Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዘመነኛው የለቅሶ መስተንግዶ

0 2,543

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለቅሶ ለመድረስ የሄደበት የዘመዱ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ጥቁር በጥቁር የለበሰች አንዲት ሴት ለቀስተኞቹን ታስተናግዳለች፡፡ ቡፌ ላይ የተደረደሩትን ምግቦች እንዲያነሱ፣ የሚጠጣም እንዲያገኙ ታስተባብራለች፡፡ ናኦድ አፈወርቅ (ስም ተቀይሯል) ሴትዮዋን ከዚህ ቀደም ዓይቷት ስለማያውቅ አብዝታ ሽር ጉድ ማለቷ ግራ አጋባው፡፡ ምናልባትም የማያውቃት የሩቅ ዘመድ ትሆናለች ብሎ ለራሱ ምላሽ ሰጠ፡፡ ሴትዮዋ ግን ዘመድ እንደሚያደርገው ትኩረቷ ሐዘንተኞችን ማጽናናት ሳይሆን መስተንግዶው በተገቢው መንገድ መከናወኑን መከታተል መሆኑን አስተዋለ፡፡ ይሄኔ ስለማንነቷ ዘመዶቹን ጠየቀ፡፡ ዘመዱ ከተቀበሩበት ዕለት ጀምሮ ለቅሶ ለሚደርሱ ሰዎች ቁርስ፣ ምሳና እራት ለማዘጋጀት የተቀጠረች ባለሙያ መሆኗን ገለጹለት፡፡

የሴትዮዋ መደበኛ ሥራ ለቅሶ ላይ ምግብና መጠጥ ማቅረብና የሚያስተናግዱ ሰዎችንም ማሰማራት ነው፡፡ የሟች ዘመዶች ወይም ጓደኞች ለቀስተኞችን ምሳ ወይም እራት ማብላት ከፈለጉም ሴትዮዋን መቅጠር ይቻላል፡፡ በተመጋቢዎች ቁጥርና በሚዘጋጀው ምግብ ዓይነት (ከአሥር ሊበልጥ የሚችል) የሚከፈለው ገንዘብ ይተመናል፡፡ ናኦድም ለሟች ዘመዱ ቤተሰቦች የእዝን እንዲሆን አንድ ቀን ለቀስተኞቹን ለማብላት ተራ ገባ፡፡ ተራው በደረሰበት ቀን ለተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ከመስተንግዶ ጋር በአጠቃላይ ወደ 20,000 ብር እንደከፈለ ይናገራል፡፡

‹‹ከቀብሩ በኋላ የሟች ቤተሰቦች የለቅሶውን መስተንግዶ እንድትይዝላቸው ከቀጠሯት በተጨማሪ 12 ቀን ያህል እዛው ለቅሶ ቤት ሆና ማብላት ለሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎት ትሰጥ ነበር፤›› ሲልም ይገልጻል፡፡

ለቀስተኞችን ማብላት እንደየአካባቢው ባህል የተለያየ ሒደት ቢኖረውም፣ በአብዛኛው በዕድር አባላት፣ በጎረቤቶች ወይም በዘመድ አዝማድ ይከናወናል፡፡ የዕድር አባላት በሐዘንተኞች ቤት በየተራ ምግብ ያዘጋጃሉ፤ ያስተናግዳሉም፡፡ ለለቅሶ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማለትም ከድንኳን ጀምሮ ድስትና ሰሀን የሚቀርበውም በዕድር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዕድር የሚሸፍነው ቦታ በቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች ወይም ለለቅሶ የተለያየ አገልግሎት በሚሰጡ ግለሰቦችም ሲሸፈን ይስተዋላል፡፡ ምግብና መጠጥ አቅርቦት እንደማሳያ ተጠቀሰ እንጂ፣ ሬሳ መገነዝ፣ በሟች ቤት ሻማና አበባ ማስቀመጥ፣ ሬሳውንና ለቀስተኞችን ቀብር ቦታ መውሰድና ከቀብር መልስ ማስተናገድን ያጠቃልላል፡፡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም ዕድር ያላቸውና የሌላቸው ናቸው፡፡

