CURRENT

ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት ጦርነትና ድህነትን ለመሸሽ ሳይሆን ኑሮን ለማሻሻል እንደሆነ አጥኚዎች ገለጹ

By Admin

March 15, 2017

በተለይ ከአፍሪካ ቀንድ ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደት ምክንያት ከዚህ በፊት እንደሚባለው ድህነትና ጦርነት ሳይሆን፣ ኑሮን የበለጠ የማሻሻል ፍላጎት መሆኑን አጥኚዎች ገለጹ፡፡

የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ‹‹ከአፍሪካ ቀንድ የሚደረገው ስደትና ውጤቱ›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የግማሽ ቀን ውይይት፣ ከቀጣናው በተለይ ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደት ምክንያት ከድህነትና ከጦርነት የተነሳ እንዳልሆነ አጥኚዎች አስረድተዋል፡፡

‹‹ዘ ሆርን ኢኮኖሚክ ኤንድ ሶሻል ፖሊሲ ኢንስቲትዩት›› የተሰኘ የፖሊሲ ምርምር ተቋም ባዘጋጀው በዚሁ የውይይት መድረክ ጥናት ያቀረቡት አቶ አሮን ተክለዝጊና አቶ ደምሴ ፈንታዬ፣ በኢጋድ ቀጣና (አፍሪካ ቀንድ) ከአገር አገር የሚደረግ ስደትና ከቀጣናው ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት ከዚህ በፊት በምዕራባዊያን እንደሚባለው ከድህነትና ከጦርነት የመነጨ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፣ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት የተመዘገበ ቢሆንም የስደተኞች ቁጥር በእሱ ልክ ከፍ ብሏል፡፡

አቶ አሮን በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) የሚሠሩ ሲሆን፣ ‹‹እስከ ዛሬ በአውሮፓ የተነገረን አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ብሎም ከመላ አፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት በዋናነት የተሻለ ሕይወትና ኑሮ ፍለጋ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የፖለቲካል ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ደምሴ በበኩላቸው፣ የተፈጠረው ኢኮኖሚ ዕድገት በቂ የሥራ ዕድል አለመፍጠሩ የሥራ አጦች ቁጥር ከፍ እንዲል ምክንያት ቢሆንም ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደት ግን እንደሚባለው ከድህነት የተነሳ ሳይሆን፣ ከማዕከላዊ እስከ ከፍ ያለ ገቢ ባላቸው ሰዎች የሚደረግና ለተሻለ ሕይወት የሚደረግ ጉዞ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአፍሪካ ቀንድ የሚደረገው ስደት 75 በመቶ በጎረቤቶች መካከል ነው፡፡ 3.5 ሚሊዮን ስደተኞች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ 2.46 ሚሊዮን የሚሆኑት ከአገር አገር በመዘዋወር በቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡ አካባቢው ከአቅም በላይ ስደተኞች ተሸክሞ እንደሚኖርም አስምረውበታል፡፡

ሁለቱም ተመራማሪዎች በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ያለው ከአገር ወደ አገር ስደት ነፃ የሰው ኃይል ዝውውር ቢፈቀድ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል እንደሆነ በመፍትሔነት ጠቁመዋል፡፡ ብዙዎቹ የሚመኙትን ኑሮ እዚሁ በጎረቤት አገር ሠርተው ሊያገኙ እንደሚችሉም አመልክተዋል፡፡