም ህዳሴ ግድባችንን ከልብ ዘንግተነዋል ለማለት ያስደፍራል።
መንግሥት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሄራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ከማቋቋም አንስቶ ልዩ ድረ ገፆችን በመክፈት፣ ስልጠናዎችን በመስጠት እና የማነቃቂያ ህዝባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ጭምር የራሱን ድርሻ እንደ አቅሙ እየተወጣ ይገኛል። ከዚህ አኳያ እኛ የት ላይ ነን? ብሎ ራስን መለስ ብሎ ማየት ግን ተገቢ ነው።
የመገናኛ ብዙሃኖቻችን ላይ የሚታየው ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት ለወሬም የሚመች አይነት አይደለም። የአፈጻጸም፣ የመዋቅር፣ የእውቀት እና የአመለካከት (ፖለቲካዊ) ችግሮች መገናኛ ብዙሃኑን በዋናነት ተብትበው የያዟቸው በመሆኑ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ የታላቅነቱን ያህል ሊነገርለት አልቻለም።
አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ የተገነቡ ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ግድቦች በየሀገራቱ የመገናኛ ብዙሃን እንዴት እንደ ተዘገቡ ምስክር መጥቀስ አያስፈልግም፤ በእርግጥ የኡጋንዳው ጋዜጠኛ የዳንኤል እማኝነት በቂ ነው።
ከግልገል ጊቤ III መመረቅ ጋር በማያያዘ፤ ሲ.ኤን. ኤንን. ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሲያስተጋቡት የነበረውን ዘገባ በተለይ ጋዜጠኞች ስንቶቻችን ተከታትለነው ይሆን?
እዚህ ላይ የመገናኛ ብዙሃኖቻችን በሙሉ ዝምታን መርጠዋል አለማለታችን ልብ ይባልልን። የመሰረት ድንጋይ ሲጣል፣ አባይ ተፈጥሮአዊ አቅጣጫውን ሲቀይር፣ ግንባታው የተጀመረበት ቀን ልደቱ ሲከበር እና የግብጾች ድምፅ ሲሰማ ወዘተ… እየጠበቁ (የአዘጋገቡ ነገር እንዳለ ሆኖ) የዜና ሽፋን ሰጥተዋል፡፡ ይህ ግን በፍጹም በቂ አይደለም።
በየሰከንዱ ስለ አርሴናልና ማንቼስተር ግብግብ፣ ስለሜሲ እና ሮናልዶ የፀጉር ቁርጥ ሰፊ የአየር ጊዜ እየሰጠን ስለህዳሴው ግድብ አንዳች ነገር አለመተንፈስ “ብሔራዊ ወንጀል” ነው። በዘገባዎቻችን ከሻኪራ ዳንኪራዎች፣ ከቢዮንሴ አለባበስ፣ ከሌዲ ጋጋ ቀሚሶች ይልቅ አባይ የኩራት ድምፁን እያሰማ መፍሰስ አለበት።
የህዳሴ ግድባችን ጉዳይ ‘ሁኔታን’ እና ‘በአላትን’ እየጠበቁ ብቻ የሚያነሱት አይደለም። ሁሌም ራሱን የቻለ በአል ነው። ከዚህ መሰረተ ሀሳብ በመነሳት የህዳሴ ግድባችን በበቂ መልኩ አለመዘገባችንን እያጤንን እንደ አገር ሁላችንም በጋራ በመስራት አገራዊ ኩራታችንን የበለጠ ከፍ ለማድረግ እንጣር።ethpress