ናኦድ እንደሚለው፣ ዕድር ቢኖርም ባይኖርም ከለቅሶ ጋር የተያያዙ የሥራ ኃላፊነቶችን ለቀብር አስፈጻሚዎች መስጠት የሚመርጡ ሰዎች አጋጥመውታል፡፡ ይህ  ከሰዎች የገንዘብ አቅም ጋር የሚሄድ ቢሆንም፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችም አገልግሎቱን ሲመርጡ ይታያሉ፡፡ አስከሬን ከመገነዝ አንስቶ ሐዘንተኞችን እስከማስተናገድ የሚደርሱ የለቅሶ ሥራ ኃላፊነቶች ለንግድ ተቋማት መስጠት ቀድሞ ከነበረው ልምድ በተለየ ብቅ ማለቱም ይስተዋላል፡፡

አንድ ማኅበረሰብ ተባብሮ ከሚያከናውናቸው ጉዳዮች ሐዘን አንዱ መሆኑ እሙን ነው፡፡ የሥራ ኃላፊነቶችን መጋራት ማኅበራዊ መስተጋብሩን ያጠናክራል ብለው የሚያምኑ ግለሰቦች፣ የቀብር አስጻሚዎች ሚና እየጎላ መምጣቱ እርስ በርስ ያለንን ትስስር አያላላውምን? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ባለንበት ዘመን የሰዎች ግላዊ ሕይወት እንዲሁም የሥራ ጫናዎች በርካታ እንደመሆናቸውና ጊዜውም የሩጫ ከመሆኑ አንፃር ገንዘብ ሊሸፍናቸው የሚችሉ ነገሮችን በገንዘብ ሸፍኖ ጊዜን ማዳን የግድ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አገልግሎቱ አሁን ካለውም በበለጠ መስፋፋት እንዳለበት ያምናሉ፡፡

በናኦድ አስተያየት፣ ለቀብር አስፈጻሚዎች መሰጠት ያለባቸውና ለሟቹ ቅርብ በሆኑ ሰዎች መሸፈን የሚገባቸው ኃላፊነቶች አሉ፡፡ ለቀስተኞችን ለማብላት ሲፈለግ በዕድር አባላት ወይም በዘመድ ላይ ሥራውን ከመጫን ባለሙያዎች ቀጥሮ ማሠራት ይመረጣል፡፡ የአንድ ዕድር አባላት ድንኳን ለመትከል፣ ምግብ ለማዘጋጀት፣ ለማስተናገድና የሟች ቤተሰቦችን እያጽናኑ ለማምሸት ተራ ይይዛሉ፡፡ በዚህ ተራ መሠረት ግዴታውን ያልተወጣ አባል የሚቀጣበት አግባብም አለ፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኃላፊነት ክፍፍሉን መወጣት ለብዙዎች ባይከብድም፣ ዛሬ ዛሬ ግላዊ ግዴታዎችን ለማከናወንም ጊዜ ስለሚያጥር እንደ ቀብር አስፈጻሚ ያሉ አማራጮችን መጠቀም የግድ ይሆናል፡፡

አንዳንዶች፣ ከጊዜና ከሰው ኃይል እጥረት አንፃር ከባድ ሥራዎች በቀብር አስፈጻሚዎች መሠራታቸውን ቢደግፉም፣ ከሟች ቤተሰቦች ወይም ጓደኞች ውጭ ማንም ሰው ሊያከናውናቸው የማይገቡ ነገሮች በቀብር አስፈጻሚዎች መካሄዳቸውን ይነቅፋሉ፡፡ ናኦድም፣ ‹‹ሬሳ ወደ ቀብር ሥፍራ ከመሄዱ በፊት የሬሳ ሳጥኑን ከቤት የሚያወጡት የሟቹ የቅርብ ዘመዶች መሆን ሲገባቸው በቀብር አስፈጻሚዎች ታጅቦ ይወጣል፤›› ይላል፡፡ ለሟች ቅርብ የሆኑ ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹባቸው ነገሮችን ገንዘብ ስለተከፈለ ብቻ በሌላ ግለሰብ እንዲከናወኑ መፍቀድ አሁን ብቅ ያለ ልማድ መሆኑን ያክላል፡፡

