CURRENT

የህወሓት መስራቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ተማፀኑ

By Admin

March 23, 2017

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባርን (ህወሓትን) ከመሰረቱት 11 ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አሰገደ ገብረስላሴ በልብ ህመምና በደም ቧንቧ መጥበብ በተከሰተ ህመም ህይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ገለጹ። ለህክምናም ከ300 ሺህ ዶላር (ስምንት ሚሊዮን ብር ገደማ) እንደሚያስፈልግ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት ደብዳቤ ገልጸዋል።

አቶ አሰገደ ውጭ ሀገር ሂደው እንዲታከሙ የህክምና ተቋማት ቢገልጹላቸውም የገንዘብ ችግር ስለገጠማቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝና እና ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ ለሀገር መካለከያ ሰራዊት፣ ለኢህአዴግ ዋና ጽ/ቤት፣ ለኢፈርት ዋና ጽ/ቤት፣ ለጄኔራል ሳሞራ የኑስና ለአራቱ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እንዲሁም ለጥረት ዋና ጽ/ቤት እና ለትግራይ ልማት ማህበር (ትልማ) በጻፉት የእርዳታ ድጋፍ ጥያቄ “በአሁኑ ወቅት ከእናንተ ጋር ምንም እንኳ የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረኝም ለ19 ዓመት ሙሉ እልህ  አስጨራሽ የትጥቅ ትግል ለአንድም ሰዓት ሳላርፍ በትግሉ ምክንያት ከመላው አካላቴ 33 በመቶ ያጎደልኩበት በመሆኑ ልትረዱኝ ይገባል፣ ቀሪውን እድሜዬን ትንሽ ለማራዘም ቢያንስ 300 ሺህ ዶላር እርዳታ ታደርጉልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ” ሲሉ አስታውቀዋል።

አቶ አሰገደ ለቀድሞ ጓዶቻቸው የድጋፍ ጥያቄያቸወን ያቀረቡበትን ምክንያት ሲገልጹም “በመገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ባቀርብ በህዝብ ላስወቅሳቸው ሰላልፈለኩ ነው” ብለዋል። “ለህክምና የሚፈጅብኝ ገንዘብ መልካም ፈቃዳችሁ ከሆነ ለእናንተ ከባድ ባለመሆኑ” ብለው ጥያቄያቸውን ያቀረቡት አቶ አሰገደ ጥያቄ ያቀረቡላቸው የኢህአዴግ ባለስልጣናትም ሆኑ የኢህአዴግ ድርጅቶች እስከትላንትናው ዕለት ድረስ ለጥያቄያቸው መልስ እንዳልሰጣቸው ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። አቶ አሰገደ አያይዘውም “አሁን የምገኘው የማስታገሻ መድሃኒት እየወሰድኩ ሲሆን የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ስላለብኝ ህመሙ ሊበረታብኝ ችሏል” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አሰገደ ገብረስላሴ ከትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ህወሓት) መስራቾች አንዱ ሲሆኑ ከእናት ድርጅታቸው ህወሓት በ1985 ዓም ተለይተው ከወጡ በኋላ ሶስት ቅጾች ያሉት “ጋኅዲ” የተባለ መጽሀፍ ደራሲ ናቸው።