የከተሜነት መስፋፋት ተፅዕኖ ካሳደረባቸው ማኅበራዊ መስተጋብሮች መካከል ለቅሶ አንዱ እንደመሆኑ፣ የቀድሞውና የአሁኑ የሐዘን ሥርዓት ልዩነት አላቸው፡፡ ቀብር አስፈጻሚዎች በሐዘን ወቅት ሚናቸው መጉላቱ ለውጡን ከሚያሳዩ ሁነቶች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጡ የመጡ ክንውኖችም አሉ፡፡ ጡሩንባ በመለፈፍ የሞተ ሰው መኖሩን ማሳወቅ እየደበዘዘ፣ በስልክ ጥሪና በጽሑፍ መልዕክት ለቅሶ ስለመኖሩ ማሳወቅ እየተስፋፋ ነው፡፡ የቀብር ዕለት የሟች ቤተሰቦች ሰልስት እንደማይኖር ሲገልጹ መስማትም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ አርባ፣ ሰማኒያና ሙት ዓመትን እንደ ቀድሞው በሰፊው ሰዎችን በመጥራት የነፍስ ይማር ዝክር የሚያደርጉ ቢኖሩም፣ የሃይማኖታዊ ሥርዓቱን አከናውኖ አቅመ ደካሞችን በመመገብ ዕለቱን ማሰብም እየተለመደ መጥቷል፡፡

ሰዎች ሐዘናቸው እንዳይፀናባቸው የሚደረጉ ጥረቶችን ቢደግፉም፣ በለቅሶ ወቅት የቀብር አስፈጻሚዎች ሚና የሰው ለሰው ግንኙነትን እያደበዘዘ መምጣቱ የሚያሠጋቸው ወ/ሮ በላይነሽ ገረሱ ናቸው፡፡ በዕድሜ በመግፋት ወይም ጤና በማጣት ሳቢያ የለቅሶ  ሥርዓቶችን መወጣት የማይችሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ በጎረቤቶቻቸው ወይም ዕድር ካላቸው በዕድሩ አባላት ቢታገዙም፣ ይህ አማራጭ በማይኖርበት ወቅት ወደ ቀብር አስፈጻሚዎች ፊታቸውን ሊያዞሩ ይችላሉ ይላሉ፡፡ አማራጭ እስካለ ድረስ ግን ጠቅላላ የለቅሶ ሥርዓት ከሟቹ ጋር ትውውቅ እንኳን በሌላቸው ሰዎች መከናወን እንደማይገባው ያምናሉ፡፡ ወይዘሮዋ በዋነኛነት የሚጠቅሱት ሬሳ መገነዝንና ለቀስተኞችን ማስተናገድን ነው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ቀብር አስፈጻሚዎች ሬሳ እንዲገንዙና ለቅሶ የሚደርሱ ሰዎችን እንዲያስተናግዱ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹መገነዝ ሰው የሚወደውን ሰው ሲያጣ የመጨረሻ ስንብቱን የሚያደርግበት መንገድ ነው፡፡ ሐዘንተኞችን ማስተናገድም እርስ በርስ ለመጽናናት ትልቅ ቦታ አለው፡፡ እነዚህ በሚቀራረቡ ሰዎች መካከል የሚከናወኑ ሥራዎችን ለባዳ መስጠት ሟችን ማቅለል ይመስለኛል፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የለቅሶ ሥርዓት እንደየአከባቢው ባህልና እንደየሰው ሃይማኖት የተለያየ ሒደት ሲኖረው፣ ሥርዓቶቹን ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው በሐዘን የተሰበረ ሥነ ልቡናን ለመጠገን ተገቢ ናቸው ተብሎ የታመነባቸው መንገዶችን መከተላቸው ነው ይላሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የለቅሶ ሥርዓት መጠነኛ ልዩነት ቢኖረውም፣ እሳቸው ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ባለው ሥርዓት፣ በተሸለመ ፈረስ  ወደ መቃብር ሥፍራ ይጋለብና ሟች ስላደረጋቸው ነገሮች እየገለጹ በማወደስ ‹‹ሆሆሆ. . .›› እየተባለ እንደሚለቀስ ይናገራሉ፡፡ በለቅሶ ካለው አለባበስ ጀምሮ የእዝን እንጀራና ወጥ ይዞ መሄድ፣ ለሐዘንተኞቹ የገንዘብ ድጎማ ማድረግ፣ ለቀስተኛ ማስተናገድ፣ ለቅሶ ቤት ማምሸት ወይም ማደር ማኅበራዊ ትስስር የሚገለጽባቸው መንገዶች በመሆናቸው መደብዘዝ እንደሌለባቸው ያምናሉ፡፡

ከዘመኑ ጋር ተያይዘው ስለመጡ ለውጦች ሲነሳ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሐዘን ለመግለጽ በሚል በሰውነት ላይ ጉዳት የማድረስ ልማድና ከቀብር በኋላ ከመጠን ያለፈ ገንዘብ የሚወጣባቸው አካሄዶች እየቀሩ መምጣታቸው መልካም ቢሆንም፣ በለውጥ ስም የማኅበረሰቡ መሠረት የሆኑ ሥርዓቶች እንዳይናዱ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ፡፡

ከማኅበረሰቡ የአኗኗር ለውጥ ጋር አብረው እየተቀየሩና በአዲስ ልማድ እየተተኩ ያሉ ሥርዓቶችን በመቃወም እንደ ቀድሞው ብቻ ካልሆነ ማለት ብዙ ርቀት ላያራምድ ይችላል፡፡ ቢሆንም መሻሻል የሚፈልጉና ጊዜ እንዳይሽራቸው መጠበቅ የሚገባቸው ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? የሚለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት ስንነጠቅ ከሚፈጠረው ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ለማገገም የምንወስዳቸው ግላዊ ዕርምጃዎች እንዳሉ ሆነው፣ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች እንዲሁም ገንዘብ ተከፍሏቸው አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦች ሚና ምን መሆን አለበት? የሚለውንም መጠየቅ ያሻል፡፡

እንደ መነሻ የወሰድነው የአዲስ አበባን ተሞክሮ ቢሆንም፣ የአንድ ሰው ሕይወት ካለፈ በኋላ ሥርዓተ ቀብር እስከሚፈጸምና ከተቀበረ በኋላ ያለው ሐዘን የሚገለጽበት መገንድና ሐዘንተኞችን ለማጽናናት የሚደረገው ጥረት የየአካባቢውን ባህል የተመረኮዘ እንደመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለው ለውጥም እንደየአካባቢው ይለያያል፡፡ ከተማ ቀመስ አካባቢዎች የሚስተዋለው ለውጥ የተቀረው የአገሪቱ ክፍሎችም ዕውነታ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በለቅሶ ወቅት በሟች ዙሪያ ያሉ ሰዎች ያላቸውን ኃላፊነት በተመለከተ በዳውሮ ብሔረሰብና በአፋር ክልል ያለውን ሥርዓት እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡

በደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን ቀብር ከተፈጸመ በኋላ ምሽት ላይ ወጣቶች በቡድን ተከፋፍለው በመተራረብና በመቀለድ ይወዳደራሉ፡፡ ይህም ሐዘንን ለማስረሳትና ለማጽናናት የሚደረግ ነው፡፡ በአፋር ክልል ሰው የሞተባቸውን ለማጽናናት የቤት እንስሳት ተይዞ ለቅሶ ይደረሳል፡፡ ሰዎች እንደየአቅማቸው በሐዘን ወቅት የሚደጋገፉበት ሥርዓት እንደ ግዴታ ስለሚወሰድ፣ ኃላፊነቱን ያልተወጣ ሰው ይነቀፋል፡፡ በዘሐን ወቅት የሥራ ክፍፍል በመውሰድ መደጋገፍ እንደ አንድ የለቅሶ ሒደት እንደሚወሰድ ከነዚህ ሥርዓቶች መረዳት ይቻላል፡፡ በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚረዱም ይታመናል፡፡

የነጋሽ ደገፉ ቀብር አስፈጻሚ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንደሚናገረው፣ ቀብር አስፈጻሚዎች በለቅሶ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከሰዎች ፍላጎት አንፃር በዓይነትና በቁጥርም እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ንግዱ ሲጀመር የሬሳ ሳጥንና የአባባ ጉንጉን መሸጥን ብቻ ያማከለ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ቀብር የሚወስድ መኪናና ቀብር የሚያጅቡ ፕሮቶኮሎችን ማዘጋጀት፣ በመቀጠልም ድንኳና ሌሎችም ለለቅሶ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ወደ ማከራየት ተሸጋገረ፡፡ አሁን አገልግሎቱ ሬሳ ከሆስፒታል ወደ ሟች መኖሪያ ቤት መውሰድ፣ መገነዝ፣ ለቀስተኞችን በአውቶብስ ቀብር ቦታ መውሰድ፣ ምግብ ማዘጋጀት፣ ቡና ማፍላትና መስተንግዶንም ያካትታል፡፡

እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) እና በሪል ስቴቶች ቤት ገዝተው የሚኖሩ ሰዎች ከአጎራባቾቻቸው ጋር እስከሚተዋወቁ (ሳይተዋወቁ የሚቀሩበትም ጊዜ አለ) በለቅሶ ወቅት የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውንላቸው ድርጅት ከመቅጠር ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ ቀብር አስፈጻሚዎች እንደ ሐዘንተኞቹ አቅም ዘመናዊ የቀብር መኪና ከማከራየት ጀምሮ የተለያዩ ዓይነት ምግቦችም ያሰናዳሉ፡፡ በሐዘን ቤቱ ሻማ፣ አበባና የሟችን ፎቶ ያስቀምጣሉ፡፡

ቀብር አስፈጻሚዎች ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች መካከል ሁሉንም የሚወስዱ እንዲሁም የሚፈልጉትን ብቻ የሚመርጡ ያሉ ሲሆን፣ ከ500 ብር እስከ 30,000 ብር ድረስ እንደየአገልግሎቱ ይከፍላሉ፡፡ ዕድር ያላቸው፣ ሠፈር በመቀየር ምክንያት ከዕድር የወጡና ዕድር ያልገቡ ተጠቃሚዎችም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይናገራል፡፡

በእሱ እምነት፣ ዕድርን የመሰሉ ዕድሜ ጠገብ የማኅበራዊ ትስስር መገለጫዎችን መተካት ባይቻልም፣ አማራጭ አገልግሎት ሰጪዎች በንግድ መልክ ተፈጥረዋል፡፡  ‹‹ዕድር ጫፍ ላይ አንደርስም፤ ሐዘንተኞች በተለያየ መንገድ የሚያጽናናበት መንገድ አሁንም ያለ ሲሆን፣ እኛ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ክፍተቱን እንሞላለን፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ቀብር ማስፈጸም ንግድ እንደመሆኑ፣ በለቅሶ ሥርዓት ያሉ ክፍተቶችን እያስተዋሉ አዳዲስ አገልግሎቶች ይጨምራሉ፡፡ ለምሳሌ የሚጠቅሰው፣ ሰዎች እክል ገጥሟቸው ለቅሶውን ለማከናወን ገንዘብ ሳይኖራቸው ሲቀር በረዥን ጊዜ በሚከፈል ዱቤ አገልግሎቶቻቸውን መስጠት መጀመራቸውን ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ አሁን ማዘጋጃ ቤት እንደሚያደርገው በሃይማኖት ምክንያት በአንድ ሃይማኖታዊ ተቋም መቀበር ላልቻሉ ሰዎች የግል መቀበሪያ የማዘጋጀት ዕቅድ አላቸው፡፡

እሱ እንደሚለው፣ የቀብር አስፈጻሚዎችን አገልግሎት የሚጠቀሙ ሰዎች መጨመራቸው አንድም የማኅበረሰቡ አኗኗር መለወጡን ያመላክታል፡፡ ወደ ቢዝነሱ የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥር መጨመሩ የተጠቃሚዎች ቁጥር እየናረ ስለመምጣቱ ማስረጃ ይሆናልም ይላል፡፡ ቀብር አስፈጻሚዎቹ የሰዎች ምርጫ እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ይመስላሉ፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ ያለው ጥያቄ ደግሞ በለቅሶ ጊዜ ለቅሶን ለሚያቀናብሩ ድርጅቶች መሰጠት ያለባቸውና የሌለባቸው ክንውኖች የትኞቹ ናቸው የሚለው ነው፡፡ ethiopianreporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy